ሀዋሳ መንገድ ላይ ትልቅ ኣየር ማረፊያ ልገነባ ነው


ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ ለሚገነባው አውሮፕላን ማረፊያ ድጋፋቸውን ሰጡ


   የቦሌ መንገደኞች ተርሚናል ማስፋፊያ ሥራ ሊካሄድ ነው
በቃለየሱስ በቀለ
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በሞጆ አካባቢ ለመገንባት ላቀደው ግዙፍ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ድጋፋቸውን ገለጹ፡፡ የኤርፖርቶች ድርጅት አንድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢንተርፕራይዙን በኤርፖርት ግንባታው ዕቅድ ላይ ቀጣይ ሥራ እንዲሠራ መመርያ ሰጥተውታል፡፡ አዲስ ስለሚገነባው ኤርፖርት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ በቅርቡ የሰጡት የትራንስፖርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የሥራ ኃላፊዎች ናቸው፡፡

የአዲሱ ኤርፖርት ግንባታ ፕሮጀክት ዕቅድ በቅርቡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ የሚፀድቅ ሲሆን፣ በመቀጠል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀርባል፡፡ ለፕሮጀክቱ የሚሆን ገንዘብ ከቻይናው ኤግዚም ባንክ እንደሚጠየቅ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

አዲስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መገንባት ያስፈለገበት ምክንያት የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እየተጨናነቀ በመሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፍጥነት በማደጉና በርካታ አውሮፕላኖች በመግዛት ላይ በመሆኑ፣ የተለያዩ አገሮች አየር መንገዶች ወደ አዲስ አበባ በረራ መጀመራቸው ለኤርፖርቱ መጨናነቅ እንደ ምክንያት ተቆጥሯል፡፡ በተጨማሪም መደበኛ የበረራ አገልግሎት፣ ጄነራል አቪዬሽን (መደበኛ ያልሆነ የቻርተር በረራ አገልግሎት) እንዲሁም የ‹‹ቪአይፒ›› በረራዎች በአጠቃላይ በአንድ ኤርፖርት መስተናገዳቸው የሥራ ጫና ፈጥሯል፡፡

በተለይ እንደ ሴስና ያሉ ትናንሽ አውሮፕላኖችንና እንደ ቦይንግና ኤርባስ ዓይነት ትላልቅ አውሮፕላኖችን በአንድ ኤርፖርት ማስተናገድ ለአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተፈጠረው የአየር ክልል መጨናነቅ የተወሰኑ የበረራ መለማመጃ አውሮፕላኖችን ወደ ደብረ ዘይትና ድሬዳዋ በመውሰድ አብራሪዎቹን በኢትዮጵያ አየር ኃይል ቅጥር ግቢ በማሠልጠን ላይ ይገኛል፡፡

አዲሱን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት የታቀደው ሐዋሳ መንገድ ላይ ሞጆና መቂ ከተሞች መካከል ሜዳማ ቦታ ላይ ሲሆን፣ ይህ ቦታ ሊመረጥ የቻለው ሜዳማ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ዝቅተኛ አልቲቲዩድ ያለው በመሆኑና አውሮፕላኖች በተለይ በሚነሱበት ጊዜ የሚፈጁትን ነዳጅ መጠን መቀነስ ስለሚያስችል ነው፡፡ በተጨማሪም አውሮፕላኖቹ የተሻለ ክበደት ጭነው መነሳት ይችላሉ፡፡

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች  ደርጅት በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሦስተኛ የማስፋፊያ ሥራ ለመሥራት በዝግጅት ላይ መሆኑ ታወቀ፡፡ ድርጅቱ ከዚህ በፊት አንደኛ የማስፋፊያ ሥራ (24 የአውሮፕላኖች ማቆሚያ) ያካሄደ ሲሆን፣ ሁለተኛውን የማስፋፊያ ሥራ (14 አውሮፕላኖች ማቆሚያ) በቅርቡ ያጠናቅቃል፡፡ በሦስተኛው ማስፋፊያ ፕሮጀክት ተርሚናል ሁለት (አዲሱ ተርሚናል) የማስፋፋት ሥራ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት አሁን ካለው ተርሚናል ሁለት ቀጣይ ሕንፃ የሚገነባ ሲሆን፣ ከተርሚናል አንድ (አሮጌው ተርሚናል) ጋር ይገጥማል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአዲሱ ሕንፃ የንድፍ ሥራ በመካሄድ ላይ ነው፡፡ በቀጣይ የሕንፃውን ግንባታ የሚያካሂድ ኮንትራክተርና አማካሪ ድርጅት ለመቅጠር ጨረታ እንደሚወጣ ለማወቅ ተችሏል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/8382-2012-11-03-12-11-48.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር