‹‹የዳኝነት ሥርዓቱ ራሱን ከመቆጠብ መውጣት ይኖርበታል››



አቶ ጌታሁን ካሣ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብት ማዕከል መምህር
አቶ ጌታሁን ካሣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብት ማዕከል መምህር ናቸው፡፡
የትግራይ ብሔራዊ ክልል የፍትሕ ቢሮ ኃላፊ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ እንዲሁም የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ አባል በመሆንም ለሁለት የሥራ ዘመኖች አገልግለዋል፡፡ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤትም በመምህርነት ሠርተዋል፡፡ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከእንግሊዝ ኩዊንስ ዩኒቨርሲቲ ያገኙ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብት ማዕከል በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የፒኤችዲ ምርምራቸውን በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሰለሞን ጎሹ በዳኝነት ነፃነትና በሕገ መንግሥታዊ ትርጉም ላይ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የፍትሕ አስተዳደር ውስጥ ዳኞች ምን ዓይነት ሚና ነው ያላቸው?

አቶ ጌታሁን
፡- ከ1948 ዓ.ም ጀምሮ ያሉትን ሕገ መንግሥቶች ወይም ከዚያ በፊት የነበሩትን ሁኔታዎች ስንመለከት የዳኝነት ተቋማት ሥራ በዋነኛነት በሚነሱ ጉዳዮች ላይ የሁለት ወገኖችን ክርክርና ማስረጃ በመመልከትና በማገናዘብ ውሳኔ መስጠት ነው፡፡ የመንግሥት አደረጃጀትን በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ በሥልጣን ክፍፍል መርህ ስናይ ግን በሦስት እንከፍላለን፡፡ ሕግ አውጪው፣ ሕግ ተርጓሚውና ሕግ አስፈጻሚው ይኖራሉ፡፡ በአገራችንም እነዚህ የመንግሥት አካላት አሉን፡፡ አንዱ በአንድ ወቅት ከነበረው የሚለይበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ የተለያዩ ገጽታዎችም አሏቸው፡፡ ለምሳሌ የተጻፈ ሕገ መንግሥት ከኖረን ጊዜ ጀምሮ ያለውን ብንመለከት የዳኝነትና የሕግ አስፈጻሚነት ሥልጣን በአንድ አካባቢ ተደራርቦ የምናገኝበት ሁኔታ ነበር፡፡ አሁን ባለው ሕገ መንግሥት ለመለያየት ተሞክሯል፡፡ ዋነኛው የዳኞች ሚና ሕግን በመተርጎም ውሳኔዎችን ማስተላለፍ ነው፡፡ ውሳኔዎቹ የሚተላለፉት ለሁለቱ ተከራካሪ ወገኖች ብቻ ሳይሆን በሕግ አውጪውና በሕግ አስፈጻሚው ሥልጣን ላይ ገደብ የሚያስቀምጡ መሆን አለባቸው፡፡

አንዱ የመንግሥት አካል ሌላኛውን ሊቆጣጠረው ይገባል፡፡ የመንግሥት የሥልጣን አጠቃቀም የተወሰነና የተገደበ መሆኑን ሊያረጋግጡ ይገባል፡፡ የፌዴራሉና የክልል ሕገ መንግሥቶች ማንኛውም በዳኝነት የሚታይ ጉዳይ ሁሉ የፍርድ ቤቶች ሥልጣን መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከተመሠረተባቸው መርሆዎች አንዱ የሕግ የበላይነት ነው፡፡ ለሁሉም ወገኖች እኩል ተፈጻሚነት ባለው ሕግ መመራትን ይጠይቃል፡፡ አከራክሮ መወሰን ብቻ ሳይሆን አንድ አሠራር የሚያመጣው ውጤት በሕግ የተመሠረተና የሚገዛ እንዲሆን አስተዋጽኦ ማበርከት ከዳኞች ይጠበቃል፡፡

ሪፖርተር፡- የዳኝነት ሥርዓቱ ከበርካታ አቅጣጫዎች ተግዳሮቶች እንዳሉት ይገለጻል፡፡ በዋነኛነት የሕገ መንግሥት ትርጉም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መሰጠቱና የሕገ መንግሥት ትርጉም የተፈጻሚነት ወሰን ላይ ግልጽ ገደቦች አለመኖራቸው የዳኝነት አካሉን ሥራ እየጎዳው ነው የሚል ቅሬታ ይቀርባል፡፡

አቶ ጌታሁን
፡- የሕግ የበላይነት አንዱ መገለጫ ሕገ መንግሥታዊነትን መወሰን ነው፡፡ ይኼ ሥልጣን የማን መሆን አለበት የሚለው በእኛ አገር ከ1948 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ አቋሞች አሉ፡፡ ለምሳሌ የኢሕዲሪ ሕገ መንግሥት ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን የመንግሥት ምክር ቤት እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ አሁን ሕገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ የሌሎች አገሮችን ልምድ ካየን በአጠቃላይ ሦስት ዋና ዋና ልምዶች ነው ያሉት፡፡ ሕገ መንግሥትን የመተርጎም ሥልጣን ትልቅ ዋጋ ይሰጠዋል፡፡ ምክንያቱም የአንድ ሥርዓትን የዴሞክራሲ ሒደት ለማጠናከርና መሠረት ያለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲኖር ለማድረግ ከምታደርጋቸው ጥረቶች አንዱ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች እንዴት ይዳኛሉ የሚለውን ጥያቄ በአጥጋቢ ሁኔታ መመለስ ሊሆን ይገባል፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ ይህ ሥልጣን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ነው፡፡ በሕግ አውጪው የወጣ ሕግ ወይም በሥራ አስፈጻሚው የተወሰደ ዕርምጃና ውሳኔ ሕገ መንግሥታዊነት ጥያቄ ከተነሳበት ሥልጣኑ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ነው፡፡ ወደ ሌሎች አገሮች ስንሄድ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ያላቸው አሉ፡፡ ከዚያም ካለፍን እንደኛ አገር የዳኝነት ተቋም ባልሆነ አካል ሕገ መንግሥታዊነት እንዲታይ የሚደረግበት ሁኔታ አለ፡፡ አገሮቹ የተለያዩ ልምዶችን የሚከተሉት ምክንያት የአገሮቹ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህልና ልምዶች የተለያዩ ስለሆነ ነው፡፡ የአንዱ ለሌላው የግድ አግባብነት ይኖረዋል ብለን መናገር አንችልም፡፡

በማንኛውም አገር ሥርዓት ውስጥ በብዙኀን ድምፅ የተመረጠ መንግሥትም እንኳን ቢሆን ሕገ መንግሥቱን መተርጎም በተመለከተ ሊነኩ የማይገባቸው መሠረታዊ መርሆዎች አሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱን መተርጎም ያለበት ነፃና ገለልተኛ የሆነ አካል ነው፡፡ በርካቹ ፍርድ ቤቶች ገለልተኛና የፖለቲካ አቋም የሌላቸው በመሆናቸው ሕገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን ሊሰጣቸው ይገባል ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ፍርድ ቤቶች ሕገ መንግሥትን የመተርጎም ሥልጣን ከተሰጣቸው የሕዝብ ውክልናና ምርጫ ባለው ተቋም የወጡ ሕጎችን ፍርድ ቤቶች ሕገ መንግሥታዊ አይደሉም የሚሉ ከሆነ ዴሞክራሲያዊ አይደለም በማለት ይከራከራሉ፡፡

ምክንያታቸው ደግሞ ዳኛ የተመረጠ፣ የሕዝብ ውክልና ያለውና በዴሞክራሲያዊ ሒደት የመጣ ስላልሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ያዛባል የሚል ነው፡፡ ዳኞች ሕገ መንግሥቱን ይተርጉሙ የሚሉት አካላት በብዙኀን ድምፅ የተመረጠው አካል የሁሉም ዜጎች ድምፅ የለውም የሚል ክርክር ያቀርባሉ፡፡ የአናሳዎችን መብት ለማስከበር ገለልተኛ የሆነውና የፖለቲካ ዓላማ የሌለው ፍርደ ቤት የተሻለ ነው በሚል ይሟገታሉ፡፡ በእኛ አገር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን ለመተርጎም ለምን ተመረጠ የሚለውን ጥያቄ ስናይ የተለያዩ ምክንያቶችን እናገኛለን፡፡ ሕገ መንግሥቱ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነት መገለጫ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ይኼንን ሕገ መንግሥት ደግሞ መተርጎም ያለበት ባለቤት የሆነው አካል ነው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ደግሞ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተወካይ ነው፡፡ በእርግጥ በሕገ መንግሥት ማርቀቅ ሒደት ወቅት በነበረው ውይይት ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ይኑር የሚል ሐሳብም ተነስቶ እንደነበር የሕገ መንግሥቱ ቃለ ጉባዔ ያሳያል፡፡

ሕገ መንግሥቱ በሕግ የበላይነት፣ በእኩልነትና የተዛቡ ግንኙነቶችን በማስተካከል መርህ ነው የተረቀቀው፡፡ እነዚህን መርሆዎች ተግባራዊ ማድረግ ነው ዋናው ነገር፡፡ የዳኝነት ነፃነትን በግልጽ ይደነግጋል፡፡ ይኼን መሬት ላይ የሚወርድ እውነታ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በአንድ ወገን የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፖለቲካ ዓላማ አለው፡፡ በአገሪቱም የአንድ ፓርቲ የበላይነት የሚታይበት የፖለቲካ ሥርዓት አለ፡፡ ስለዚህ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነፃ ሆኖ የራሱ ተቋማት የሆኑትን ሕግ አስፈጻሚ ሕግ አውጪውን አካል ውሳኔዎችን ተመልሶ ሕገ መንግሥታዊ አይደሉም ለማለት አቅም የለውም የሚል መከራከሪያ ይቀርባል፡፡ ይኼ ሁኔታ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን ዓላማዎች በሚገባ ተግባራዊ እንዳይሆኑ እንደሚያስቸግርና የአናሳዎች ድምፅ እንዳይሰማ ያደርጋል የሚል ቅሬታም የሚያቀርቡ አሉ፡፡ በሌላ ወገን የፌዴሬሽን ምክር ቤት የብሔር ብሔረሰቦች ተወካይና የሉዓላዊነታቸው መገለጫ በመሆኑ ሕገ መንግሥቱን መተርጎሙ ትክክል ነው በማለት የሚቀርብ ክርክር አለ፡፡

እነዚህ ሁለት ወገኖች ባለፉት 18 ዓመታት ያለማቋረጥ ተከራክረዋል፡፡ ነገር ግን ሊያነጋግር የሚገባው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሥልጣን ገደብ ነው፡፡ በሕግ አውጪው የሚወጡ ሕጎችን ብቻ ነው የሚመለከተው? ወይስ የሕግ አስፈጻሚው ውሳኔዎችንም ይመለከታል? የሚለው ላይ ሕገ መንግሥቱ የግልጽነት ጉድለት አለው፡፡ እዚህ ላይ ሁለት ዓይነት አስተሳሰብ አለ፡፡ በአንድ በኩል የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕግ አውጪውንም ሆነ የሕግ አስፈጻሚውን ውሳኔዎች ማየት ይችላል የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥታዊነትን ነው የሚመለከተው እንጂ መተርጎምንና ተግባራዊ ማድረግን ጠቅልሎ የመውሰድ ሥልጣን አልተሰጠውም የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ሥልጣን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ለምን ተሰጠ ከሚለው በተጨማሪ፣ የምክር ቤቱ አባላት የክልል ምክር ቤት አባል መሆናቸውና በተቋሙ አደረጃጀትና የሥራ ጊዜያት ላይ ብዙ ቅሬታዎች ይሰማሉ፡፡

አቶ ጌታሁን
፡- በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ትርጉም የሚሰጠው ዳኝነት በሌለው ተቋም ነው፡፡ ይኼ ከሌሎች አገሮች የተለየ ነው፡፡ የተለየ መሆኑ በራሱ ችግር አይደለም፡፡ ተቋሙ ምን ያህል ገለልተኛ በመሆን የሕግ አስፈጻሚውንና የሕግ አውጪውን የሥልጣን ገደብ ማስቀመጥ ይችላል የሚለው ነው ትልቅ ተግዳሮት የሚሆነው፡፡ ከተቋማዊ ብቃት አንፃር የሚነሱት ቅሬታዎች አስተዳደራዊ ዕርምጃዎችን በመውሰድ የሚስተካከሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከጽንሰ ሐሳብ አንፃር የሥልጣን ገደብ ለማድረግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይችላል ወይ የሚለው ጥያቄ ወሳኝ ነው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደ ዳኝነት አካሉ ገለልተኛ መሆን አይችልም የሚል ጥያቄ አለ፡፡ ገደብ ማድረግ የማይችል ከሆነ ሕግ አውጪውና ሕግ አስፈጻሚው የሚፈልጉትን  መሥራት ይችላሉ፡፡ የሕግ የበላይነት (Rule of Law) ማስፈን ይቀርና በሕግ መግዛት (Rule  by Law) ይጀመራል ማለት ነው፡፡

አንዳንድ አገሮች የሕግ ረቂቅ ለሚቀርበው አካል ያቀረቡት ረቂቅ ከሕገ መንግሥቱና ከሰብዓዊ መብቶች መርሆዎች ጋር የሚስማማ ስለመሆኑ (Compatibility Statement) እንዲያቀርቡ ያስገድዳሉ፡፡ ይኼ ተግባር በእኛ አገር ስለመኖሩ አላውቅም፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የአመራረጥና የአወካከል ሥርዓቱንም ስንመለከተው ሕገ መንግሥቱ የመሠረተውን የሥልጣን ክፍፍልና መለያየት መርህ ሊጣረስ ይችላል የሚል አስተያየት አለ፡፡ ይኼ በአግባቡ መታየት አለበት፡፡ በተጨማሪም የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በዓመት ስንት ጊዜ ይሰበሰባል? እስካሁን ለምን ያህል ጉዳዮች ውሳኔ ሰጥቷል? ውሳኔ የሚሰጥበት ሥነ ሥርዓት ምን ይመስላል? የሚለውን ካነሳን አሁንም መመለስ ያለባቸው በርካታ ነገሮች መኖራቸውን ያሳያል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከ18 ዓመታት በፊት ሕገ መንግሥቱን በዳኞች መተርጎሙ ካልተመረጠባቸው ምክንያቶች አንዱ ገዥው ፓርቲ በዳኞች አቅምና የፖለቲካ ገለልተኛነት ላይ የነበረው አለመተማመን ይገኝበታል፡፡ ከእነዚህ ዓመታት በኋላ አሁንም ዳኞች ስላለባቸው ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎች እየተነገረ ነው፡፡

አቶ ጌታሁን
፡- ነፃና ጠንካራ የዳኝነት አካል ከሌለ የሕገ መንግሥቱ ዋነኛ መርህ የሆነው የሕግ የበላይነት ትርጉም አይኖረወም፡፡ የዳኝነት ነፃነትና ዳኞች በሕግ ብቻ ተመሥርተው እንዲሠሩ ሕገ መንግሥታዊ ማረጋገጫ አለ፡፡ የዳኝነት አስተዳደሩም በሥራ አስፈጻሚው ወይም በሌላ አካል ሳይሆን ዳኞች በብዛት በሚወከሉበት የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ እነዚህ መሠረቶች ተጥለዋል፡፡ ሆኖም ከዚያ በኋላ ከወጡ ዝርዝር ሕጎችና ከተግባር ጋር ሁኔታውን መመልከት ይኖርብናል፡፡ የዳኝነት ነፃነት ሁለት ገጽታዎች አሉት፡፡ እነዚህም ተቋማዊና ግለሰባዊ ነፃነት ናቸው፡፡ ተቋማዊ ነፃነት ከሕግ አውጪው፣ ከሕግ አስፈጻሚውና ከሌላ ወገን ተፅዕኖ ውጪ መሆንን፣ አስተዳደራዊ ነፃነት መጎናጸፍንና የፋይናንስ ነፃነትን ይጨምራል፡፡

የአቅም ግንባታ ሚኒስጼር በ1997 ዓ.ም. ባስጠናው ጥናት፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የካናዳው ሲዳ ባስጠኑት ጥናት፣ በዓለም ባንክ ጥናትና በሌሎችም በርካታ ጥናቶች ስንመለከት የዳኝነት ነፃነትና ብቃት ላይ አሁንም መሠራት ያለባቸው በርካታ ነገሮች መኖራቸውን ይጠቁማሉ፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ዳኞችን ሲያናግሩ ያነሷቸው በርካታ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ፍርድ ቤቶች ከመንግሥት ተገቢውን ትኩረት አላገኙም የሚል ነበር፡፡ በዳኞች አሿሿም ላይም ችግር መኖሩ ተጠቁሟል፡፡ እርግጥ ከዚያ በኋላ የዳኞችን አሿሿም በማስተካከል ረገድ መንግሥት አንዳንድ ነገሮችን አድርጓል፡፡ ለምሳሌ የሥልጠና ማዕከሎችን ከፍቷል፡፡ የሕግ ትምህርት ቤቶች ተስፋፍተዋል፡፡ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ ደግሞ ከዳኞች አስተዳደር ውጪ ያሉ አካላትን ተሳትፎ የማረጋገጥ ጥረቶች አሉ፡፡ እነዚህ የራሳቸው አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ይሁንና እየወጡ ባሉ ሕጎች በአስተዳደራዊ ችሎቶች የዳኝነትን ሥልጣንን የመቀነስና የመጋፋት ነገር ታይቷል የሚል ሐሳብ አለ፡፡ የዳኝነት ተቋሙ ራሱ በውስጣዊ ምክንያቶቹ ሥልጣኑን አሳልፎ ሰጥቷል የሚልም አስተያየት አለ፡፡ ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሚና ስለሌለው የዳኝነት አካሉ ተፈጥሯዊ የሆነውን የሕግ አውጭውንና የሕግ አስፈጻሚውን ሥልጣን የመገደብ ሚናውን አልተወጣም የሚል ክርክርም ይነሳል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቅራቢነት ፓርላማው የአዳዲስ ዳኞችን ሹመት አፅድቋል፡፡ ከ18 ዓመታት በፊት ይነሳ የነበረው የዳኞች ወጣት መሆን፣ ከፖለቲካ ሥርዓቱ ጋር ያላቸው ቁርኝትና የዜጎች ንቁ ተሳትፎ በዕጩዎች መረጣ ላይ አለመኖር ግን አሁንም እየተነሳ ነው፡፡

አቶ ጌታሁን
፡- የዳኞች አመራረጥና ግልጽነት ላይ ያለው ጥያቄ ይታወቃል፡፡ ጥናቶቹም ይኼንን ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች በዝምታ ሊታለፉ አይገባም፡፡ የዳኝነት ተቋም በሕዝብ ዓይን በሁለት ነገሮች ነው የሚመዘነው፡፡ አንደኛው እይታ ነው፡፡ ሁለተኛው ተጨባጩ እውነታ ነው፡፡ በእይታም እንኳን ቢሆን የሕዝብ አመኔታን የማያተርፍ የዳኝነት ተቋም ከሆነ የምንገነባው ጉዳት አለው፡፡ እውነት ነው አይደለም የሚለውን በማስረጃ ማረጋገጥ አልችልም፡፡ የመንግሥት አካል የሆነው የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር ያስጠናው ጥናት ራሱ ይህን ጥያቄ ያነሳል፡፡ ሌሎችም ጥናቶችና የግለሰብ አስተያየቶች ይህንኑ ይደግማሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች መሠረት አልባ ናቸው ማለት ያስቸግራል፡፡ ልክ ናቸው ለማለት ደግሞ ማስረጃ የለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት ዓመታት በኦሮሚያና በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት በሙስና ምክንያት የተነሱትን በመቶዎች የሚቆጠሩ ዳኞች ጨምሮ፣ በተለያዩ ቦታዎችና ጊዜያት ዳኞች በጅምላ መነሳታቸው ዳኞች ካላቸው የዕድሜ ልክ የሥራ አገልግሎት ጥበቃ ጋር እንዴት ይታያል? ይህስ መጀመርያም ጥያቄ ከሚነሳበት የአመራረጥና የአሿሿም ችግር ጋር አይገናኝም ወይ?

አቶ ጌታሁን
፡- የዳኝነት ነፃነት ከተጠያቂነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ነፃ የሆነ ዳኛ በሥራ ላይ ደግሞ የሚጠየቅ ነው፡፡ ዳኞች ከሥራ የተነሱት በሚያስጠይቃቸው ነገር ከሆነ ትክክል ነው፡፡ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔዎች አንዱ ሥራቸው ይህ ነው፡፡ ለዳኞች ነፃነት የተሰጠው የፍትሕ ሥራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ስለሆነ አጥፍተው ሲገኙ የሚጠየቁበት አግባብ ሊኖር ይገባል፡፡ ነገር ግን ይህ የተጠያቂነት ሥርዓት ዳኞችን ለማስጠንቀቅ ወይም የሰጡትን ውሳኔ መሠረት የሚያደርግ ከሆነ አደገኛ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የዜጎችንም እይታ በጣም ስለሚጎዳ፡፡ ዳኞቹ የተባረሩት ባለባቸው የሥነ ምግባር ችግርና የብቃት ማነስ ከሆነ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ዳኞች የተባረሩት ሌሎች ሰዎችን ስላላስደሰቱ ነው በሚል ከሆነ ይህ ሥርዓቱን በአጠቃላይ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚያስገባ ነው የሚሆነው፡፡

ሪፖርተር፡- በየጊዜው እየተቋቋሙ ያሉ አስተዳደራዊ ችሎቶች የዳኝነቱን ሥልጣን እየሸረሸሩት ነው የሚል ቅሬታ ይቀርባል፡፡ በተጨማሪም አንዳንድ ሕጎች ለዳኞች ይግባኝ የማየትና ውሳኔዎችን የመከለስ ሥልጣን ይከለክላሉ፡፡

አቶ ጌታሁን
፡- ለአስተዳደራዊ ችሎቶች የዳኝነት ሥልጣን መስጠት የቅርብ ጊዜ ልምድ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያም ብቻ ልምድ አይደለም፡፡ የበርካታ አገሮች ልምድ ነው፡፡ ዋነኛው መታየት ያለበት ጥያቄ ዓላማው ለምንድን ነው? የሚለው ነው፡፡ ዓላማው የዳኝነትን ሥልጣን ለመቀነስ ከሆነ በሌላ በር ዞሮ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌውን መወሰድ ይሆናል፡፡ በእኛ አገር ለምሳሌ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች ጉዳይ በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ውስጥ በሚቋቋም ችሎት ድሮም ይታይ ነበር፡፡ ነገር ግን ይግባኝ ወደ ፍርድ ቤት ማለት ይቻላል፡፡ አስተዳደራዊ ችሎቶች አስፈላጊ ናቸው፡፡ አንደኛ ሁሉም ጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤት ቀርበው ሊታዩ አይገባም፡፡ ዳኞች የቴክኒክ ጉዳዮች ዕውቀት ላይኖራቸው ስለሚችል በባለሙያ ቢታዩ ጥቅም አለው፡፡ ሆኖም ይህ ለአስተዳደራዊ አካላት የተሰጠ የዳኝነት ሥልጣን ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ ሊፈጸም የሚገባው ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት ሰንሰለት በመዘርጋት ነው፡፡ አሁን አንዳንድ ሕጎች የአስተዳደራዊ ችሎቶች ውሳኔ በፍርድ ቤት አይታይም የሚል አንቀጽ እየያዙ ነው፡፡

ለምሳሌ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር አዋጅ፣ የሊዝ አዋጅ፣ የጉምሩክ ሠራተኞች አስተዳደር ደንብ የመሳሰሉ አዋጆች ላይ የሚቀርበው የዳኝነት ሥልጣኑን የመቀነስ አዝማሚያ አላቸው የሚለው ቅሬታ ምክንያታዊ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱን የሥልጣን ክፍፍል መርህ የሚቃረን ነው፡፡ የሊዝ አዋጅ የከተማ ቦታ ማስለቀቅ ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቋቁሟል፡፡ ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ መመልከት የሚችለው ግን የገንዘብ መጠኑን ብቻ መሆኑን ሕጉ ይገልጻል፡፡ አላግባብ ነው የተነጠቅኩት የሚል ሰው የት ቦታ ይደመጣል? የመንግሥት ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ግዴታውን ያልተወጣ ተከራይ አስወጥቻለሁ ይላል፡፡ ግዴታዬን ተወጥቻለሁ፤ ያልተወጣሁት ግዴታ የለም ቢል የት ነው የሚሄደው? በሙስና ተጠርጥሮ የተሰናበት ሠራተኛ በፍርድ ቤትም ቢሆን ጉዳዩ ሊታይ አይችልም ካልን ሙስናን መዋጋት በአማራጭነት ሊቀመጥ የሚችል ጉዳይ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ለአስተዳደራዊ አካላት የዳኝነት ሥልጣን የመስጠት ግንዛቤ እንደገና ደግሞ ማየት ያስፈልጋል የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት የዳኝነት ሥልጠና ማዕከል በዳኝነት አገልግሎት ላይ ለውጥ ማምጣቱን እየገለጸ ነው፡፡ ይሁንና አንዳንድ ሠልጣኞች ሥልጠናው በሕግ ትምህርት ቤት የተሰጡትን ትምህርቶች ከፖለቲካ ሥርዓቱ ጋር የማዋሀድ ሥራ የሚሠራበት ተደጋጋሚ ሒደት ነው በሚል ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡

አቶ ጌታሁን
፡- የሥልጠና ተቋማቱ ጠቃሚ ናቸው፡፡ ይዘቱና የአሰጣጥ ሒደቱን መገምገም ከጀመርክ የእኛም ትምህርት እንደዚያው መታየት አለበት፡፡ ምን ያህል አስፈላጊ ነው? ድግግሞሽ የለበትም ወይ? በየጊዜው ከሚታዩት ሁኔታዎችና ለውጦች ጋር አብሮ የሚሄድ ነው ወይ? የሚለውን ጥያቄ ካነሳን ለሁሉም ይሠራል፡፡ ይሁንና የዳኝነት ማሠልጠኛ ተቋማት የሚሰጡት ትምህርት በየጊዜው እየተፈተሸና እየተሻሻለ ሊሰጥ ይገባዋል፡፡ ተቋማቱ ለጠንካራና ነፃ የዳኝነት አካላት ግንባታ አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የተጠቃለለ የማስረጃ ሕግ አለመኖሩና የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ አለመሻሻል ዳኞች ከሌሎች የፍትሕ አካላት ጋር ያላቸውን ግንኙነት እየጎዳው ነው በሚል የሚተቹ አሉ፡፡

አቶ ጌታሁን
፡- የተሟላ ሕግ ያስፈልጋል፡፡ ብቃት ያለው ዳኛ፣ ነፃ ፍርድ ቤትና አመኔታ ያለው የፍትሕ ሥርዓት ለመገንባት አስፈላጊ ነው፡፡ የማስረጃ ሕጉም ሆነ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ ተሟልቶ ተግባር ላይ ቢውል የፍትሕ ሥርዓቱን የተሟላ ያደርገዋል፡፡ የሕጎቹ አለመሟላት የፈጠረው ተፅዕኖ ምን እንደሆነ ግን ከጉዳይ ጉዳይ ስለሚለያይ ማጠቃለያ መስጠት ይከብደኛል፡፡ ሕጎቹ በረቂቅነት ደረጃ ረጅም ጊዜ እንደሆናቸው ግን አውቃለሁ፡፡ የተሻለ ትኩረትም ማግኘት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ዳኞች ሲባረሩ በሙስና ምክንያት መባረራቸው ነው የሚጠቀሰው፡፡ የዳኞች ደመወዝ፣ ጥቅማ ጥቅምና የተመቻቸ የሥራ አካባቢ አለመፈጠሩ ለአገልግሎቱ መዳከም ምን ያህል ምክንያት ይሆናል?

አቶ ጌታሁን
፡- ዳኞቹ በምን ምክንያት እንደተገለሉ የእያንዳንዱን ዳኛ ጉዳይ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ዳኞቹ በሚያቀርቧቸው ሪፖርቶችና ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ሲወያዩ በርካታ ነገሮች እንዳልተሟሉላቸው ገልጸዋል፡፡ ደመወዝ፣ የሥራ ቦታ ምቹነት፣ ወዘተ ተጠቅሰዋል፡፡ እነዚህን አለማሟላት በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡

ሪፖርተር፡- በምዕራብ አገሮች ያለውን የዳበረ የዳኞችና የሕግ ምሁራንን በጎ ግንኙነት ትተን በአፍሪካ ደረጃ እንኳ እንደ ደቡብ አፍሪካና ጋና ያሉ አገሮች ውስጥ የሕግ ምሁራኑ ሥራዎች በዳኞች ውሳኔ ላይ ተፅዕኖ ሲያደርጉ ይታያል፡፡ በኢትዮጵያ ግን ይህ አይታይም፡፡

አቶ ጌታሁን
፡-  የሕግ ትምህርት አጠቃላይ የፍትሕ ሥርዓቱን አጋዥ በሆነ  መልኩ እንዲሰጥ በሚል በአቅም ግንባታ ሚኒስቴር የተጀመረ የማሻሻያ ፕሮግራም እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ የሕግ ትምህርት ለፍትሕ ሥርዓቱ በምርምር፣ በጥናትና የሐሳብ አመንጪ በመሆን ሊያግዝ ይገባል፡፡ አሁን እንደዚያ ዓይነት ተፅዕኖ የለውም ማለት አይቻልም፡፡ ዳኞቹ እኮ ከሕግ ትምህርት ቤቶች ነው የሚወጡት፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ሁኔታዎች ላይ አስተያየትን ያለማድመጥ ወይም የመቀየም ልምድ አለ፡፡ በዚህ ምክንያት በቂ አስተዋጽኦ አላደረጉ ይሆናል፡፡ ትችትን የለውጥና የዕድገት መነሻ አድርጎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በተሰጡ ውሳኔዎች ላይ ትችቶች ቢቀርቡና የጎደሉ ነገሮች ቢነገሩ አጠቃላይ ሥርዓቱን ለማሳደግ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አዋጅ ቁጥር 250 እና 251 የዳኝነት አካሉን ተፈጥሯዊ ሥልጣን ሁሉ ወስደዋል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ አይደሉም በሚል ቅሬታ የሚያቀርቡ ምሁራን አሉ፡፡

አቶ ጌታሁን
፡- የፌዴሬሽን ምክር ቤቱንና የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔውን ሥልጣን የሚወስኑ አዋጆች በሕግ አውጪው የሚወጡ ሕጎችን ሕገ መንግሥታዊነትን የመወሰን ሥልጣን የፌዴሬሽን ምክር ቤት መሆኑን ያሳያሉ፡፡ ነገር ግን ከዚያ ውጪ ያሉ በሕግ አስፈጻሚው የሚሰጡ ውሳኔዎችን ሕገ መንግሥታዊነት የመወሰን ሥልጣን ግን በእነዚህ አዋጆች ተወስዶባቸዋል ከማለት ይልቅ፣ ፍርድ ቤቶቹ ራሳቸው ሥልጣን የለንም ብለው ማሰባቸው ነው ከባድ ችግር፡፡ በሁለቱ አዋጆች ላይ የሚነሳው ጥያቄ ተገቢ ቢሆንም የዳኞቹ አመለካከት ይበልጥ ያሳስባል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዳኝነት ነፃነቱና ከሕገ መንግሥት አተረጓጎም ጋር በተገናኘ ከሕጉ የሚመነጨውን ችግር ለመቅረፍ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ የሚጠይቁ በርካታ ምሁራን አሉ፡፡ ሆኖም ገዥው ፓርቲ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያን በበጎ ጎኑ አያየውም፡፡

አቶ ጌታሁን
፡- ሕገ መንግሥት አንዱ መገለጫ ባህሪው ቋሚነት ነው፡፡ በየጊዜው በጥቃቅን ነገሮች ሁሉ ሕገ መንግሥትን ማሻሻል ብዙ ቦታ የሚደገፍ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥትን ማሻሻል እንደ መደበኛ ሕጎች ማሻሻል መታየት የለበትም፡፡ ይህ የሕገ መንግሥቱን ዘላቂ ሰነድነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባል፡፡ ነገር ግን የሕገ መንግሥቱን ዋነኛ መርሆዎች ለማሳካት ችግር የሆነን ነገር ማሻሻል ያስፈልጋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ የአንድ ፓርቲ ሰነድ ሳይሆን የሕዝብ ሰነድ ነው፡፡ የሕገ መንግሥት ትርጉምን በተመለከተ በድጋሚ ማየቱ አይከፋም ብዬ አስባለሁ፡፡

በሕዝብ ውይይትና ተሳትፎ እንደመጣ ሰነድ ለሕገ መንግሥቱ ያለውን ክብር ለመቀነስ ሳይሆን ሊያሳካ ያላቸውን ዓላማዎች እንዲያሳካ ከተፈለገ፣ በሕግ አስፈጻሚውና በሕግ አውጪው ላይ ገደብ መጣል የሚችል አካል ለማዋቀር እንደገና ማየት ያስፈልጋል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ሆኖም የእኛ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሥርዓት በጣም ከባድ ነው፡፡ ቢሆንም ሐሳቡን ማንሳቱ ችግር አለበት ብዬ አላስብም፡፡ ምርጫችን እስካሁን ምን ዓይነት ውጤት አስገኝቷል ብለን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ከሕገ መንግሥት ማሻሻያ ውጪ ያሉትን መፍትሔዎችም አብሮ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ የዳኝነት ሥርዓቱ ራሱን ከመቆጠብ መውጣት ይኖርበታል፡፡ ሕጎቹም በድጋሚ ሊታዩና የሕገ መንግሥቱን የሥልጣን ክፍፍል መርህ እንዳይቃረኑ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ 
http://www.ethiopianreporter.com/interview/297-interview/8342-2012-11-03-10-09-12.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር