ብሄራዊ የስነ- ህዝብ ምክር ቤት ሊቋቋም ነው
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 17፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) በያዝነው ዓመት የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር 84 ነጥብ 3 ሚሊዮን ገደማ መድረሱን ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ያደረገው ሳይንሳዊ ግምት ያመለክታል።
የሃገሪቱ ፖሊሲ የህዝብ ቁጥርን መቀነስ ላይ ከማተኮር ይልቅ ፥ ያለውን የህዝብ ቁጥር ከሃገሪቱ የልማት አቅምና የኢኮኖሚ ክፍፍል ጋር ማጣጣም ላይ አተኩሮ የሚሰራ ነው።
ኢትዮጵያም የህዝብ ቁጥሩን ዕድገት ከኢኮኖሚ ዕድገቷ ጋር ለማመጣጠን እንዲያስችላት ፥ ከዛሬ 18 ዓመት በፊት የስነ-ህዝብ ፖሊሲ ቀርጻ ወደ ትግበራ ብትገባም ፥ እስካሁን ተግባራዊ አልተደረገም።
ይህንኑ የስነ-ህዝብ ጉዳይ የሚያስተባብረውን የብሄራዊ ስነ-ህዝብ ምክር ቤት ለማማቋም ፥ ባለፈው አመት ረቂቅ ደንብ በማዘጋጀት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን ፤ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ተጠባባቂ የስነ-ህዝብ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ መኮንን ናና ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳሉት የሚቋቋመው ምክር ቤት ይበልጥ ውጤታማ ይሆን ዘንድ ፥ እንደገና ሰፋ ያለ ጥናት ተደርጎበት ፤ በዚህ አመት መጨረሻ ወይም በሚቀጥለው አመት መጀመሪያ ላይ ፥ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ይቀርባል።
ረቂቁ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ አስኪጸድቅ ድረስም ፥ የማስተባበሩን ሒደት ለማከናወን ሃገር አቀፍ ግብረ ሃይል በያዝነው ወር ውስጥ በማቋቋም ፥ ምክር ቤቱ እስኪመሰረት ግብረ ሃይሉ የማስተባበሩን ስራ እያከናወነ ይቆያል ብለዋል አቶ መኮንን።
ሃገሪቱ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ብታስመዘግብም ፥ ካላት የህዝብ ብዛት ጋር መመጣጠን ባለመቻሉ አጠቃላይ የምርት መጠኗ 412 አሜሪካን ዶላር ላይ እንዲወሰን አስገድዷታል።
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ ፥ በሃገሪቱ 100 ሰራተኞች ቢኖሩ በስራቸው የእነርሱን እጅ ጠባቂ 94 ሰዎች መኖራቸውን ባህሩ ይድነቃቸው ዘግቧል።
Comments
Post a Comment