የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት ወደ ግብፅ ሊጓዙ ነው



በዮሐንስ አንበርብር
ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ አባላትን ያካተተ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥትን በመወከል፣ ኢትዮጵያ የምትገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ በዓባይ ወንዝ ላይ ምንም ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን ለማስረዳት፣ የኢትዮጵያንና የግብፅን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር የሚል ተልዕኮ ይዞ ወደ ግብፅ ሊያቀና ነው፡፡
የዲፕሎማሲ ቡድኑ አባላት ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ከታዋቂ ሰዎች፣ ከመገናኛ ብዙኅን፣ ከሥነ ጥበብና ከእምነት መሪዎች የተውጣጡ ሲሆን፣ በትናንትናው ዕለትም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተገኝተው በተጠባባቂ ማኒስትሩ አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ገለጻ ተደርጐላቸዋል፡፡

ኢትዮጵያና ግብፅ የረዥም ዘመናት ግንኙነት ያላቸው አገሮች መሆናቸውን በመጥቀስ ገለጻቸውን የጀመሩት ተጠባባቂ ሚኒስትሩ፣ ይህ ግንኙነታቸው ከተፈጥሮና ከመንፈሳዊ እምነት ጋር የተዛመደ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡

በዚህ ረጅም ዘመን የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የሚያስተሳስሩ በርካታ መልካም ነገሮች የመኖራቸውን ያህል፣ በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱ የፖለቲካ መሪዎችም ግንኙነታቸውን ሲያሻክሩና ጠባሳ ለመፍጠር ሲሞክሩ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ግን ሁለቱ አገሮች ከዚህ ቀደም የነበራቸውን አለመግባባት ለመቅረፍ ጥረት መደረጉን የገለጹት ተጠባባቂ ሚኒስትሩ አምባሳደር ብርሃነ፣ እ.ኤ.አ. በ1993 የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ወደ ግብፅ በመሄድ የሥራ ጉብኝት ያደረጉ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

በዚህ ወቅትም አቶ መለስ መንግሥታቸው በዓባይ ጉዳይ ላይ መወያየትን እንደሚፈልግ በመግለጻቸው፣ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የሁለቱ አገሮች ውይይት እንደተጀመረና በከፍተኛ ሁኔታ እንዳደገ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ግብፆች ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ምክንያት ትጐዳናለች የሚል የቆየ እምነታቸው እየተሸረሸረ መምጣቱን፣ በቅርቡም የፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክን አገዛዝ ሕዝቡ በትግሉ ካስወገደ በኋላ የግብፅ ሕዝብን የሚወክሉ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

የግብፅን ሕዝብ የወከለው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባላትም በወቅቱ ከተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የተገናኙ መሆናቸውን አውስተው፣ በወቅቱ የጠየቁት በዓባይ ላይ ለመገንባት የታሰበው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግብፅን ሊጎዳ ይችላል ወይ የሚል እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በወቅቱ ኢትዮጵያ የምትገነባው የህዳሴ ግድብ ወንድም የሆነውን የግብፅ ሕዝብ ፈጽሞ እንደማይጐዳ፣ ይህንንም ለማረጋገጥና ለማስተማመን ከኢትዮጵያ፣ ከሱዳን፣ ከግብፅና ከዓለም አቀፍ ተቋማት የተውጣጡ የኤክስፐርቶች ቡድን እንዲቋቋምና እንዲገመግመው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ቃል ገብተው ነበር ብለዋል፡፡ በዚህም መሠረት የቴክኒክ ቡድኑ ተቋቁሞ በሥራ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹እናንተም በዚሁ መሠረት ወደ ግብፅ ሄዳችሁ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ፍላጐት ምን እንደሆነ በትክክል እንድታስረዱ እንፈልጋለን፤›› በማለት ለኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባላት ገልጸዋል፡፡

‹‹ዓባይን ገድቦ የግብፅ ሕዝብን መጉዳት በሰው ልጅ ሰብዓዊነት ላይ ወንጀል መፈጸም ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይም ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ በተሳሰረው የግብፅ ሕዝብ ላይ ጉዳት ሊፈጽም ፈጽሞ እንደማይፈልግ እንድታስረዱ እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡

የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባላቱ የተደረገላቸው ገለጻ በእጅጉ እንዳስደሰታቸው በመግለጽ፣ ከዚህ ቀደም ከግብፃውያን ጋር ሲገናኙ የነበራቸውን ተሞክሮ ለመድረኩ አስረድተዋል፡፡

በተለያዩ አጋጣሚዎች በኢትዮጵያም ይሁን በውጭ አገሮች ከሚያገኟቸው ግብፃውያን ጋር በሚገናኙበት ወቅት ከግብፃውያኑ የሚሰሙት ልማቱ ለሁሉም ሊጠቅም የሚችል መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን የውኃው መጠን ይቀንሳል የሚል ፍራቻ እንዳላቸው አስረድተው፣ በመሆኑም ይህንን ፍራቻ ለማስወገድ ራሳቸውን በመረጃ እንደሚያደራጁ አባላቱ ገልጸዋል፡፡

ከፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላቱ መካከል አቶ ብርሃነ ዴሬሳ፣ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፣ ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ፣ የዓለም ሎሬት ጥበበ የማነ ብርሃን፣ አቶ ሀብተ ሥላሴ ታፈሰ፣ አምባሳደር ብርሃነ ገብራይ፣ ዶ/ር ኃይለ ሚካኤል አበራ፣ አቶ አማረ አረጋዊ፣ አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ፣ ወ/ት ሀያት አህመድ፣ አቶ ሙሼ ሰሙ፣ ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ፣ ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌ ዴሌቦ ይገኙበታል፡፡ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ በመጪው ታህሳስ ወር ውስጥ ወደ ግብፅ ያቀናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/8562-2012-11-17-12-42-01.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር