የሐዋሳ ፍርድ ቤት በአንድ የወንጀል ድርጊት ሁለት የተለያዩ ቅጣቶችን መወሰኑ እያነጋገረ ነው



-    በአንደኛው ቅጣት 10 ዓመት በሌላኛው ደግሞ ዕድሜ ልክ እስራት ወስኗል

በታምሩ ጽጌ

በደቡብ ክልል የሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአንድ ወጣት ላይ በተፈጸመ የግድያ ወንጀል በቀረቡለት የተለያዩ ክሶች ላይ የተለያዩ የቅጣት ውሳኔዎችን መስጠቱ እያነጋገረ ነው፡፡

ድርጊቱ የተፈጸመው አማረ ሙሉጌታ በተባለ የ23 ዓመት ወጣት ላይ በሐዋሳ ከተማ ሚያዝያ 5 ቀን 2003 ዓ.ም. ምሽት ላይ መሆኑን፣ ሁለቱም የክልሉ የከፍተኛ መርማሪ ከሳሾች ክሶች ያስረዳሉ፡፡

የከተማው ከፍተኛ መርማሪ ከሳሽ መጀመርያ ለሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግንቦት 29 ቀን 2003 ዓ.ም. ክሱን ያቀረበ ሲሆን፣ ለክሱ መነሻ የሆነው ፍሬ ጉዳይ አማረ ሙሉጌታ በተባለ የ23 ዓመት ወጣት ላይ በሁለት ጓደኞቹ የተፈጸመን የግፍ አገዳደል ወንጀል የሚያስረዳ ነው፡፡

ከሳሽ በክሱ ላይ እንዳብራራው፣ ሟች አማረ ሚያዝያ 5 ቀን 2003 ዓ.ም. እስከ ሌሊቱ አጋማሽ ድረስ አፈወርቅ ሌሊሳና ውብሸት ደሞል ከሚባሉ ጓደኞቹ ጋር በተለያዩ ሬስቶራንቶችና ሆቴሎች ሲዝናኑ ያመሻሉ፡፡ ጓደኞቹ አስቀድመው በነበራቸው የመግደል ሐሳብ፣ ወጣቱን በተለያዩ መጠጥ ቤቶች በማዞርና በማጠጣት በስካር ራሱን እንዲስት ካደረጉት በኋላ፣ ወደ ሰዋራ ሥፍራ በመውሰድ ውብሸት የተባለው ጓደኛው ሲይዘው፣ ጌታሁን የተባለው ሌላኛው ጓደኛው በስለት የግራ ደረቱን እንደወጋው ክሱ ያብራራል፡፡


ጓደኞቹ ድርጊቱን ሌላ ሰው የፈጸመው ለማስመሰል ለመሞት በማጣጣር ላይ የነበረውን አማረ ሙሉጌታን በመሸከም አሴር ወደሚባል ሆስፒታል ቢወስዱትም፣ ሕክምና ሳይደረግለት ሕይወቱ ማለፉን የቅጣት ውሳኔው ሰነድ ያስረዳል፡፡

ጓደኞቹ በጥርጣሬ ተይዘው ከታሰሩ በኋላ ፍርድ ቤት ቀርበው በሰጡት ቃል፣ ጓደኛቸው መሆኑንና ለሦስት ዓመታት እንደሚተዋወቁ፣ ድርጊቱ ተፈጸመ በተባለበት ዕለትም እስከ ምሽቱ ሰባት ሰዓት አካባቢ አብረው መቆየታቸውን ካስረዱ በኋላ፣ አብረው እንዲሄዱ ሲለምኑት ባለመስማማቱ ተለይቷቸው ከሄደ ከደቂቃዎች በኋላ እሱ ወደታጠፈበት ቦታ ሲሄዱ ወድቆ እንዳገኙትና ወደ ሆስፒታል እንዳደረሱት በመግለጽ፣ ቃላቸውን መስጠታቸውን ውሳኔው ይገልጻል፡፡

ከሳሽ የከተማው ዋና መርማሪ አምስት አስረጅ ምስክሮችን ለፍርድ ቤቱ አቅርቦ ያሰማ ሲሆን፣ አንደኛ ምስክር ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ሟችና ተጠርጣሪዎች እየተጨቃጨቁ ሲሄዱ ማየቱንና አብረውት እንዲሄዱ ሲለምኑት እንደነበር፣ እንደማይሄድ ሲነግራቸው ስልኩን እንዲሰጣቸው ሲጠይቁት እንዳልሰጣቸውና ወደ ስታዲየም ትቷቸው መሄዱን ገልጾ፣ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ተሸክመውት ወደ ሆስፒታል ሲወስዱት ማየቱንና ‹‹ወግተውት›› ሸሹ እንዳሉት ሲመሰክር፣ ቀሪዎቹም የሆስፒታሉ የጥበቃ ሠራተኛና ሌሎችም ምስክሮች ያዩትን መመስከራቸውን ውሳኔው ይገልጻል፡፡

ፍርድ ቤቱ የምስክሮቹን ቃል ከተቀበለ በኋላ ምስክሮቹ የሰው ግድያ ወንጀልን በሚያሟላ መልኩ አለማስረዳታቸውን ገልጾ፣ ተከሳሾቹ የተከሰሱበትን አንቀጽ በመቀየር በወንጀል ሕጉ 540 መሠረት እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾቹ የተከሳሽነት ቃላቸውን ከሰጡ በኋላ መከላከያ ምስክሮቻቸውን ማሰማታቸውን የሚገልጸው ውሳኔው፣ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ለመመርመር ተከሳሾቹ ተከላከሉ በተባሉበት የሕግ አንቀጽ ሥር ተከላክለዋል? ወይስ አልተከላከሉም? ጥፋተኛ ናቸው ወይስ አይደሉም? የሚለውን ጭብጥ ይዞ መመርመሩን ውሳኔው ያብራራል፡፡

ሟች በግራ በኩል የላይኛው ደረቱ ላይ ተወግቶ መሞቱን የሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ማረጋገጡንና በተከሳሾቹ አንደበት መረጋገጡን፣ በፖሊስ አማካይነት ፍርድ ቤት ቀርበው በወንጀል ሕጉ 35 መሠረት ከሰጡት ቃልና ከሳሽ ካቀረበው እንዲሁም ከተከሳሾች የተከሳሽነት ቃል ፍርድ ቤቱ ግምት መወሰዱን በመተንተን፣ ሟችና ተጠርጣሪዎች አብረው ማምሸታቸውንና አብረን ካላደርን በሚል ተጨቃጭቀው፣ ‹‹እሄዳለሁ አትሄድም›› ሲባባሉ በተደረገው ትግል የአንደኛው አንገት ተቧጭሮ መቁሰሉንና የአንደኛ ተከሳሽ እጅ በሟች መነከሱን፣ ሟች ይዞት በነበረ 10 ሺሕ ብር ቼክም አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበር ፍርድ ቤቱ ማረጋገጥ መቻሉን በውሳኔው አስፍሯል፡፡

ተከሳሾቹ ወድቆ አግኝተው ወደ ሆስፒታል መውሰዳቸውን ገልጸው እንዳልገደሉት ቢናገሩም፣ ከመለያየታቸው በፊት ተፈጥሮ በነበረው አለመግባባትና በአምስት ደቂቃ ውስጥ ሟች በሌላ ሰው ተወግቶ ወድቆ እንዳገኙት መናገራቸውን ፍርድ ቤቱን ሊያሳምነው ባለመቻሉ፣ ሟች ደውሎ እንዳይናገር ስልኩን እንዲሰጣቸው መጠየቃቸው፣ ሊወስዱት ይታገሉት የነበረው ወደ አንደኛው ጓደኛ ቤት መሆኑን ቢናገሩም፣ ወዴት ሊወስዱት እንደነበር በግልጽ እንደማይታወቅ በመግለጽ የግድያ ወንጀል ድርጊቱ ኃላፊነት የእነሱ መሆኑ ውሳኔው ያብራራል፡፡

ሟች ከደከመ በኋላ ወደ ሆስፒታል መውሰዳቸው ወንጀሉን ሌላ ሰው እንደፈጸመ ለማስመሰልና ራሳቸውን ከተጠያቂነት ለማዳን መሆኑን ፍርድ ቤቱ ግንዛቤ በመውሰዱ፣ በወንጀል ሕግ 540 መሠረት በሙሉ ድምፅ ጥፋተኛ በማለት እያንዳንዳቸው በ10 ዓመት ፅኑ እሥራት እንዲቀጡ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

ተከሳሾቹ ይግባኝ ቢጠይቁም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሥር ፍርድ ቤትን ቅጣት አፅንቷል፡፡ ለሰበር አቤቱታ ቢያቀርቡም የሕግ ስህተት እንደሌለው በማስረዳት መዝገቡን መልሶት ነበር፡፡

ከላይ የተጠቀሰውን የክስ ሒደት መርምሮ የመጀመሪያውን የቅጣት ውሳኔ የሰጠው ፍርድ ቤትና የክልሉ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ግን፣ የሟች አማረ ገዳዮች ሌሎች ናቸው ተብሎ ክስ ሲመጣላቸው ተቀብለው አስተናግደዋል፡፡

የሟች አማረ ገዳዮች ተብለው እያንዳንዳቸው አሥር ዓመታት ተፈርዶባቸው ማረሚያ ቤት የገቡት ፍርደኞች፣ በእስር ላይ እያሉ፣ የከተማው ከፍተኛ መርማሪ ገዳዮች አብነት (ቀዬ) እና ተስፋ ፅዮን አበራ መሆናቸውን በመግለጽ አዲስ ክስ መመሥረቱን፣ መስከረም 14 ቀን 2005 ዓ.ም. ሌላ የቅጣት ውሳኔ መተላለፉን የሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለሁለተኛ ጊዜ የሰጠው ውሳኔ ያስረዳል፡፡

በሁለተኛው ክስ ወንጀለኛ ሆነው የቀረቡት አብነት (ቀዬ) እና ተስፋ ፅዮን በሌላ የወንጀል ድርጊት በማረሚያ ቤት እንደነበሩ የሚገልጸው ውሳኔው፣ አዲሶቹ ተከሳሾች ሟች አማረ ሙሉጌታን የገደሉት እነሱ መሆናቸውን፣ ነገር ግን በስህተት አፈወርቅና ውብሸት የሚባሉ ምስኪኖች መታሰራታቸውን ሲያወሩ ‹‹ሰማን›› ባሉ ታራሚዎች አማካይነት መከሰሳቸውን ውሳኔው ያብራራል፡፡

አዲሶቹ ተከሳሾች ድርጊቱን እንዳልፈጸሙ ክደው መከራከራቸውን፣ ነገር ግን ከሳሽ ባቀረበባቸው የማስረጃ ምስክሮች እንዳስመሰከረ ውሳኔው ይገልጻል፡፡ ፍርድ ቤቱም እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶ ተከላክለዋል፡፡

አብነት (ቀዬ) የሚባለው ተከሳሽ መከላከያ ምስክር እንደሌለው ገልጾ ራሱ በሰጠው ቃል፣ ድርጊቱ በተፈጸመበት ወቅት ሐዋሳ እንዳልነበር፣ ሟችንም ሆነ የተፈረደባቸውን እንደማያውቃቸው፣ ወደ ሐዋሳ የመጣው ለሥራ ተቀይሮ መሆኑንና ከሥራ ቦታ ተይዞ መቅረቡን ማስረዳቱን ውሳኔው ይገልጻል፡፡ ተስፋ ፅዮን የሚባለው ተከሳሽ በሌላ ወንጀል ተፈርዶበት በማረሚያ ቤት እያለ ወንዶ ኬሮ የተባለ ታራሚ ‹‹እፈልግሀለሁ›› ካለውና ካገኘው በኋላ ሁለት ልጆች አሥር ዓመት እንደተፈረደባቸውና ባልሠሩት ወንጀል መሆኑን እንዳስረዳው ገልጿል፡፡ በመቀጠልም ወንዶ ኬሮ የሚባለው ታራሚ፣ አብነት (ቀዬ) በሠራው ወንጀል በመታሰራቸው እሱ መግደሉን ትመሰክርና 15 ሺሕ ብር ይሰጥሃል እንዳለው፣ ከተፈቱ እንደሚጨምሩለት ሲነግረው፣ እንዳልተስማማ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱን ውሳኔው ይገልጻል፡፡ ሌሎቹም በመከላከያነት የቆጠራቸው ታራሚዎች ወንዶ ኬሮ የተባለው ታራሚ ሲገፋፋውና ገንዘቡ እንደሚከፈለው መስማታቸውን ማስመስከሩን ውሳኔው ገልጿል፡፡

ፍርድ ቤቱ ሁለቱም ፍርደኞች የከሳሽን ማስረጃ አለማስተባበላቸውን ገልጾ ጥፋተኛ በማለት፣ የግራ ቀኙን የቅጣት ማክበጃና ማቅለያ ካደመጠና ከሕጉ ጋር ካገናዘበና ከመረመረ በኋላ፣ ሁለቱም ተከሳሾች በዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ማስተላለፉን ሰነዱ ይገልጻል፡፡

ፍርድ ቤቱ በአንድ የወንጀል ድርጊት በሁለቱ ላይ የአሥር ዓመት ፅኑ እስራት ፈርዶ ሰበር ደርሶ ከፀደቀ በኋላ፣ በሁለቱ ላይ ደግሞ ከወር በፊት በዕድሜ ልክ ፅኑ የእስራት ቅጣት ውሳኔ በማስተላለፉ ‹‹ለምን ቀድሞ ምርመራውን አላጣራም? ዓቃቤ ሕግስ በተዘጋ ፋይል ላይ እንዴት ሌላ ክስ ሊመሠርት ቻለ?›› በሚል ውሳኔው እያነጋገረ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

 http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/8463-2012-11-10-12-55-03.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር