የኢትዮጵያን ባለ ልዩ ጣዕም ቡናዎች ለአለም ለማስተዋወቅ የሚያስችል ጉባኤ እየተካሄደ ነው



በአዲሰ አበባ እየተካሄደ ያለው አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ቡናዎች ላኪዎች ጉባኤ የኢትዮጵያን ባለ ልዩ ጣዕም ቡናዎች ለአለም ለማስተዋወቅ፣ በአለም አቀፍ ገበያ ያላቸውን ተቀባይነት ለማሳደግና የገጠሙትን ፈተናዎች ተወያይቶ ለመፍታት አልሟል፡፡


ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ዘርፉ ለኢትዮጵያ 1 ሚሊዬን አርሶ አደሮችና ለሌሎች 15 ሚሊዬን ዜጎች የስራ እድል በመፍጠርና የገቢ ምንጭ በመሆን የሸቀጦች የውጭ ንግድን በበላይነት እየመራ መሆኑን ተናግረዋል፤ ለዘርፉ መጠናከርም የመንግስት ቁርጠኝነት እንደሚቀጥል ነው የገለፁት፡፡

«መንግስት በቡና ዘርፍ ሙሉ ድጋፍ መስጠቱን አጠናክሮ ይቀጠላል፡፡ ባለ ልዩ ጣዕም ቡናዎች ምቹ ተፈጥሯዊ ሁኔታ ያለንን ያክል ከዘርፉ ተጠቃሚዎች መሆን አለብን፡፡ እኛ በኢትዮጵያ በአነስተኛ ማሳዎች ቡና ለሚያሙ አርሶ አደሮች ትኩረት ሰጥተን እየደገፍን ነው፡፡ የግሉ ባለሃብትም በዘርፉ እንዲሰማራ ሰፊ ጥረትም ተደረጓል፡፡ ቁጥሩ ብዙ የሆነ የግል ባለሃብትም በዘርፉ ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡»

የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ በበኩላቸው የቡናው ዘርፍን ለመደገፍ መንግስት የግብይት ስርዓቱን በማዛመን፣ የትራንስፖርት ችግሮችን በመቅረፍና ገበያ በማፈላለግ ለዘርፉ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

«ኢትዮጵያ ድህነትን በመቅረፍ ረገድ አበረታች ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች፤ የግብርና ምርቷንም በእጥፍ ለማሳደግ አቅዳ እየሰራች ነው፤ አሁንም ለቡና ጥራትና ምርታማነት ብዙ ተግባራት እያናከወነች ነው፡፡ ግብይቱ ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆንም እየሰራች ትገኛለች፡፡»

በጉባኤው እየተሳተፉ የሚገኙ የቡና ላኪዎችም ዘርፉ የበለጠ እንዲጠናከር በኃይል አቅርቦት፣ በመልቲ ሞዳል ትራንስፖርትና በጆንያ አቅርቦት በኩል ለሚስተዋሉ ችግሮች ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

”የኢትዮጵያን ቡናዎች መልካም ስም እናስቀጥል” በሚል ርዕስ የሚካሄደው ጉባኤ በቡና ምርት ጥራት፣ አለም አቀፍ የገበያ ሁኔታዎችና አእምሯዊ ንብረት ጉዳዮች ላይ በማተኮር ለሁለት ቀናት ይካሄዳል፡፡

ኢትዮጵያ በ2005 ከቡና የወጭ ንግድ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዬን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት አቅዳ እየሰራችም ነው፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር