ግልጽነትና ተጠያቂነት የመልካም አስተዳደር ወሳኝ መሣሪያዎች ናቸው



ሕዝብም መልካም አስተዳደር እፈልጋለሁ ይላል፡፡ መንግሥትም መልካም አስተዳደርን ማስፈንና ማረጋገጥ ራዕዬ፣ ዓላማዬና ዕቅዴ ነው ይላል፡፡ በዚህ ላይ ልዩነት የለም፡፡ በአባባል፣  በፍላጎትና በምኞት ደረጃ፡፡
መልካም አስተዳደርን ተግባራዊ ለማድረግ ግን የግድ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን በተግባር ማስፈን ያስፈልጋል፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ከሌለ መልካም አስተዳደር አይኖርም፣ አይሰፍንም፡፡

ግልጽነት ሲባል ትርጉሙ ‹‹ግልጽና ግልጽ›› ነው፡፡ በሕዝብ ተመርጫለሁ የሚል መንግሥት ውክልና ሰጥቶ፣ መርጦ ለሥልጣን ላበቃው ሕዝብ የሚሠራውንና የሚያስበውን በግልጽ ማሳወቅ አለበት፡፡

ሕዝብ መንግሥትን እዚህ ጋ ተሳስተሃል፣ እዚህ ጋ አጥፍተሃል፣ እዚህ ጋ ጥሩ ሠርተሃል፣ እዚህ ጋ እንዲህ ብታደርግ ይሻላል በማለት ሕገ መንግሥቱ የሰጠውን መብት ተጠቅሞ ሐሳብ ለመስጠት፣ ሂስ ለማቅረብና ድጋፉን ለመግለጽ መንግሥት የሚያከናውነውን ሁሉ በግልጽ ሊያውቀው ይገባል፡፡ መንግሥት ግልጽ ሊሆንለት ይገባል፡፡

ሕገ መንግሥታችን ግልጽነትን ይደግፋል፡፡ ሁሉም ነገር ለሕዝብ ግልጽ እንዲሆን የሚያዝና የሚደነግግ ሕግም አለን፡፡ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ፡፡ በሕገ መንግሥትና በሕግ በኩል በአገራችን ግልጽነት እንዳይኖር የሚያደርግ አንዳችም ነገር የለም፡፡ በተግባር ግን ግልጽነት እየተዳከመ ነው፡፡ በተግባር ግን ቢሮክራሲው የሚጠቅመውን ይናገራል፤ የማይጠቅመውንና የሚያጋልጠውን ይደብቃል እንጂ ግልጽነት (ትራንስፓረንሲ) እውን ሊሆን አልቻለም፡፡ ለመልካም አስተዳደር ትልቅ የተደቀነ እንቅፋት የሆነው የግልጽነት አለመኖር ሆኗል፡፡

ተጠያቂነትን (አካውንተቢሊቲ) በሚመለከትም ሕገ መንግሥታችንና ሕጎቻችን የሚደግፉትና የሚያበረታቱት ናቸው፡፡ በተግባር ግን ተጠያቂነት እየጠፋ ነው፡፡ ቢሮክራሲው በሚጠቅመው መንገድ እያሽከረከረው ነው፡፡ ሕዝብን ለመምራት፣ ሥራን ለማከናወንና ዳር ለማድረስ ኃላፊነት ተሰጥቶት የተሾመ ወይም የተቀመጠ ሰው የተሰጠውን ኃላፊነትና ሥራ በአግባቡ ሠርቷል ወይስ አልሠራም ተብሎ ሊጠየቅ ይገባል፡፡ ሥራውን ካልሠራ፣ ካበላሸ፣ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ካላከናወነና የተሰጠውን በጀት በአግባቡ ካልተጠቀመ ለምን ይህን አደረግክ ወይም አላደረግክም ተብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ ተጠያቂ መሆን አለበት፡፡

ተጠያቂነት ሊኖር የሚችለው ግልጽነት ሲኖር ነው፡፡ አንድ ሹም ወይም ሠራተኛ ተጠያቂ ሊሆን የሚችለው ጥፋቱ ሲታወቅ ነው፡፡ ጥፋቱ ሊታወቅ የሚችለው ደግሞ ግልጽነት ሲኖር ነው፡፡ መረጃ ማግኘት ሲቻል ነው፡፡

ግልጽነትና ተጠያቂነት ካለ መልካም አስተዳደር ይኖራል፡፡ ሕዝብ ስለአገሩ ሁኔታ በትክክል መረጃ ይኖረዋል፡፡ ግልጽነት አለና፡፡ በያዘው መረጃ ደግሞ በትክክል የሚሠራውንና የማይሠራውን በመለየት ተጠያቂ ማድረግና ዕርምጃ ማስወሰድ ይችላል፡፡ ይህንን ማድረግ ከቻለ ደግሞ መልካም አስተዳደር ይኖራል ማለት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ተያይዘው እየተንከባለሉ ያሉት ሦስቱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ግልጽነት እየተዳከመ ነው፡፡ ተጠያቂነት እየጠፋ ነው፡፡ መልካም አስተዳደር ‹‹ላም አለኝ በሰላም ወተቷንም አላይ›› እየሆነ ነው፡፡

ሕዝብም መንግሥትም በጋራ ለግልጽነትና ለተጠያቂነት መታገል አለባቸው፡፡ ሕዝብ ለመብቱ ይቁም፤ መንግሥት ግዴታውን ይፈጽም፡፡ አሁን ሥራዎች እየተከናወኑ ያሉት በጉቦ፣ በእከከኝ ልከክህ ግንኙነትና በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ነው፡፡ ሕግ፣ ሥርዓት፣ ፍትሕ፣ መብትና ግዴታ የሚባሉ ቁምነገሮች ቀልድና ፌዝ ሆነዋል፡፡

ሕዝብ ይበደላል፣ አቤት የሚልበት ይጠፋዋል፡፡ ጥያቄ ቀርቦም፣ ማመልከቻ ገብቶም፣ እንባ ፈሶም መልስ የሚመልስና እንባ የሚያብስ የለም፡፡ ምክንያቱ አይታወቅም፡፡ ግልጽነት የለም፤ የበደለ ዕርምጃ አይወሰድበትም፤ ተጠያቂነት የለም፡፡ በዚህም ምክንያት መልካም አስተዳደር የለም፡፡
የቀረቡ አቤቱታዎችን የሚያያቸው የለም፡፡ በደል በፈጸመ ላይ ዕርምጃ የሚወስድበት የለም፡፡ መንግሥት ለዚህ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መፍትሔ ለመስጠት ሊረባረብ ይገባል፡፡ የሕዝብ ጥያቄ መልስ የሚያገኝበትን መንገድ ማመቻቸት አለበት፡፡ ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ ተሳታፊ መሆን አለበት የሚል ሕገ መንግሥት ተይዞ፣ ሕዝብን አሳታፊ የሆነውን መንገድ የሚዘጋ አካሄድ ግን ሊኖር አይገባም፡፡ ሕዝቡ እየተሸማቀቀ ወንጀለኛ፣ ማፍያ፣ ጉቦኛና ቀማኛ በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት ማኅበረሰብ ሊኖረን አይገባም፡፡

በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ የመንግሥት ሹማምንትና ተቋማት ችግሩን እየተገነዘቡ አሳሳቢነቱን በግልጽ መናገር ሲጀምሩ፣ ሌሎች የመንግሥት ሹማምንትና አካላት ደግሞ እነሱን ሲቃወሙና ችግሩን ሲያስተባብሉ እየሰማን ነው፡፡ መንግሥት ሕዝቡን ብቻ ሳይሆን ችግር አለ የሚሉ የራሱን ሰዎችና የራሱን ተቋማትም ማዳመጥና ማበረታታት አለበት፡፡

የመልካም አስተዳደር እጦት ከምንምጊዜም በላይ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ይህ ችግር የኢንቨስትመንት አመኔታን ያዳክማል፣ ለስርቆትና ለወንጀል አበረታች ሆኗል፡፡ ሌባ እየፈነደቀ ሕዝብ የሚሸማቀቅበት ድባብ እየተከሰተ ነው፡፡ ይብቃ፡፡

ግልጽነትና ተጠያቂነት የመልካም አስተዳደር ቁልፍ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ መንግሥትና ሕዝብም ለግልጽነት፣ ለተጠያቂነትና ለመልካም አስተዳደር ዘብ ይቁሙ!
http://www.ethiopianreporter.com/editorial/294-editorial/8510-2012-11-17-08-37-25.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር