የመጀመርያው የቡና ሙዚየም በመጠናቀቅ ላይ ነው



በዮናስ አብይ
በኢትዮጵያ የመጀመርያው ነው የተባለለትና ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ በደቡብ ክልል በቦንጋ ከተማ በመገንባት ላይ የሚገኘው ብሔራዊ የቡና ሙዚየም በቅርቡ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የቦንጋ ዞን አስተዳደር አስታወቀ፡፡
ለ2000 ዓ.ም. የሚሊኒየም በዓል ተቋቁሞ የነበረው የበዓሉ አስተባባሪ ሴክሬተሪያት ሥራው ከመጠናቀቁ በፊት ካሳለፋቸው ውሳኔዎች አንዱ፣ የቡናን ባህላዊና ታሪካዊ አመጣጥ የሚያሳይ ሙዚየም ስለመገንባት ነበር፡፡

ምንም እንኳ የሙዚየሙ ግንባታ ከዕቅዱ ቢዘገይም በጥቂት ወራት ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚጀምር የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ክፍሌ ገብረ ማርያም በተለይ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እንደ አስተዳዳሪው ገለጻ፣ የሚሊኒየም አካባበር አስተባባሪ ኮሚቴው በወቅቱ ኃላፊነቱን ለደቡብ ክልል የሰጠ ቢሆንም፣ ክልሉ ደግሞ ግንባታውን የማስተባበርና የመከታተል ኃላፊነቱን ለዞኑ አስተዳደር ሰጥቷል፡፡

ሙዚየሙ ብሔራዊ እንዲሆን በመወሰኑ በጀቱን የፌዴራል መንግሥት እንዲመድብ በቅድሚያ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ ግን ክልሉና ዞኑ እንዲሸፍኑ መደረጉን አክለው ገልጸዋል፡፡

ግንባታው ለምን እንደዘገየ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ክፍሌ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በወቅቱ የሚያስፈልገንን ያህል በጀት ማግኘት ባለመቻላችንና የግንባታ ዕቃ ባለማሟላታችን ነበር፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ሙዚየሙ ቋሚና ጊዜያዊ ኤግዚቢሽኖችን የሚያካትት ሲሆን፣ የዲዛይን ሥራው የገጠሪቱን ኢትዮጵያ ባህላዊ ቤቶችን እንዲያንፀባርቅ ተደርጐ የተሠራ ነው፡፡ በተጨማሪም ሙዚየሙ የአገሪቷን የቡና መገኛነት ከማንፀባረቁም ባሻገር የቡናን ባህላዊና ታሪካዊ ዳራና ሥነ ሥርዓት እንዲያሳይ ታስቦበት የተሠራ መሆኑን የዞኑ አስተዳዳሪ ያብራራሉ፡፡

ግንባታውን ታዬ አስፋው ሕንፃ ተቋራጭ የተባለ ድርጅት እያከናወነው መሆኑን፣ እስካሁንም ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ እንደተከፈለው ከአቶ ክፍሌ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሚተላለፍ መሆኑ ታውቋል፡፡

ከአምስት ዓመት በፊት የሙዚየሙ ግንባታ በፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የመሠረተ ድንጋይ ተጥሎ በይፋ መጀመሩ ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ የኦሮሚያ ክልልም የራሱን የቡና ሙዚየም በጅማ ከተማ በመገንባት ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡    
http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/8553-2012-11-17-12-32-47.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር