ሲዳማ ቡና ቅጣት ተላለፈበት


•ፕሪሚየር ሊጉ ነገና ከነገ በስቲያ ቀጥሎ ይካሄዳል

ሲዳማ ቡና እየተካሄደ በሚገኘው የ2005ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መለስ ዋንጫ ውድድር በአራተኛው ሣምንት ሲዳማ ቡና በሜዳው ይርጋለም ላይ አርባ ምንጭ ከነማን ባስተናገደበት ጨዋታ በተፈጠረው የዲሲፕሊን ጥሰት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቅጣት ተላልፎበታል።
ፌዴሬሽኑ ያደረሰን ዘገባ እንደሚያመለክተው ውድድሩን የሚመራው የሊግ ኮሚቴ ከዲሲፕሊን ኮሚቴ የደረሰውን ሪፖርት ከገመገመ በኋላ ሲዳማ ቡና በስድስተኛ ሣምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ነገ በሜዳው ከሃዋሳ ጋር ሊያደርግ የነበረውን ጨዋታ በሌላ ገለልተኛ ሜዳ እንዲያካሂድ ወስኖበታል።
ይህንንም ተከትሎ ሁለቱ ቡድኖች ይርጋለም ላይ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ የቦታና ሰዓት ለውጥ ተደርጎበት በአሰላ ስታዲየም ከቀኑ በስምንት ሰዓት የሚካሄድ ይሆናል። ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ የሆኑ ተግባራት የተመልካቾች ማነስ እያሳሰበው ለሚገኘው የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መለስ ዋንጫን የበለጠ የሚያደበዝዙት በመሆኑ ክለቦች ደጋፊዎቻቸውንም ሆነ ተጫዋቾቻቸውን ለስፖርታዊ ጨዋነት መርሆዎች ተገዢ እንዲሆኑ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
የስድስተኛው ሣምንት የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ነገና ከነገ በስቲያ ቀጥሎ የሚካሄድ ሲሆን፤ ሰባት ጨዋታዎችም ይከናወናሉ። አምስቱ ጨዋታዎች ነገ በአበበ ቢቂላና በክልል ከተሞች የሚደረጉ ሲሆን፤ ሁለቱ ደግሞ ሐሙስ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይደረጋሉ።
በእዚሁ መሠረት ነገ ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል ኢትዮጵያ ቡና ከመከላከያ የሚያደርጉት ጨዋታ ትልቅ ትኩረት ስቧል። ሁለቱ ክለቦች በደረጃ ሠንጠረዡ በአንድ ነጥብ ተበላልጠው ስምንተኛና ዘጠንኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ መከላከያ በሰባት ነጥብ ስምንተኛ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና በስድስት ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ባለ ሜዳው ኢትዮጵያ ቡና ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ የሚችል ከሆነ ደረጃውን ሲያሻሽል፤ መከላከያ ከረታ ደግሞ ያለበትን ደረጃ አስጠብቆ ለመዝለቅ የሚችልበትን ዕድል ያሰፋል። በወጣው መርሐ ግብር መሠረት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ነገ በ12 ሰዓት የሚከናወን ይሆናል።
በሌሎች ጨዋታዎች መብራት ኃይል በደረጃ ሠንጠረዡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ሐረር ቢራን ያስተናግዳል። መብራት ኃይል እስካሁን ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ስምንት ነጥቦችን ሰብስቦ አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን፤ ጥሩ አጀማመር እያሳየ ያለው ሐረር ቢራ በተመሳሳይ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች 11 ነጥቦችን በማግኘት ነው ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው። የመብራት ኃይልና ሐረር ቢራ ጨዋታ ነገ በ10 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይደረጋል።
ሌላው አዲስ አበባ ላይ በሚደረገው ጨዋታ የዘንድሮው የፕሪሚየር ሊግ እንግዳ ቡድን ኢትዮጵያ ውሃ ሥራዎች አዳማ ከነማን ነገ በስምንት ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ያስተናግዳል። በደረጃ ሠንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ክለቦች የሚያደርጉት ይህ ጨዋታ በመጨረሻው የወራጅ ቀጣና ላይ የደረጃ ለውጥ ሊያስከትል ይችላል። 
በአንድ ነጥብ የመጨረሻውን ደረጃ ይዞ የሚገኘው ኢትዮጵያ ውሃ ሥራዎች ቡድን የሚረታ ከሆነ ከመጨረሻው ደረጃ ከፍ በማለት የአዳማ ከነማን 12ኛ ደረጃን የሚረከብ ሲሆን፤ አዳማ ከነማም የማሸነፍ ዕድሉን ካገኘ ደረጃውን ከፍ የማድረግ ዕድሉን ያሰፋል።
በተመሳሳይ በአሰላ ስታዲየም የቅጣት ሰለባው ሲዳማ ቡናና ሃዋሳ ከነማ ከሚያደርጉት ጨዋታ በመቀጠል በ10 ሰዓት ሙገር ሲሚንቶ ኢትዮጵያ መድንን ያስተናግዳል። በአምስተኛው ሣምንት አበበ ቢቂላ ላይ በመከላከያ የተሸነፈው ሙገር አንድ ነጥብ ብቻ ይዞ በአስራ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ በሰባት ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ነው ወደ አሰላ ተጉዞ ሙገርን የሚገጥመው።
ይኸው የስድስተኛ ሣምንት ጨዋታ ከነገ በስቲያ ሲቀጥል 10 ሰዓት ላይ የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ አርባ ምንጭ ከነማን ሲያስተናግድ፤ በ12 ሰዓት ደግሞ ደደቢትና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይገናኛሉ። 
በባለፈው ሣምንት ጨዋታ ደደቢትን ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት በመርታት የደረጃ ሠንጠረዡን መሪነት የተረከበው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጠንካራው የደቡብ ክልል ክለብ አርባ ምንጭ ከነማ ቀላል የማይባል ፈተና ይጠብቀዋል ተብሎ እየተገመተ ይገኛል። አርባ ምንጭ ከነማ እስካሁን ባደረጋቸው የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች ስምንት ነጥቦችን በማግኘት ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ከሐረር ቢራ ጋር በዕኩል 11 ነጥቦች በግብ ክፍያ በልጦ ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኘው አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ ይህንን ጨዋታ መርታት ከቻለ መሪነቱን በአስተማማኝ ሁኔታ ማጠናከር ይችላል። 
ከቅዱስ ጊዮርጊስና አርባ ምንጭ ከነማ ጨዋታ በመቀጠል ደደቢት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የሚያስተናግድበት ጨዋታ በ12 ሰዓት ይከናወናል። በ10 ነጥቦች ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ደደቢት እና በአራት ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዘንድሮ በአዳዲስ አሠልጣኞች እየተመሩ ውድድራቸውን በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ደደቢት በቅርቡ ባስፈረማቸው አሠልጣኝ አብርሃም ተክለሃይማኖት የሚመራ ሲሆን፤ ንግድ ባንክ በበኩሉ፤ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና አሠልጣኝ በነበሩት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ነው የሚመራው። የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 12 ላይ ይካሄዳል። 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር