የሲዳማ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄ


ከማህበራዊ መረብ ላይ የተገኘ ጽሁፍ
የሲዳማ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄ
መግቢያ
አገራችን ለአያሌ ዘመናት ለተለያዩ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ተጋልጣ የቆየች በመሆኗ አብዛኛው ህዝቧ በድህነት አረንቋና በኋላቀርነት ቀንበር ተተብትቦ መኖሩ የማይካድ ታሪካዊ ሀቅ ነው::
የሲዳማ ህዝብም የዚሁ አስከፊ ሰቆቃ ተጠቂ በመሆኑ ይህንን ነባራዊ ችግር ለመታገልና ለመፍታት ፈርጀ-ብዙ ትግል ማድረግ በማስፈለጉ፣ እንዲሁም የችግሩን መሠረታዊ ምንጭ አጉልቶ ለማሳየትና የመፍትሔውንም አቅጣጫ ለመጠቆም የሚያስችል የትግል ስልት ያካተተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጽሑፍ ለማዘጋጀት ተገደናል::
እንደሚታወቀው የሲዳማ ብሔር ባለፉት አፋኝ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቶች ሥር ከመውደቁ በፊት የራሱ የሆነ ባሕላዊ የአስተዳደር ሥርዓት (The Luwa System)፣ ቋንቋና(Sidaamu Afoo) ባህል፣ የራሱ የሆነ ታሪካዊ አመጣጥ ያለው ህዝብ ሆኖ በአንድ ጆኦግራፊያዊ ክልል ሰፍሮ የሚኖር በአንድ ስነልቦና የተሳሰረ ታላቅ ብሔር እንደሆነ ይታወቃል::ይሁን እንጂ ህዝቡ በእነዚያ አስከፊና አፋኝ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቶች ሥር ከወደቀ በኋላ በራሱ ማስተዳደር እንዳይችልና ነፃነት እንዳይኖረው ፣ በገዛ ክልሉ ሊኮራባቸው ቀርቶ በአደባባይ በቋንቋውና በባህሉ እንዳይጠቀምበት ይልቁንም እንዲያፍርበት ተደርጎ ቆይቷል:: በአጠቃላይ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ልማት የበላይ ባለቤትነትና ተጠቃሚነት እንዳይኖረው በተለያዩ ሥውር ስልቶች ተከልክሎ ቆይቷል:: ከእነዚህ አስከፊና አፋኝ ፀረ- ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቶች ለመላቀቅ በየሥርዓቱ በተናጠል፣ በቡድንና በተደራጀ መልኩ ሳይታገል ያለፈበት አንድም ጊዜ አልነበረም:: በተለይ የንጉሣዊው ሥርዓት ተገርስሶ ደርግ ሥልጣኑን በጨበጠ ማግስት የመሬት ከበርቴውን አካርካሪ በመስበር መሬት ለራሹ የሚል አዋጅ የካቲት 1967 .ም አበሰረ:: የመሬት ይዞታ በአርሶ አደሩ ባለቤትነት ተረጋገጠ:: መሐይምነትንም ለማጥፋት ሲባል ያልተማረ ይማር፣ የተማረ ያስተምር፣ የማይጽፉ እጆች እንዲሁም የማያነቡ ዓይኖች አይኖሩም በሚል መርህ የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ አዋጅም ወጣ:: እነዚህና መሰል ብሔራዊ እንቅስቃሴዎች ተደረጉ እንጂ ለዘመናት የህዘቦች ጥያቄ ሆኖ የቆየው መሠረታዊ የፖለቲካ ሥልጣን ጥያቄ ሳይመለስ ተዘለለ::ለዚህ ምክንያት ሆኖ የሚጠቀሰው የፊውዳሉ ሥርዓት በህዝባዊ ንቅናቄ ተገረሰሰ እንጂ የቢሮክራሲው አሠራሮች፣ የአፈና፣የጸጥታና የደህንነት መዋቅሮች ሙሉ በሙሉ ስላልተበጣጠሱ/ሥር-ነቀል ለውጥ ሳይደረግባቸው/ የመሬት ከቤርቴው ቅሪቶች መልካቸውን ቀይረው በደርግ ሥርዓት ውስጥ በብዛት በመሰግስግ ውስጥ ለውስጥ ድብቅ የአፈና መዋቅር ዘረጉ:: የህዝቡ የፖለቲካ ሥልጣን ጥያቄዎችም ተዳፈኑ፣ በተለይ ገዢዎቹ የከተማውን ሥልጣን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር የብሔሩ ልጆች ነቅተው እንዳይደራጁ በማድረግ የተለመደውን ጭቆናና የብዝበዛ መረባቸውን ዘርግተው ከመቼውም ጊዜ የበለጠ አጠናክረው ቀጠሉ::በተለይም የደርግ መንግሥት ለይስሙላ ያደራጃቸውን መኢገማ፣ መኢሴማ፣ መኢወማ የመሳሰሉት “ህዝባዊ ማህበራት” መጠቀሚያ መሣሪያ በማድረግ የብሔሩን ልጆች በጉዳይ አስፈጸሚነት መመልመልና መሾም ተያያዙት፤ በተለይ በሲዳማ ውስጥ አድገው የህዝቡን ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክና ስነ-ልቦናውን ጠንቅቀው በሚያውቁ የሌላ ብሔር ተወላጆች ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠትና ቁልፍ ሚና እንዲጫወቱ በመሾም በሲዳማ ህዝብ ላይ ሥውር የጥቃት ዕላማቸውን አጧጧፉ::ይህ ሁኔታ ያስመረራቸው ጥቂት የማይባሉ ሥልጣን ላይ የነበሩና ከሥልጣን ውጭ ያሉ የብሔሩ ተወላጆች ሥልጣናቸውንና መንግሥት የሰጣቸውን ኃላፊነት እርግፍ አድርገው በመተው የትጥቅ ትግል ለማካሄድ ትውልድ ቀዬአቸውንና አገራቸውን ጥለው ወደ ጎረቤት አገር ኮበሌሉ፣ እንዲሁም የትጥቅ ትግሉን በይፋ ጀመሩ::የሲዳማ ብሔር የንጉሡ ሥርዓት ተገርስሶ መሬት ለራሹ በተባለ ጊዜ የደርግን አብዮት በነቂስ ወጥቶ ሲደግፍ የቆየ ቢሆንም ወታደራዊው አምባገነን መንግሥት ሲከተል የነበረው አካሄድና አሠራር ህዝቡን ጥርጣሬ ውስጥ ስለከተተው በአብዮቱ ላይ ጥላቻ ፈጥሮበታል:: ምክንያቱም የመሬት ጥያቄ ለይስሙላ ያህል ተመለሰ ተባለ እንጂ ህብረተሰቡ ባመረተው ምርት ተጠቃሚ አልነበረም:: ከሁሉም በላይ ትልቁና ቁልፍ ጥያቄ የነበረው የፖለቲካ ሥልጣን ሲሆን ይህ ጥያቄ ባለመመለሱ የሲዳማ ህዝብ በአብዮቱ አምጾ ወደ ግልጽ የትጥቅ ትግል ለመግባት ተገደደ:: በዘመነ አፄ ምኒልክ ጊዜ አፌ ንጉሥ ሉዑልሰገድ የተጠቀመው የከፋፍለህ ግዛ ፖሊስ ዓይነት ደርጎችም ይህንኑ ተመሣሣይ አሠራር በመከተል የህዝቡን አንድነትና ብሔራዊ ማንነቱን በመናድና ሰርጎ በመግባት ሥውር ተልዕኮአቸውን ዕውን አደረጉ:: የየሥርዓቶቹ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊስ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ እንዲሉ ሆነ:: ይህ ሁሉ ጭቆና በእጅጉ ያበሳጨው የሲዳማ ብሔር የአቶ ወልደአማኑኤል ዱባሌ ፋና /ዱካ/ ተከትሎ የደርግን መንግሥት በይፋ በመቃወም በዓለም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከ11 ሺህ በላይ የብሔሩ ተወላጆች ለትጥቅ ትግል ወደ ጫካ ገቡ:: በመቀጠልም ወደ ሶማሊያ በረሃዎች በማምራት እጅግ እልህ አስጨራሽ፣ ረጅምና መራራ ጉዞ በመጓዝ ክላሽንኮቭ፣ ጂ-3 ፤ መትሪየስ(-አር)፣ ስኖፍ፣ምንቶቭ… ወዘተ የተባሉ በወቅቱ እጅግ ዘመናዊ ተብለው የሚታወቁ አውቶማቲክ የጦር መሣሪዎችን በመታጠቅ ከደርግ መንግሥት ጋር ግንባር ለግንባር በመግጠም ጠንካራ ውጊያ አካሂዶ ለደርግ መንግሥት የእግር እሳት ከመሆኑም በላይ ለውድቀቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል:: በተለይ ከ1969 .ም እስከ 1975 .ም ድረስ የደርግ መንግሥት ተጠናክሮ በሁለት እግሩ የቆመበት ወቅት ስለነበረ ትግሉን እጅግ መራራ አድርጎታል:: የሲዳማ ህዝብ ሰላም፣ ልማትና እኩልነት በተጠማበት ሰዓት ላይ ወደማይፈልገው ጦርነት እንዲገባ ያስገደደው ዋነኛ ምክንያት ከላይ እንደተጠቀሰው የፖለቲካ ሥልጣን ጥያቄ አለመመለስ በመሆኑ እንዲሁም የኢኮኖሚ ባለቤትነትና ተጠቃሚነት መብት ስላልተረጋገጠለት የደርግን መንግሥት በአደባባይ ተቃወመ:: ተቃውሞውንም የስሜቱ መገለጫ በሆነው ጭፈራና ቄጣላ እንደሚከተለው ገለጸ:: ይኸውም “Mangistu Baana Darge Diqaala
Moohi Duguna (Amaanueli) Ane Aana”
የሚል እንደነበር እናስታውሳለን::ከላይ እንደተጠቀሰው የሲዳማ ህዝብ በንጉሡ ሥርዓት አስከፊ አገዛዝ ወቅት ብሔራዊ ማንነቱ ላይ ከፍተኛ በደልና መደባዊ ጭቆና ካረፈባቸው ህዝቦች አንዱ መሆኑ የታሪክ አሻራ ከመሆኑም በላይ የጭቆናው ቀንበር ምን ያህል አሳማሚ እንደነበር አሁን በሕይወት ያሉ የመከራው ገፈት ቀማሽ አባቶች በምሬት ያወሳሉ::ሕዝቡ የማንነቱ መገለጫ የሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮች ማለትም ቋንቋው፣ ባህሉና ታሪኩ ተረግጠውና ተንቀው ያለፍለጎቱ የተጫነበትን ጨቋኝ ሥርዓት የዚያነም ቢሆን አሜን ብሎ አልተቀበለውም:: ሥርዓቱ ይባስ ብሎ የገዛ መሬቱን በመቀማትና የንጉሡን ታማኝ ነፍጠኞች አምጥቶ በማከፋፈል የይዞታ ባለቤት የነበረውን ሕዝብ ጭሰኛና የበይ ተመልካች፣ ርስት አልባ እንዲሆን ባደረገው ጥረት ባይሳከለትም የአቅሙን ያህል ሞክሮ ነበር:: ነገር ግን ምንም ዓይነት የዴሞክራሲ ጭላንጭል ባልነበረበትና የተደራጀ ትግል ማድረግ በማይቻልበት በዚያ ድንግዝግዝ የጨለማ ሥርዓት ወቅት እንኳን የሲዳማ ህዝብ ውስጥ ለስውጥ ህቡዕ ትግሎችን በማካሄድ በሥርዓቱ ላይ የነበረውን ተቃውሞ ከማሰማት ተሸማቆ አያውቅም:: ማንኛውንም አጋጣሚ በመጠቀም ከተቻለ እስከንጉሡ ድረስ የህዝቡን ታማኝ እንደራሴዎች በመላክ፣ አሊያም ደግሞ በአካባቢው የተለያዩ የተቃውሞ ስሜቶችን በማንጸባረቅና ተገቢውን ምላሽ በማግኘት ማንነቱን አስከብሮ የቆየ ጠንካራና እጅግ የተሳሰረ ማህበረሰብ (Highly Integrated Society) ነው:: የንጉሡ ሥርዓት ከዳር እስከዳር በተነቃነቀ ህዝባዊ አመፅ ሲገረሰስ ሕዝባዊ አብዮቱን ለመምራት በቂ ዝግጅት ሣይኖረው የኢትዮጵያን ህዝብ ለማስተዳደር ድንገት በሥልጣን ኮርቻ ላይ የተቆናጠጠው ወታደራዊው የደርግ መንግሥት ለረጅም ዘመናት የህዝብ ጥያቄ ሆኖ የቆየውን የመሬት ጉዳይ “መሬት ላራሹ” በሚል መርህ ለባለይዞታው ሲመልስ በወቅቱ ሰፊ ድጋፍ አግኝቶ ነበር:: ሆኖም የደርግ ሥርዓት እያደር አፋኝ፤ ኢ-ዴሞክራሲያዊና መደባዊ ጭቆናን በሕዝቦች ላይ እያበረታ ሲሄድ የሲዳማ ሕዝብ ውስጥ ለውስጥ ሲያካሄድ የነበረው ሕዝባዊ ትግል ገንፍሎ በመውጣት ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው በ1971 .ም ከ11ሺህ የሚበልጥ ሕዝብ የተደራጀ የትጥቅና የፖለቲካ ትግል ለማድረግ ወደ ሲዳማ ጠረፋማ አካባቢዎችና ሶማሊያ በረሃዎች ልዩ ሥፍራ ሐማራ ወደ ተባለ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሥልጠና ማዕከል ተመመ:: ይህ አመጽ የወለደው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (Sidama Libration Movement) በህዝቡ ውስጥ የተቀሰቀሰውን የፖለቲካ ትግል በመምራት የደርግን ሥርዓት ክፉኛ በማስጨነቅ ከሌሎች ለዴሞክራሲ ከተዋደቁ አጋር ኃይሎች ጋር በማበር ለሥርዓቱ መውደቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የኢትዮጵያ የትግል ታሪክ ያረጋግጣል:: በተጨማሪም አፋኙ የደርግ መንግሥት በሀቀኛ ኢትዮጵያውያን የጋራ ትግል ሲገረሰስ የደስታ ችቦ ካቀጣጠሉ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ(ሲአን) የኢትዮጵያ የሽሽግር መንግሥት መመሥረቻ ቻርተር ከጸደቀ በኋላም ለተመሠረተው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ግንባታ አዎንታዊ ሚና የተጫወተ አንጋፋ ድርጅት ነው::ስለዚህ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ የፖለቲካ ትግል ታሪክ አሁን ሥልጣን ላይ ካሉት የሕወሓትና የቀድሞው ኢህዴን የአሁኑ ደግሞ ብአዴን የትግል ታሪክ የሚተናነስ እንዳልሆነ የሚታወቅ እውነት ነው:: ይህ ሁሉ የሲደማ ህዝብ ተጋድሎ የተነጠቀውን የፓለቲካ ሥልጣን በእጁ በማስገባት ህዝቡንና ሀብቱን በአግባቡ መርቶ መብቱንና ጥቅሙን ለማስከበር ነው::የሲዳማ ህዝብ በዘመነ ኢህአዴግ!!በአገራችን የአፈና ሥርዓት ተወግዶ በምትኩ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማቆጥቆጥ ከጀመረበት ከ1984 .ም ጀምሮ የሲዳማ ህዝብ በርካታ የመብት ጥያቄዎቹ በሕገ መንግሥቱ ተካትተዋል:: ከሽግግር መንግሥት ቻርተር ቀጥሎ በሕዝቦች ተሳትፎ የጸደቀው የጋራ መተዳደሪያ የሕጎች ሁሉ የበላይ ህግ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እንደ ሌሎቹ የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለሲዳማ ብሔርም መሠረታዊ የመብት ጥያቄዎችን ሊመልሱ የሚችሉ አንቀጾች በሕገ መንግሥቱ ተረጋግጠዋል::ለአብነት ያህል፤ 
-
የሲዳማ ህዝብ ህገ መንግሥታዊ መብቱን በመጠቀም የራሱ የሆነ መሪ የፖለቲካ 
ድርጅት መሥርቶ መደራጀቱ፤
-
ራስን በራስ የማስተዳደር መብት መጎናጸፉ፣
የማንነቱ ማረጋገጫ የሆኑትን ቋንቋውን፣ ባህሉንና ታሪኩን መጠቀም፣ ማሳደግና መንከባከብ መቻሉ፣
የሲዳምኛ ቋንቋን የትምህርትና የሥራ ቋንቋ አድርጎ በዞኑ መጠቀም መቻሉ፣ እንዲሁም የዳኝነት ሥርዓቱ ወጥ በሆነ የቋንቋ አጠቃቀም መከናወን መቻሉ፣
በቀደሙት ሥርዓቶች ተመሣሣይ መደባዊ ጭቆና ካደረሰባቸው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በፍቅርና በመከባበር መርህ ላይ የተመሠረተ አንድነት መኖሩ፣
ሕዝቡን የልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ፍትሓዊ የበጀት ክፍፍል እንዲኖር የሚያስችል አሠራር መኖሩ፣
የሲዳማን የሕዝብ ብዛት ከግምት ባስገባ አሠራር በሁሉም የመንግሥት መዋቅር ላይ ፍትሓዊ የሕዝብ ውክልና የሚኖርበት አሠራር መፈጠሩ፣
ሕገ መንግሥቱ የማይፈቅዳቸው የጣልቃ ገብነት አሠራሮች ከላይ እስከታች እንዳይኖር አሠራር መዘርጋቱና የራሱን የውስጥ ጉዳይ በራስ መተማመን(Self-confidence) የመፍታት ሕገ መንግሥታዊ መብት መኖሩ፣
የሲዳማ ዞን ዋና ከተማ፣ የክልሉ መንግሥት ደግሞ መቀመጫ የሆነው ሐዋሳ ከተማ የአስተዳደር ተጠሪቱ የሲዳማ ዞን አስተዳደር ሥር መሆኑና የዞኑ ምክር ቤት ትክክለኛ የሥልጣን ባለቤትነቱን የሚረጋገጥበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩና ሌሎችም መሰል ጥቅሞች ሊጠቀሱ ይችላሉ::እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩ መሠረታዊ መብቶችና ሌሎች ተያያዥ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ከሞላ ጎደል ኢህአዴግ ሥልጣን ላይ በወጠባቸው የመጀመሪዎቹ ዓመታት በመመለሳቸው የሲዳማ ህዝብ ደስተኛ ነበር:: እስከ 1985 .ም ድረስ ለሁለት ያህል ዓመታት የሲዳማ ሕዝብ ክልል ስምንት በሚባል አዲስ የአደረጃጀት ስያሜ በአንፃራዊ መልኩ የተሻለ ሁኔታ ይተ” ዳደር ስለነበር ከሌሎች የአከባቢ ሕዝቦች ጋር የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል ሽኩቻ እምበዛም አልነበረም::ታዲያ ሀቁ ይህ ሆኖ ሣለ የሲዳማን ሕዝብ ያስከፋው ምንድር ነው? የሕዝቡን ቁጣ የቀሰቀሰው፤ የሲዳማን ሕዝብ ከልቅ እስከ ደቂቅ ከዳር እስከ ዳር ያነቃነቀውና የዘወትር ራስ ምታት የሆነበት የፖለቲካ ጥያቄስእነሆ ወደ መልሱ!!!እንግዲህ ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው እስከ 1985 .ም ድረስ “ክልል-8” ይባል የነበረው የሲዳማ አከባቢ ምንም ዓይነት አሳማኝና መሠረታዊ ጥናት ሣይደረግበት፣ እንዲሁም የሥልጣኑ ባለቤት ነው የተባለው ሕዝብ ይሁንታ ሣይጠየቅ በጥቂት የድርጅቱ አባላት ሹማምንት በጎ ፈቃድና ፍላጎት ብቻ የደቡብ ክልል በሚል አደናጋሪ አጠራሪ የብሔራዊ አደረጃጀትን መሠረት ያደረገ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሚጻረር አሠራር ተተካ:: በመሠረቱ በየትኛውም የአገራችን ክፍል የሰሜን ክልል ወይም ሕዝብ፣ የምሥራቅ ክልል ወይም ሕዝብ፣ የምዕራብ ክልል ወይም ሕዝብ የሚል ተመሣሣይ አደረጃጀት አልነበረም ወይም የለም፤ ተሰምቶም አይታወቅም:: በአንድ ሕገ መንግሥት የሚተዳደር አንድ ሉዓላዊ አገር ውስጥ ሊኖር የሚገባው አሠራር አንድ ዓይነትና ወጥነት ያለው እንጂ ባለሁለት ገጽታ ሊሆን እንደማይችል ሣይንሳዊ እውነት ነው::በደቡብ ክልል የሆነው የፖለቲካ ክስተት ግን ከዚህ እውነት ያፈነገጠ እጅግ ታቃራኒ አሠራር በመሆኑ በወቅቱ ራሳቸውን ችለው የተደራጁ ክልል 7፣ ክልል 8፣ ክልል 9፣ ክልል 10፣ እና ክልል 11፣ በድምሩ አምስት ክልሎች ነገር ግን በሥነ_ልቦና፣ በቋንቋና ባህል፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዕድገት፣ በጆኦግራፊያዊ አቀማመጥ ፈጽሞ የማይገናኙ ሕዝቦች አንድ መለስተኛ ጎጆ ተቀልሶላቸው በዚያ ጠባብ ቤት ውስጥ ተከባብራችሁ ኑሩ፣ ልዩነታችሁ ውበታችሁ ነው በሚል መርህ ታጭቀው ሣይፈናፈኑ ለመኖር ተገደዱ:: እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የሲዳማ ህዝብ ሕገ መንግሥቱ ያጎናጸፈውን መሠረታዊ የፖለቲካ መብት አሁዱ ብሎ የተነጠቀው ወይም መነጠቅ የጀመረው::በአገራችን የፖለቲካ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝቦች ከፍተኛ ተሣትፎና ይሁንታ በ1987 .ም የፀደቀው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የጂኦግራፊ አቅጣጫን ወይም አከባቢን ሣይሆን የብሔር ብሔረሰቦችን ማንነት መሠረት ባደረገ መልኩ መደራጀትን ወይም አወቃቀርን የሚፈቅድ በመሆኑ በወቅቱ “የደቡብን ክልል” በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ወክለው በሕገ መንግሥት ጉባኤው ላይ የተሣተፉ የሕዝብ እንደራሴዎች ወሳኝ ጉዳዮችን በማንሣት ምክንያታዊ ክርክሮችን ማካሄዳቸው ይታወቃል:: በተለይ የሲዳማን ሕዝብ ወክለው ጉባኤውን በወቅቱ የተቀላቀሉት አመራሮች የደቡብ ክልል አወቃቀር እንደሌሎች የአገሪቱ ክልሎች እንደ አማራ ክልል፣ እንደ ኦሮሚያ ክልል፣ እንደ ትግራይ ክልል የሚታይ ሣይሆን እያንዳንዱ ዞን ወይም ልዩ ወረዳ በውስጣቸው የሚገኘውን ሕዝብ የሚወክሉ በመሆኑ ሕገ መንግሥቱ ለነዚህ በርካታ ስብጥር ህዝቦች ልዩ ግምት(Special Consideration) እንድሰጣቸው አበከረው ተከራክረዋል::ይህ ምክንያታዊ ክርክርና መሠረተ-ሐሳብ (Logical Argument) ከብዙ አከራካሪ ውይይት በኋላ ለሲዳማ ህዝብ እንደራሴዎች ውሳኔው አሳማኝ ሆኖ ባይዋጥላቸውም የቀረበው ሀሳብ በተግባር ተተርጉሞ የሥልጣኑ ባለቤት በሆነው ህዝብ ዘንድ ቀርቦ ተቀባይነቱ እስኪረጋገጥ ድረስ በስምምነት ታለፈ:: በዚሁ ልዩ ግምት መሠረት እያንዳንዱ ክልል የራሱን ተጨባጭ ሁኔታ፣ የሕዝቦችን መሠረታዊ የመብት ጥያቄና ፍላጎት ከግምት አስገብቶ ክልላዊ ሕገ መንግሥት ማዘጋጀት ይችላል የሚል የመፍትሔ አቅጣጫ በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 50 ንዑስ አንቀጽ 4 ስለተቀመጠ ጉባኤው በአንድ ዓይነት የስምምነት አቋም ሊጠናቀቅ ችሏል:: በዚሁ መነሻ በሰኔ 1987 .ም የጸደቀው የደቡብ ክልል ሕገ መንግስት በአንቀጽ 69 የክልሉን ሕዝብ በተለይም በዞንና በልዩ ወረዳ ደረጃ የተዋቀረውን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝብ መሠረት ያደረገ አወቃቀር ሥራ ላይ ዋለ:: የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች በእኩልነት ያጎናጸፋቸው ዴሞክራሲያዊና ፖለቲካዊ መብቶች መረጋገጥ ጀመሩ:: በዚህ ወቅት የሲዳማ ሕዝብ ከሞላ ጎደል መሠረታዊ መብቶችን በማስከበር የተገኙ ድሎችን መንከባከብና ማጣጣም ጀመረ:: ቀሪ ጥያቄዎችም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ እስካለ ድረስ በመሪው ድርጅት ሲህዴድ ትግል በሂደት ይመለሳሉ በሚል ፅኑ እምነት ቀጠለ::ይሁን እንጂ የሲዳማ ሕዝብ በዚህ እምነትና ተስፋ ብዙም ሣይጓዝ በ1988 .ም አስቸጋሪ ፈተና ገጠመው:: ወቅቱ የሲዳማ ህዝብ እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለረጅም ዓመታት ሲታገልለት የኖረው ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በሕገ መንግሥቱ በመረጋገጡ የሐዋሳን ከተማ ጨምሮ የማስተዳደር ሥልጣን ተገናፅፎ የአከባቢው ሕዝብ የመሠረተ ልማት አገልግሎት ወደተሟላለት የከተማ ሕይወት ገብቶ ሕገ መንግሥቱ የፈጠረለትን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ተሣትፎ መብቱን እንዲያረጋግጥ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ የሚደረግበት ጊዜ ነበር:: በዚህ ወቅት ነው እንግዲህ በሊዝ ፖሊሲ አዋጅ ሰበብ ለሲዳማ ዞን አስተዳደር ከላይ የተጠቀሰው ፈተና የቀረበበት::የሊዝ አዋጁ ሕዝቡ በግልጽ ሣይመክርበት፣ በወቅቱ የሕዝቡን ውክልና ይዞ ኃላፊነት ላይ የነበረው አመራር ሣያውቀውና ሣይወያይበት በአርባ ምንጭ ከተማ በተደረገው የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ በድንገት የመወያያ አጀንዳ ሆኖ ብቅ አለ:: ጉባኤው በቀረበው አጀንዳ ላይ ሰፍ ውይይት ካደረገ በኋላ የሊዝ ፖሊሲ አዋጁ የሲዳማንም ሆነ የሌላውን ሕዝብ መሠረታዊ ጥቅሞች የማያስከብርና ይልቁንም ሕገ መንግሥቱ ለአካባቢው ሕዝብ ያረጋገጠውን መብት መልሶ የሚነጥቅ በመሆኑ በሙሉ ተቃውሞ ውድቅ ተደረገ:: በዚህ ውሳኔ ሕዝቡ ጊዜያዊ እፎይታ አግኝቶ የከተማው ልማት ቀጥተኛ ተጠቃሚ መሆኑን ቢያረጋግጥም የሊዝ ፖሊሲው በደፈጣ ውጊያ አሳቻ ጊዜ ላይ በወቅቱ የነበሩ የዞኑ አመራር አካላት ከሥልጣን እንዲወገዱና በምትካቸው ለዘብተኛ አቋም ያላቸው አመራሮች እንድቀመጡ ተደርጎ በተፈጠረ ቀዳዳ በመጠቀም ድጋሚ ቀርቦ በ1990 .ም የሊዝ አዋጁ ተግባራዊ እንዲሆን ተወሰነ:: አዋጁ ይጽደቅ እንጂ በአፈፃፀም ላይ ያጋጠመው ፈተና በቀላሉ የሚዘልቅ አለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነበር::ይህ ብቻ ሳይሆን በሰኔ 1987 .ም በወጣው የደቡብ ክልል ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 69 ላይ የተደነገገው ሥልጣን የዞኖችንና የልዩ ወረዳዎችን ሕግ የማውጣት፣ የዳኝነትና የማስፈጸም መብት በአዋጅ ቁጥር 35/1994 ተሻሻሎ በጸደቀው በአዲሱ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 80 እንዲቀየር ተደርጎ ለብሔራዊ ዞኖች እና ለልዩ ወረዳዎች የተሰጠው ሥልጣን ተነጠቀ፣ ሥልጣንና የመወሰን ኃይል ሙሉ በሙሉ በአቅጣጫ ወደተሰየመው ደቡብ ክልል ተጠቅልሎ እንዲገባና ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ሽባ መዋቅር ተራ አሻንጉሊት (Puppet) እንዲሆኑ አደረጋቸወ:: የሲደማ ህዝብ በዚህ ክልል ከተጨፈለቁ ህዝቦች በህዝብ ቁጥር አንደኛ፣ በአገሪቱ ደግሞ 4ተኛ ደረጃን ይዞ የሚገኝ አንጋፋ ብሔር እንደመሆኑ መጠን የዚሁ ችግር የመጀመሪያ ሰለባ ለመሆን በቃ::1994 .ም የሲዳማ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሲዳማን ያታግላል፣ ያደራጃል ያነቃል በሚል እሳቤ በኢህአዴግ ጥላ ሥር የተቋቋመው ይኸው የፖለቲካ ድርጅት “የጥገኞች መሰባሰቢያና የጠባቦች መፈልፈያ መዋቅር ስለሆነ መጥፋት አለበት” ተብሎ ደብዛው እንዲጠፋ ተደርጎ በምትኩ ሕዝባዊ መሠረት የሌለው፣ ደኢህዴን የሚባል ብሔር ብሔረሰብ በክልሉ በሌለበት ሁኔታ የኢህአዴግን የአደረጃጀት መርህ በጣሰ መልኩ አየር ላይ የተንጠለጠለ ድርጅት “ደኢህዴን” ተመሥርቶ ሁሉም በዚሁ ቅርጫት ውስጥ እንዲገቡ መደረጉ ህዝባችን መሪ የብሔሩን ድርጅት እንዲያጣ፣ መረጋጋት እንዳይኖረው፣ ተስፋ እንዲቆርጥ፣ ኢኮኖሚያዊ አቅሙ እንዲዳከም በሴረኞች አድማ ሆን ተብሎ የተጠነሰሰ እንደሆነ ተደርሶበታል::ይህ ሁሉ ሲሆን በአንድ ሕገ መንግሥት፣ በአንድ ፓርቲ፣ በአንድ ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ የሚተዳደረው የደቡብ ሕዝብ ተመሣሣይ የፖለቲካ መብት ጥሰትና ሕገ መንግሥታዊ ጥቅሞቹ ሲቀሙበት በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ግን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በትክክል ተፈፃሚ እየሆነ ይገኛል፣
ለምሳሌ፤ በኦሮሚያ ክልል ኦህዴድ፣ በትግራይ ክልል ሕወሓት፣ በአማራ ክልል ብአዴን እና ሌሎችም ብሔሮቻቸውን ወክለው በሕይወት መኖራቸው፣ እንዲሁም በእነዚህ ክልሎች ራስን በራስ የማስተዳደር ዴሞክራሲያዊ መብትና የልማት ተቋማት እንዳይዳከሙ፣ እንዳይፈርሱ፣ እንዳይጠፉና ይልቁንም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የተደረገው ብርቱ ትግል የሕገ መንግሥቱን ተፈጻሚነት ያሳያል:: በእንዲህ ዓይነት የፖለቲካ ግፊት እየተነዳ የሲዳማ ህዝብ ለ1994 .ም ደረሰ፣ ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የሲዳማ ህዝብ በኢህአዴግ ሥርዓት ቀደም ባሉት ጨቋኝና የአፈና ሥርዓቶች የተቀማውን መሠረታዊ የፖለቲካ መብት መልሶ በእጁ በማስገባት ተጠቃሽ ድሎችን በማጣጣም ላይ ባለበት ወቅት በ1994 ዓመተምህረት ያጋጠመው ሌላው አስደንጋጭ አደጋ የሐዋሳን ከተማ የማስተዳደር ሥልጣን ሰበብ በማድረግ በሲዳማ ሕዝብ ላይ የተፈጸመው ኢ_ሰብአዊ ጭፍጨፋ የሕገ መንግሥቱን ተአማኒነት አደጋ ላይ የጣለ፤ የኢህአዴግን ሕዝባዊ ውግንና ጥያቄ ውስጥ የከተተ፣ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊውን ሥርዓት በዓለም አቀፍ መድረክ ያስተቸና ክፉኛ ያስነቀፈ ክስተት ሆኖ በታሪክ ማስታወሻነት ወይም አሻራነት ተመዝግቧል:: ይህ Looqe Massacre ተብሎ የሚታወቀው ክስተት በታሪክ ማስታወሻነት የሚዘከረው በመልካም ገፅታው ሣይሆን የሲዳማ ህዝብ ከኢህአዴግ የማይጠብቀው፤ ነገር ግን በሠላማዊ ሕዝብ ላይ የተፈጸመ ኢ-ሰበአዊ ድርጊት የበርካታ ዜጎች የሕይወት መስዋዕትነት ያስከፈለና የደም ዕዳ ያለበት ጉዳይ በመሆኑ ነው::1993 .ም በነበረው አገራዊ የፖለቲካ ተሃድሶ ሰበብ ወደ ደቡብ ክልል የገሰገሰው የነውጥ ማዕበል ከሌሎች ይልቅ በሲዳማ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ያሳረፈበት ወቅት ነበር:: ይህ የተሃድሶ ነውጥ በ1994 ዓም በሲዳማ ህዝብ ላይ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት መሠረታዊ ስህተቶች እንዲፈጸሙበት ምክንያት ሆኖአል፤
የሲዳማ ሕዝብ የሀዋሳን ከተማ የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መብት ሙሉ በሙሉ የተቀማበትና ይህንን ውሳኔ በሠላማዊ መንገድ ተቃውመው የፍትሕ ጥያቄ ባቀረቡ የሲዳማ ተወላጆች ላይ የመንግሥት ታጣቂ ኃይል ተኩስ በመክፈት የለጋ ወጣቶችን ሕይወት በመቅጠፍ የወሰደው አረመኔያዊ እርምጃ ለታሪክ የማይረሳ ጠባሳ መፈጠሩ፣
የሲዳማን ሕዝብ ፖለቲካዊና ሕገ መንግሥታዊ መብት ለመንጠቅና ለመሸራረፍ በማሰብ ብቻ የህዝቡ ይሁንታ ሣይጠየቅ፣ ተገቢው ምክክርና ውይይት ሣይደረግበት፣ በወቅቱ ለሥልጣን በቋመጡ ግለሰቦች ፍላጎትና ፈቃድ ላይ በተመሠረተ አገባብ የክልሉን ሕገ መንግሥት በአዋጅ ማሻሻል ወይም መቀየር፣
የሲዳማን ሕዝብ በኢህአዴግ መስመር በመምራት ታሪካዊ ሚና የተጫወተውን መሪ የፖለቲካ ድርጅት የሲዳማ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት(ሲህዴድ) የድርጅቱ መሥራችና ባለቤት የሆነው የሲዳማ ሕዝብ ተራ አስተያየት እንኳን ሣይሰጥበት ደብዛው ከምድረ ገጽ እንዲጠፋ ሥውር ሤራ የተሸረበበት መሆኑ፣
ታሪካዊ ዳራ (Historical Background) የሌለውና አየር ላይ የተንጠለጠለው በአሮጌው አጠራር ደኢህዴግ በአዲሱ ደግሞ ደኢህዴን ተብየው እንዲመሠረት የሕዝብ ውግንና መንፈስ የሌላቸው ጥቂት ግለሰቦች ተረባርበው ውሳኔ የሰጡበት ጊዜ ነበር፣ ይህ በወቅቱ የተመሠረተው ደኢህዴን ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም እንዲሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያቋቋሙአቸው ዴሞክራሲያዊ ድርጅቶችን በኃይል በመዋጥ በፈረጠመ ጡንቻ ብቻውን ፈላጭ ቆራጭ የመሆን ዓላማ አንግቦ ይመስረት እንጂ ማንን እንደሚወክል እንኳን በውል የማይታወቅ ድርጅት ነበር፣ 
የዚህ ዓይነት ተመሣሣይ የፖለቲካ አደረጃጀት በሌሎች በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች አልተሞከረም፣ ቢሞከርም አይሆንም:: እንደ እውነቱ ከሆነ መሞከርም የለበትም፣ ምክንያቱም ኢህአዴግ በአገር ደረጃ ወደ አንድ ወጥ ፓርቲ አልተቀየረምና:: በደቡብ ክልል የሆነው ግን ተቃሪኒው ብቻ ሣይሆን ለማመንም የሚያስቸግር ግራ የሚያጋባ ነውር ነገር ነው:: በአንድ ሉዓላዊ አገር ውስጥ፣ በአንድ የፖለቲካ አመራር ሰጪ ሥርዓት ሁለት ገፅታ ያለው ፖሊሲ ምንኛ ያስገርማል? ብቻ በአጭሩ ክልሉን ቤተ-ሙከራ ያስመስለዋል ብለን ጆሮ ዳባ ልበስ እንዲሉ ዝም ከማለት ውጭ ምን ይባላል!!!::የሲዳማ ህዝብ ግን ቀደም ባለው ሥርዓት የነበረውን መደባዊ ጭቆና ለማስወገድ፣ ለጭቁን ሕዝቦች ነፃነትና እኩልነት መረጋገጥ በሲዳማ አርነት ንቅናቄ(ሲአን) በኩል ከሕወሓት እኩል ዋጋ የከፈለ ሆኖ ሳለ የሲአን አደረጃጀትና አካሄድ በወቅቱ “ለኢህአዴግ አይመችም” በሚል ሐሳብ ሌላ ተለዋጭ እህት የፖለቲካ ድርጅት ሲህዴድ መቋቋሙ አይዘነጋም:: በወቅቱ ይህ ሁኔታ ያስደነገጠው የሲዳማ ህዝብ በ1985 .ም በሲአን መሪነት በተለይ አርቤጎና፣ በንሳና አሮረሳ አካባቢዎች ጦርነት ተቀስቅሶ ከኢህአዴግ ሠራዊት ጋር አላስፈላጊ ትንቅንቅ በመፈጠሩ ለበርካታ ዜጎች ሕይወት መጥፋት መንስኤ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው:: ይሁንና የሲዳማ ህዝብ ነገሩን አስፍቶ በማየት በአካሄዱ ላይ ከፍተኛ ሥጋትና ጥርጣሬ ቢኖርበትም መሠረታዊ ጥቅሞቹና መብቱ በሲህዴድ በኩል የሚረጋገጥ ከሆነ የተለየ ዓላማ የለንም ባለው መሠረት ስምምነት ላይ ተደረሰ:: ይሁን እንጂ ሥጋቱ አልቀረለትምና፣
-
ከሲአንም ከሲህዴድም ሣይሆን ያለ መሪ የፖለቲካ ድርጅት ባዶ እጁን ሲቀር
ታሪካዊ ተጠያቂነትን አያስከትልም ወይ?
-
ለሠላምና ዴሞክራሲ የተከፈለውን ከፍተኛ መስዋዕትነት ዋጋ አያሳጣውምን?
-
ሕገ መንግሥቱ የሰጠንን ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳንጠቀም ያደረገን አባዜ ምንድር ነው?
-
የሲዳማ ህዝብ በ20 ዓመታት ውስጥ የተረጋጋ አመራር፣ ሰላምና ልማት እንዳይኖረው የተፈለገው መነሻ ምክንያቱ ምን ይሆን?መልሱን ለመላው የሲዳማ ተወላጅና እውነትን ለሚፈርድ ወገን እንተወዋለን!!!ሌላው በ1994 .ም በሲዳማ ህዝብ ላይ ብቻ በማነጣጠር የተፈጸመው ታሪካዊ ስህተት በዞኑ ውስጥ እየተካሄደ የነበረውን መልካም የልማት ጅምር እንድደናቀፍ መደረጉ ነው:: በተለይ መንግሥት እያከናወነ ከነበረው ሰፊ የልማት ሥራዎች በተጨማሪ እጅግ ፈጣንና ቀጣይነት ባለው መልኩ በአየርላንድ መንግሥት እርዳታ(Irish Aid Development) በሲዳማ ዞን እየተሠራ የነበሩ ዘርፈ-ብዙ የልማት ጅምሮች ግልጽ ባልሆነ ምክንያት እዚያው ባሉበት መክነው እንዲቀሩ መደረጉ ሌላው አስገራሚ ትንግርት ነው:: በዚሁ ተቋም እየሠሩ የቆዩ ታላላቅ ባለሙያዎች ሥራቸውንና የሚወዱትን አገራቸውን ለቀው እንዲሰደዱ ተደርገዋል፣ ታስረዋል፣ ከሥራ ገበታቸው ተባረዋል ወይም የህሊና ቁስለኞች ሆነው ከቤተሰቦቻቸው ተፈናቅለዋል:: ዳግም ለህዝባቸው መልካም ነገር እንዳያስቡ በመደረጋቸው ሌሎች መልካም የሚያስቡ ካሉም ከእነርሱ ተምረው እንዲሸማቀቁና እንዲቆጠቡ ተደርገዋል:: እነዚህ የልማት ተቋማት ዳግም እንዳያንሠራሩ ተደርገው አከርካሪያቸው ተሰብሮ፣ በሰው ኃይል ልማት እና በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ቀጣይነት ያለው የአየርላንድ የልማት ትብብር ለምን ሲዳማ ብቻ ተለይቶ ያድጋል በሚል የተሣሣተ የምቀኝነትና የቅናት መንፈስ ያ መልካም ውጥን መና ሆኖ እንዲቀር መሰሪ ትግሎች ተካሂደዋል፤ ተሳክቶላቸዋልም:: ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ቢሆንም::በዞኑ የሚገኙ የሲዳማ ልማት ተቋማት እንዳይሞቱ፣ እንዳይኖሩ ሽባ መዋቅር ተደርገው ለይስሙላ እንዲታዩ በተደረገው ርብርብ እነሆ ከህዝቡ ተነጥለው እንደ ተራ ልማት ተቋም የለቀማ ሥራ እየሠሩ የታለመላቸውን ራዕይ ስተው ዕለታዊ ኑሮአቸውን እየገፉ ይገኛሉ፣
የሲዳማ ባህልና ቋንቋ እንዲሁም ታሪክ የማሳደጊያና ማበልፀጊያ የጥናትና የምርምር ማዕከል ገለልተኛ ሆኖ እንዲቋቋም ህዝቡ በተለያየ ጊዜ ውሳኔ ያስተላለፈ ቢሆንም እስካሁን ተግባራዊ እንዳይሆን ተደርጓል፣
የሐዋሳ ከተማ በሲዳማ ዞን አስተዳደር ሥር ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ በሚፈቅደው መሠረት እየተዳደረ እያለ ሐዋሳ ከተማ ልዩ ዞን ይሁን፣ ተጠሪነቱም ከሲዳማ እጅ ወጥቶ ለክልሉ መንግሥት ይሁን፤ በተጨማሪም ውስጥ ለውስጥ ደግሞ የሲዳማ ዞን አስተዳደር ከሐዋሳ ከተማ ይወጣል የሚል ግልፅ ያልሆነ ድብቅ ምኞት አልፎ አልፎ ብቅ ጥልቅ እያለ የሲዳማን ሕዝብ ክፉኛ ያስቆጣ ስለነበር ወቅቱ የውዥንብር ጊዜ ነበር:: ይኸው የሐዋሳ ከተማ አጀንዳ በወቅቱ ለነበሩ የሲህዴድ ከፍተኛ አመራር አካላት ለውይይት ሲቀርብ አጀንዳው ከባድና የሕዝቡን ህልውና ክፉኛ የሚጎዳ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ በመሆኑ አየር በአየር ለመወሰን ስለሚያስቸግር በጉዳዩ ላይ የሲዳማ ሕዝብ ግንዛቤ አግኝቶና መክሮበት የመጨረሻውን ውሳኔ እንድሰጥበት ይደረግ የሚል አቋም በአብዛኛው ተንፀባርቆ ነበር:: ይሁን እንጂ እጅግ በጣም ርካሽ ተወዳጅነትን በማትረፍ ጊዜያዊ የሥልጣን ኮርቻ ላይ ለመውጣት ከፍተኛ ጉጉት የነበራቸው ጥቂት ባለሥልጣናት የሲዳማን ሕዝብ ባለመወገናቸው የተነሣ የሐዋሳ ከተማ አሰተዳደር ከሲዳማ ዞን አስተዳደር እጅ ወጥቶ ልዩ የሽግግር ዞን እንዲቋቋም ፈቀዱ:: ይህም በክልሉ ውስጥ በሚገኙ በሌሎች ትላልቅ ከተሞች ላይ ያልተደረገ፣ ነገር ግን በሐዋሳ ከተማ ላይ ብቻ የተሞከረ የፖለቲካ ሥራ ልምምድ ነው:: በዚህ የተቻኮለና በሳል የፖለቲካ አመራር ሚና የሌለበት ውሳኔ ምክንያት ከ1995 .ም እስከ ምርጫ 97 .ም ድረስ በሲዳማ ሕዝብ ላይ የደረሰው በደል ፈጽሞ የሚረሳ አይደለም፤የሀዋሳን ከተማ መሬት ለመቀራመትና የከተማውን አስተዳደር ሥልጣን ለመሻማት የተጣጣሩ የክልሉ ሹማምንት ባለሥልጣናት በሲዳማ ህዝብ ዘንድ ፈተና የወደቁበት ተሞክሮ ነበር::ከአራቱም ማዕዘን ወደ ሀዋሳ ገበያ የሚገቡ የሲዳማ ሴቶች በጓሮአቸው አምርተው ያመጧቸውን ምርቶች ለሸማቹ ሕብረተሰብ ተረጋግተው መሸጥ እንዳይችሉ በማሰብ መደብር እንዳያገኙና ጀርባቸው ላይ ተሸክመው እያሉ ሸጠው ከተማውን ፈጥነው እንዲለቁ መደረጉ፣ በመዝናኛ ሥፍራዎችና በእህል ወፍጮ ቤቶች ሕብረተሰቡ ጎራ ለይቶ ወደ ግጭት እንዲገባ ግፊት መኖሩ፣ ከመዘላለፍ አልፎ ዱላ እስከ መሰናዘር መድረሱ፤
ብቸኛው በሲዳምኛ ቋንቋ ትምህርት የሚሰጥበትና በህዝቡ በጀት የተሠራው የቤተክህነት ትህምርት ቤት በሲዳምኛ ቋንቋ ለማስተማርም ሆነ ለመማር እንደማይገደድ ከሽግግር አስተዳደሩ ግልፅ ደብዳቤ በመፃፉ ቋንቋው አደጋ ላይ መውደቁ፣ በዚሁ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የነበሩ ግለሰብ ውሳኔውን በመቃወማቸው ብቻ ከሥራ ተፈናቅለው እንግልት እንድደርስባቸው መደረጉ፣ ይህም በሲዳማ ሕዝብ ዘንድ ውስጣዊ አመጽና ቁጣ መቀስቀሱ፣
በከተማው ውስጥ በሲዳምኛ ቋንቋ የተፃፉ ዋና ዋና መልዕክቶች ተነስተው በአማርኛ ቋንቋ ብቻ እንዲፃፉ መደረጉ፣
በሽግግር አስተዳደሩና በማዘጋጃ ቤቱ በሚሰጡ አገልግሎቶች የሲዳማ ተወላጅ ባይተዋር እንዲሆን መገፋቱ፣
ለሲዳማ መፈናቀል ከፍተኛ ሚና ይጫወቱ የነበሩ ወገኖች ለራሳቸው የሚመች ፖሊሲና መመሪያ በማዘጋጀት ቀደም ሲል ለሕዝብ መገልገያ ይሆን ዘንድ የተመረጠ Green Area እና ያልተመራ መሬት በአጭር ጊዜ ውስጥ በማከፋፈልና በመቀራመት የየራሳቸው ብሔረሰብ ጎሳ መንደር ስያሜ መስጠታቸው፣
የሲዳማን ተወላጅ ባገለለ አሠራር የየራሳቸውን ጎሳና ተወላጆችን በመመልመልና በማደራጀት ጥቃቂንና አነስተኛ ማህበራት በሚል ሰበብ ሲዳማ የብድር አገልግሎትና በከተማ ቦታ ተጠቃሚ እንዳይሆን የጠባብነት ሐዋሪያት መሆናቸው፣
የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ የሆነው ታላቁ አውደ ዓመት Fichee (ፍቼ) በዓል በተለይ በ1995 .ም እና በ1996 .ም ሐዋሳ ከተማ እንዳይከበር መደረጉና ይህም በሕዝቡ ዘንድ የከፋ የቁጣ ስሜት እንዲቀጣጠል የፖለቲካ አጀንዳ መሆኑ፣ እና ሌሎችም በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ለማካተት ያልተቻሉ ምክንያቶች የሕዝቡ ልብ ከኢህአዴግ እንዲሸፍትና ሌላ የመፍትሔ አመራጭ እንዲያፈላልግ አስገደደው:: ከላይ በተጠቀሱ መሠረታዊ ችግሮች ያኮረፈው የሲዳማ ህዝብ በምርጫ 97 ሙሉ በሙሉ ከኢህአዴግ ቁጥጥር ውጭ ሆነ:: የሲዳማ ህዝብ በቀዬውና በገዛ ከተማው በሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ መፈናፈኛ አጥቶ በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ የኢህአዴግን ጭንብል ለብሶ በደቡብ አቅጣጫ በተሰየመው ክልል እንደ እባብ በሚቀጠቀጥበት ጊዜ ሕገ መንግሥቱን መመርመርና ማገላበጥ ጀመረ:: ለካስ መፍትሔው ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ፍንትው ብሎ ተቀምጧል:: ይኸውም የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 እና አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 3 መሠረት የተደነገገውን ሕገ መንግሥታዊ መብቱን በመጠቀም ከታችኛው የአስተዳደር ዕርከን የቀበሌ ሸንጎ ጀምሮ ወደ ላይ እስከ ዞን ሸንጎ ድረስ ሕጋዊና ግልፅ ውይይትና ምክክር በማድረግ የመጨረሻ ውሳኔውን ሲዳማ ብሔራዊ ክልል የመሆን ጥያቄ በአንድ ድምጽ አጸደቀ:: በመቀጠልም በሕገ መንግሥቱ መሠረት ለክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ በጽሑፍ አቀረበ:: የክልሉ ምክር ቤትም አጀንዳውን ተቀብሎ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለሚሰጠው የብሔረሰቦች ምክር ቤት አስተላለፈ:: ከዚያ በኋላ የክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤትም ጥያቄውን ያለማወለወል በመቀበል ከላይ እንደተገለጸው የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጸጽ 47 ንዑስ አንቀጸ 3 መሠረት ጥያቄው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለጠየቀው ብሔር ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ ወሰነ:: የሲዳማ ሕዝብ ክልል የመሆን ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለውና ተገቢውን ሕጋዊ አካሄድ ተከትሎ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የደረሰ በመሆኑ ከሕዝበ ውሳኔ ውጭ ፈፅሞ ሊቀለበስ የማይችል ጉዳይ ነው በማለት ሁሉም ወገን የመረረው እንኳን ሳይቀር በፀጋ ተቀበለ:: በእርግጥም ጥያቄው የሲዳማን ሕዝብ በዕድሜ፣ በፆታ፣ በጎሳ፤ በኃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ ልጅ አዋቂ ሳይል ከዳር እስከ ዳር አንድ ያደረገ፣ እንዲሁም የተሟላ ስብዕና ያለው ብሔር ያሰኘ ታሪካዊና አግራሞትን የፈጠረ ጉዳይ ነው:: ይህ የሲዳማ ሕዝብ ራሱን ችሎ ክልል የመሆን ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በመደንገጉ ብቻ ሣይሆን ሕገ መንግሥቱ ከመፅደቁ ከ1987 .ም በፊትም ሕዝቡ ራሱን ችሎ ክልል ከመሆን መብት አልፎ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ወሳኝና ፍትሃዊ ውክልና ለማግኘት የሚያስችለውን እውቅና ለማረጋገጥ የተደራጀ የትጥቅ ትግል ያደረገና አሁን ላለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መፈጠርና ግንባታ ታሪካዊ የበኩሉን ሚና የተጫወተ የትግል አጋር ነው:: ከብዙ የትግል ውጣውረድ በኋላ ግን የጥያቄው ዋነኛ ምስሶና ማጠንጠኛ ብሎም ዋስትናው በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መረጋገጡ የሕዝቡ ክልል የመሆን መብት በሲዳማ ሕዝብ እጅ ውስጥ ብቻ ያለ የበሰለ እንጀራ በመሆኑ ባርኮ የመመገብ ጉዳይ የሲዳማ ሕዝብ ውሳኔ ነው:: በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ክብር አቶ መለስ ዜናዊ ከሲዳማ ሕዝብ ተወካይ ሽማግሌዎች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት የተናገሩትን እውነት እናስታውሳችሁ፤
ወቅቱ 1998 .ም ነበር:: የሲዳማ ሕዝብ ከላይ ለማብራራት እንደተሞከረው ከ1993 .ም መጨረሻ ጀምሮ በስሜ ተሃድሶ በየጊዜው የደረሰበትን የመብት አፈና መቋቋም ሲያቅተው፣ በክልሉ አንድነትና ሕብረት ሰበብ ያጋጠሙትን ፈተናዎች የግድ ለማለፍ ብዙ ከታገሠ በኋላ ሕገ መንግሥታዊ መብቱን ተጠቅሞ የክልል ጥያቄ በማቅረቡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የሲዳማ ሕዝብ ተወካይ ሽማግሌዎች ክልል የመሆን ጥያቄ በአስቸኳይ እንዲመለስለት የሲዳማ ሕዝብ እንደሚፈለግ አጥብቀው በጠየቁበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲመልሱ “የሲዳማ ሕዝብ ያቀረበው ክልል የመሆን ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ወይም ማንኛውም የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሚመልሰው ጥያቄ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በ1987 .ም በፀደቀበት ዕለት የተረጋገጠ መሠረታዊ መብት የመለሰው ጥያቄ ነው በማለት በሕገ መንግሥቱ መሠረት የሲዳማ ሕዝብ ቢፈልግ እንኳን ክልል መሆን ቀርቶ ራሱን የቻለ አንድ ነፃ ሀገር የመሆን መብት አለው” በማለት የምሥክርነት ማረጋገጫ ቃላቸውን ሰጥተዋል::ጉዳዩ ግን እስከዛሬም ታፍኖ በእንጥልጥል የቆየው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጊዜው የነበረውን ክልላዊ፣ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ የወቅቱን የፖለቲካ ሁኔታ ከሽማግሌዎቹ ጋር በመመካከርና በመገመገም የሲዳማ ህዝብ ለኢትዮጵያ መንግሥት የዝግጅት ጊዜ ወይም እይፎታ ጊዜ እንዲሰጠው ስለጠየቁ በባህሉ መሠረት ሽማግሌዎቹ ከሕዝቡ ጋር ለመመካከር ጊዜ የወሰዱ ቢሆንም ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄው ግን በሕገ መንግሥቱ ሥርዓት መሠረት ይፈታል እንጂ በጥቂት ግለሰቦች ምክክርና ድርድር ይሆናል ብሎ ማመን ሕገ መንግሥቱን መፃረር ነው:: ዳሩ ግን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 ንዑስ ቁጥር 3 መሠረት ጥያቄው ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ቀርቦ ተቀባይነት ስለአገኘና አፈፃፀሙንም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ጥያቄውን ላቀረበው ምክር ቤት ምላሽ መሰጠት የክልሉ ምክር ቤት ኃላፊነት በመሆኑ የሲዳማ ሕዝብ ክልል የመሆን ጥያቄ ከቀረበበት ጊዜ አንስቶ ህዝቡ ተግባራዊነቱን በጽኑ ያምናል እንጂ ባለሥልጣናት ወይም ግለሰቦች አመኑም አላመኑም፤ እውቅና ሰጡም አልሰጡም ሕገ መንግሥቱ ያረጋገጠው ጉዳይ ስለሆነ የሲዳማ ሕዝብ ራሱን ችሎ ክልል መሆኑን አረጋግጧል:: የሕዝቡን ክልል የመሆን ጥያቄ ተከትሎ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በአዲስ አበባ እና በሐዋሣ ከተሞች ሰፊና ተከታታይ ውይይቶችና ሽንገላዎች ከተገደረጉ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ በበኩላቸው የተወሰኑ ጊዜያዊ ምላሾችን ለመስጠት በገቡት ቃል ኪዳን መሠረት ውስን ነገሮች ተግባራዊ እየሆኑ ይገኛሉ::እነዚህም፤
ሕገ መንግሥቱ በሚያዘው መሠረት የሐዋሳ ከተማ አስተዳዳር የፖለቲካ ሥልጣን በዋናነት በሲዳማ ሕዝብ እጅ መሆኑ እየታወቀ ሥልጣኑን መሉ በሙሉ መልሰናል ማለታቸው፣
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሥልጣን በሲዳማ እጅ ተደርጓል መባሉ፣
በጭፍን አመለካከት የተስየመው የደቡብ ዩኒቨርሲቲ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ተብሎ እንዲታረምና ይህም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ለከፍተኛ የትምህርት ኮሚሽን እንዲተላለፍ መደረጉ፣
ለረዥም ዓመታት በገዛ ቀዬአቸው በሀዋሳ ከተማ ለገበያና ሌሎችም አገልግሎቶች ከገጠር የሚገቡ የሲዳማ እናቶች ያለ አንዳች መሸማቀቅና ፍርሃት በማንነታቸው ኮርተው መገልገል እንዲችሉ መደረጉ፣
የሲዳማ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ በመንከባከብ ያመጣውን የዘመን መለወጫ በዓል ፍቼ (Fichchee) በሀዋሳ ከተማ በሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ በሚገኘው ዞናዊ ጉዱማሌ ላይ ያለመከልከል እንዲያከብር የተነጠቀው መብቱ መመለሱ፣
በሀዋሳ ከተማ ውስጥ የሲዳማ ሕዝብ ማንነት የሚያንፀባርቁ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች Sidaamu Sumuda’ን ጨምሮ መሠራታቸው፣
የሲዳማ ሕዝብ የነፃነት ትግል ታጋይ የነበረው አቶ ወልደአማኑኤል ዱባለ መታሰቢያ ቋሚ ሀውልት በሐዋሳ ከተማ ወሳኝ ቦታ ላይ መሠራቱና በእኝህ ታዋቂ ታጋይ ስም የጎዳና ስያሜ መፅደቁ (Woldeamanuel Dubale Avenue) ቀደም ስል 10 ብቻ የነበሩ ወረዳዎች ቁጥር ሁለት የከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ወደ 21 አድገዋል መባሉ፣
ከሁላ መገንጠያ እስከ በንሣ ዳዬ ያለው አስቸጋሪ መንገድ ደረጃውን የጠበቀ አስፋልት እንዲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝቡ ቃል በመግባት እንደ አንድ የልማት ዕቅድ በአስተማማኝ በጀት እንዲደገፍ ለሕዝብ ተወካዮች አቅርበው ማፀደቃቸውና ሎሎችም መለስተኛ በጎ እርምጃዎች ሕገ መንግሥታዊ መብታችንን እንደ አዲስ ሥጦታ በማስመሰል ሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄ ለማዘገየት የተደረጉ ሽንገላዎች ናቸው::
ከላይ ከተብራሩት ነጥቦች መካከል የሲዳማ ዞን ወደ 19 ወረዳዎች ከፍ መደረጉ በራሱ እንደ አዎንታዊ ምላሽ ተደርጎ የሚወሰድ ቢሆንም በበጀት ምደባ ላይ አንዳች ለውጥ ባለመደረጉ ለጊዜው የሥራ አጥ ቁጥርን ከማስተንፈስ አልፎ ለካፒታል ፕሮጀክቶች በጀቱ ስለማይተርፍ ዞኑ በልማት እንቅስቃሴ ጎዳና ባለበት ሰልፍ እየረገጠ ይገኛል:: ከዚህ በተጨማሪ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው በአንደበታቸው በ1998 .ም ለሲዳማ ሕዝብ ቃል የገቡበት የበንሳ ዳዬ አስፋልት መንገድ እስካሁን ድረስ አለመጠናቀቁ ብቻ ሳይሆን ከደረጃው ወርዶ እነሆ በስደስተኛ ዓመትም ፈቀቅ ልል አልቻለም:: ውሳኔው በወቅቱ የነበረውን ሕዝባዊ ማዕበል ለማምለጥ ሲባል ብቻ የተደረሰ ሽንገላ መሆኑን ያመለክታል:: ምክንያቱም በሌሎች ክልሎች ወይም አካባቢዎች በተመሣሣይ ወቅት የተጀመሩ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክቶች በተሣካ መልኩ ተሠርተው ተጠናቀዋል ወይም ለአገልግሎት ተመርቀዋልና::
የሀዋሳ ከተማ ተጠሪነትና ሥልጣን በሕግ ማዕቀፍ ግልጽና በማያሻማ ሁኔታ ለሲዳማ ህዝብ ስላልተመለሰ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ለህዝባችን ራስ ምታትና የሥጋት አጀንዳ እየሆነ መምጣቱና ይህን ክፍተት በመጠቀም ሲዳማን ለማጥቃት የሚፈልጉ ኃይሎች በወቅቱ ለሽንገላ የሚመቹአቸውን የብሔሩን ልጆች የፖለቲካ ብስለት ማነስ ተጠቅመው የመረማመጃ ድልድይ በማድረግ በየጊዜው የከተማውን አስተዳደር የሙከራ ጣቢያ አድርገውታል::
ሀዋሳ ለሜትሮፖሊታን የታጨች ብቸኛ ከተማ
እንግዲህ ሜትሮፖሊታን የሚለው ፅንሰ ሐሳብ ለአገራችን አዲስ ቢሆንም በዚህ ስም ለመጠራት የመጀመሪያውን የሙከራ ዕድል ያገኘች ከተማ ሀዋሳ እንደሆነች ሰምተናል:: በዓለም ደረጃም ቢሆን በሜትሮፖሊታን ስያሜ የሚጠሩ ከተሞች እጅግ ውስን እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ:: ታዲያ ይህ ብዙም ያልተለመደና አዋጭነቱ በአገራችን ያልተፈተነ አዲስ “የልማት ስትራቴጂ” 
እንዴት ለሀዋሳ ከተማ ተመረጠ?
ከሁሉም የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል ሙሽሪት ሀዋሳ የተመረጠችበት መስፈርትስ ምንድር ነው?
አጀንዳውን የቀረፁና የጠነስሱ የፖለቲካ ምሁራን እነማን ነበሩ?
ማንንስ ይወግናሉ? በማን አማካይነት ለማስፈጸም ጥረት ያደርጋሉ?መልሱን ለእነዚያ ወገኖች እንተወዋለን:: ለማንኛውም ከዚህ አጀንዳ ሳንወጣ አንድ ሁለት ነገር እንበል:: የክልሉን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአንድ ቀጭን ገመድ በማሰር ወይም በአንዲት መለስተኛ ቅርጫት ውስጥ እንደ ዶሮ ጫጩት በማጨቅ እንደ ሰሌሜ ጨዋታ እየመራ ያለው ደኢህዴን በዚህ ዓመት መገባደጃ ላይ ከያዛቸው ዕቅዶች ዋነኛው የሀዋሳ ከተማ አስተዳደርን ማተራመስ መበደኛ ሥራው መሆኑን በተግባር አረጋገጠ:: ምክንያቱም ለደኢህዴን መጠናከር የሲዳማ ሕዝብ አለመረጋጋትና ከሀዋሳ ከተማ እንዲለይ ማድረግ እንደ ትልቅ ቁልፍ ስልት ተደርጎ በመወሰዱ ይኸው ሙከራ ቀጥሎ እነሆ ከአሰርት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል:: ይህ በሲዳማ ህዝብ ላይ የተደገሰው ክፉ አጀንዳ እነሆ 10 ዓመቱን ቆጥሮ ህዝባችንን እያመሰው ይገኛል::በምኒሊክ ዘመነ መንግሥት ልዑልሰገድ ሲዳማን በከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲው አንድነቱን እንዳናጋው ሁሉ ዛሬ ላይ ደግሞ የኢህአዴግን ጭንብል ለብሰው በስሜ ደኢህዴን እንደሞግዚት ህዝቡን ሲመሩ የነበሩ የሕወሓት ታጋዮች በ19ኛው ክፍለ ዘመን ወደኋላ የቀረውን የከፋፍለህ ግዛን አሠራር በመጠቀም ድብቅ ዓላማቸውን ለማስፈጸም ሌትተቀን ተግተው በመሥራት የሲዳማን ህዝብ ህሊውና ተፈታትነዋል:: የትኛውን ብሔር ወይም ህዝብ እንደወከለ በውል የማይታወቀው የደኢህዴን አደረጃጀት ከፍተኛ አመራሮች እንደሚሉት የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ለውጥ ያስፈልገዋል፣ የማስተዳደሩን ሥልጣን ከሲዳማ እጅ አውጥቶ ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በኮታ ማከፋፈል ይገባል በሚል ሥውር ሽፋን ጊዜ ያለፈበትን ስልት እየተጠቀሙ እንደሚገኙ ለማንም የተሰወረ አይደለም:: ይሁን እንጂ እንደ ድሪቶ ጨርቅ የተወሰወሰው የክልሉ አወቃቀር በየጊዜው እየተበታተነ ፎርጂድ (Forgery) ተደርጎ የተዋቀረውን የክልሉን አንድነት ከማፈራረስ አልፎ ኢህአዴግም ራሱን ቆም ብሎ እንዲያስብ አስገድዶታል::
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የደኢህዴን ከፍተኛ አመራሮች የሀዋሳን ከተማ ሜትሮፖሊታን ለማድረግ ያነሣሣቸው ምክንያት እነርሱ ራሳቸው ባቀረቡት መነሻ ጽሑፍ ውስጥ እንዳበራሩት፤
የሲዳማ አመራሮች በሙስና ተዘፍቀዋል፣ 
በኪራይ ሰብሳቢነት አዙሪት ውስጥ ወድቀዋል፣
ከተማዋ የልማት እጦት ገጥሟታል፣
በከተማው መልካም አስተዳደር አይታይም፣
የሲዳማ ተወላጆች የማስተዳደር ብቃት የላቸውም፣
የተማረ የሰው ኃይል የላቸውም፣
ተጠቃሚውና ተሿሚው የሲዳማ ተወላጅ ብቻ ነው የሚሉ እና ሌሎች ነጥቦችን ለመደርደር ሞክረዋል::ይኸው ጽሑፍ በሌላ መልኩ የሀዋሳ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ በልማት እያደገችና ከኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ሁለተኛ የአገሪቱ ዋና መናገሻ ትሆናለች፣ የተፈጥሮ ገፅታ ከለገሳት ውበት በተጨማሪ መንግሥት ለከተሞች እድገት የሰጠውን ልዩ ትኩረት በመጠቀም የሀዋሳ ከተማ የብዙ ኢንቨስተሮችንና እንግዶችን ቀልብ የመሳብ አቅም አግኝታለች፣ከተማችን ሀዋሣችን ወዘተ የሚሉ እርስ በርስ የሚጋጩ ተቃራኒ ሀሳቦችን ያትታል:: በየ10ኛ ዓመቱ ማለትም በ1984 ዓም፣ በ1994 ዓም ዛሬም በ2004 ዓም በሲዳማ ሕዝብ ላይ እየተደገሰ የሚቀርብለት የጥፋት አጃንዳ ዓለማውና ግቡ ምንድር ነው?ያም ሆነ ይህ ስለሜትሮፖሊታን ትርጉምና በሀዋሳ ከተማ ስላለው ዕቅድ የደኢህዴን ባለሥልጣናት ሲመልሱ “ሜትሮፖሊታን ማለት የመንግሥት የልማት አቅጣጫ ሲሆን ሀዋሳ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ዙሪያውን እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ሊያካልል የሚችል መሠረት ይዞ ከሐዋሳ ከተማ አንስቶ እስከ ዶንጎራ ቀበሌ አለታ ጩኮ ወረዳ ድረስ ርዝማኔ ያለው ሆኖ ስፋቱ ግን የተባለው የሕዝብ ቁጥር እስኪረጋገጥ ድረስ ይለጠጣል ማለት ነው” ብለዋል:: ዓላማውም አከባቢውን የኢንዳስትሪና የቱሪዝም ማዕከል በማድረግ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ አቅም ማፈርጠም እንደሆነ ተናግረዋል:: ምንም እንኳን የመንግሥት የልማት ፖሊሲ አቅጣጫ የሚደገፍ ቢሆንም አሁን እየታሰበ ያለው ሀዋሣን ሜትሮፖሊታን ከተማ የማድረጉ ዓላማ የሲዳማን ሕዝብ የሚጠቅም ሣይሆን ይልቁንም ለረጅም ጊዜ ጠብቆ ያቆየውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሥነ ልቦናዊ አንድነቱን የማናጋትና የማፍረስ (Dis-integrate) ሚና እንዳለው አበክረን ልናስገነዝብ እንወዳለን:: የሀዋሣ ከተማ አሁን ካለበት ደረጃ በተሻለ ሁኔታ በልማት ወደፊት እንድቀጥልና ይበልጥ በጎ ገፅታ እንዲላበስ ከተፈለገ አሁን ባለበት ሁኔታ ማሣደግ ይቻላል:: በየማዕዘኑ የሚገኙ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ደሣሣ የቀበሌ ጎጆ ቤቶች ተነስተው መሥራት ለሚችሉ ባለሀብቶች መስጠትና የከተማውን ውብት የሚያጎሉ ሕንፃዎች ወይም አገልግሎት መስጫ ተቋማት መገንባት ይቻላል:: ከዚህም በተጨማሪ በከተሞች ዕደገት ሕግ መሠረት ማንም ከይዞታው ሳይፈናቀል ወደላይ Vertically ማሣደግም ይቻላል::
ይበልጡንም በአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ የተካተቱ የመንግሥት ዋነኛ ልማት አጀንዳዎች ላይ አነጣጥረን እየተጓዝን ባለንበት በአሁኑ ሰዓት አዋኪ አጀንዳዎችን በመቅረጽና ሕዝቡን በማንጫጫት ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ምክንያት መሆን ለምን አስፈለገ? የሲዳማ ሕዝብ ነውጠኛ ወይም ሽብርተኛ ሣይሆን ልማት ናፋቂ፣ እንግዳ አክባሪ፣ ለመንግሥት ታዛዥ፣ እንዲሆም ለሕገመንግሥቱ ተገዢ የሆነ ሆደ ሰፊ ሕዝብ ነውና:: ስለዚህ ገና ለአገራችንም ሆነ ለአህጉራችን በጣም አዲስ በሆነ ጽንሰ ሐሳብ የሐዋሳን ከተማ ሜትሮፖሊታን ከተማ እናደርጋለን በሚል እጅግ የተቻኮለ አጀንዳ መንግሥትና ሕዝብ እንዲቃቃር ማድረግ ለምን አስፈለገ? እኛ ያመጣነው አጃንዳ ተግባራዊ ካልሆነ ሞተን እንገኛለን፣ ሲደማ ክልል የሚሆነው በደኢህዴን መቃብር ላይ ነው እያላችሁ ለምን ህገ መንግሥታዊ መብቱን ትንዳላችሁ? የተለያዩ የብዙሃን መገናኛዎችን በመጠቀም የሲዳማን ህሊውና በሚጎዳ መልኩ የሚትነዙትን ሚዛኑን ያልጠበቀ መሠረቱንም የሳተ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ መንዛት አስፈላጊ ነውን? የህዝቡን ዕውቅና ያላማከሉ ግለሰቦችን በየጊዜው ከየወረዳው በማምጣት በገንዘብ የመሸንገል ዘመቻ ለምን ታሰበ? እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል እንዲሉ አታውቁምን? ኃይልን ከመጠቀም ይልቅ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የአስተዳደር ጥበብ ሆኖ እያለ ይህንን ዘዴ ተግባራዊ ማድረግ እንዴት ተሳናችሁበአጠቃላይ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደተሞከረው የሲዳማ ሕዝብ በኢህአዴግ ሥርዓት የተለያዩ ድሎችን ተቀዳጅቷል:: የሲዳማ ብሔር ከአስከፊው ብሔራዊና መደባዊ ጭቆና ተላቆ በብሔራዊ ማንነቱ ላይ የተጋረጡ የእኩልነት ማነቆዎችንም አስወግዶ ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሔርች፣ በሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ላይ በተመሠረተ መርህ በመከባበር፣ በመፈቃቀድና በሠላም አብሮ የመኖር ሕይወት ማጣጣም የጀመረ ከመሆኑም በላይ አንዲት ጠንካራ አገር ለመገንባት በሚደረገው ዘርፈ ብዙ ትግል ውስጥ የበኩሉን ሚና በመጫወት ላይ ያለ ክቡር ሕዝብ ነው:: ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሊሆን የሚችለው በቅርቡ የተደረገው የአባይ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያደረገው አገራዊ ተሳትፎ ከብዙ በጥቂቱ ለአብነት የሚጠቀስ ተግባር ነው:: ይህ ሁለንተናዊ የሲዳማ ህዝብ ድጋፍ በደቡብ ክልል ከተደረገው አጠቃላይ ተሳትፎ እጅግ የላቀ ከመሆኑም በላይ በአገሪቱም ደረጃ ጉልህ ድርሻ ይዟል::
የሲዳማ ብሔር በአሁኑ ጊዜ ሁለት መሠረታዊና ቁልፍ ጥያቄዎች እንዲመለሱለት አጥብቆ ይፈልጋል::
1
. የሲዳማ ብሔር ራሱን ችሎ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለመሆን የሚያስችለው 
ሕገ መንግሥታዊ የመብት ጥያቄ፣
2
. የሲዳማ ህዝብ ህገ መንግሥታዊ የመደራጀት መብትን ተጠቅሞ የሚመሠርተው 
ብሔራዊ የፖለቲካ መሪ ድርጅት እንዲኖረው ይፈልጋል፣
እነዚህ ከላይ የተቀመጡ ወሳኝና አንገብጋቢ ጥያቄዎች በዋናነት እንደተጠበቁ ሆነው በህዝቡ ዘንድ ለረጅም ጊዜ እንቆቅልሽ ሆነው ሳይመለሱ የቆዩ የሲደማ ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ ፣ የጥናትና ምርምር ማዕከል ግንባታ፣ እንዲሁም በዞኑ ውስጥ የሚገኙ የልማት ተቋማት በአስተማማኝ መልኩ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ተጠናክረው ህዝባችንን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆን ይገባቸዋል የሚለው የህዝቡ ጥያቄ በአስቸኳይ እንዲመለስ ይፈልጋል::እንደሚታወቀው መሪ የፖለቲካ ድርጅት የሌለው ሕዝብ ትክክለኛ የትግል አቅጣጫ መከተል ስለማይቻለው አቅጣጫ የሚጠቁም ኮምፓስ እንደጠፋበት መርከብ ወደተሣሣተ አቅጣጫ እና ወደማይጠቅም ድምዳሜ መጓዙ አይቀርም:: ስለዚህ የሲዳማ ህዝብም እንዲታመስ ያደረገው አንዱና ዋነኛ መንስኤ እየመራ የቆየው የፖለቲካ ድርጅት ሲህዴድ ባልታወቀ ምክንያት ደብዛው ጠፍቶ መሪ አልባ ሊሆን በመብቃቱ ነው:: ሕዝቡ መሪ የፖለቲካ ድርጅት የለውም ሲባል በአገር ደረጃ ያለውን ኢህአዴግን የሚመለከት ሣይሆን ለብሔር ብሔረሰብ በተሰጠው ሕገ መንግሥታዊ የመደራጀት መብት መሠረት እንደ ብሔር ድርጅቶች ሕወሓት፣ ብአህዴን፣ ኦህዴድ እንደተባለው የሲዳማ ሕዝብም የራሱ የፖለቲካ ድርጅት ያስፈልገዋል በሚል ፅኑ አቋም መሆኑ ግልፅ ሊሆን ይገባል:: በመጨረሻም እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ ሁለት መሠረታዊና ቁልፍ የሲዳማ ጥያቄዎችን መመለስ የኢትዮጵያ መንግሥት በከፍተኛ የሕይወት መስዋዕትነት ያጸደቀውን ሕገ መንግሥት ማክበርና የሲዳማ ሕዝብ ለደርግ ሥርዓት መውደቅ፣ ብሎም ለኢህአዴግ ሥርዓት መገንባት ላበረከተው ከፍተኛ የትጥቅ ትግል ዋጋ መስጠቱን ያረጋግጣል::
የሲዳማ ህዝብ ጥያቄዎቹ እንዲመለሱለት የሚከተላቸው ስልቶች
አካሄዳችን ምንጊዜም እግዚአብሔርን የሚያስቀድም፣ እውነትን የሚያስረግጥና የሰላምን መንገድ የሚከተል በመሆኑ የህዝቡን ሠላምና ፀጥታ የሚያናጋ ተግባር በማንኛውም ሁኔታ እንዳይከሰት ብርቱ ጥንቃቄ በማድረግ ሁከትና ብጥብጥን ማስወገድ፣
ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ጋር ሠላማዊና መልካም መግባባትን የተላበሰ ግንኝነት መፍጠር፣ ኢ-ህገ መንግሥታዊ ተግባር አለመፈጸም፣
በግለሰቦች ማንነት ላይ ያነጣጠረ ጊዜ ያለፈበት የጥላቻ ፖለቲካ አለማካሄድ፣ ጎሳን፣ጎጥን፣ ዘርን፣ የፖለቲካ አመለካከትን፣ፆታን፣ ሐይማኖትን፣ መሠረት ያደረገ አካሄድ አለመከተል፣
በየትኛውም የኃላፊነት ዕርከን ላይ የሚገኝ ባለሥልጣን የሕዝቡን ውክልና የያዘ በመሆኑ በመታዘዝ መንፈስ ማክበርና መደማመጥ፣ ከተቻለም መተማመን፣
ከሲዳማ ህዝብ እኩል መደባዊ ጭቆና ያረፈባቸውን ማንኛውንም ህዝብ በጭፍን አመለካከት አለመፈረጅ፣ የራስን ሰብአዊ መብት ለማስከበር ጥረት እንደሚደረግ ሁሉ የሌላውንም ክብር አለመንካት፣ ሠላማዊ ሕይወቱን አለማወክ፣ 
ማንኛውም የግልም ሆነ ህዝባዊ ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የተከተለ እንዲሆን ጥረት ማድረግ፣
የሲዳማ ባህላዊ ሸንጎ (Affini-Wo’mitini Seeru Songo) በሀዋሳ ከተማ ጉዱማሌ ላይ ማድረግና ባህላዊ ሥርዓቱን በተማከለ መልኩ እንደገና ማጠናከር፣ይህ መልካም ባህል ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር መጣር፣
በየትኛውም ደረጃ ያሉ የሲዳማ አመራር አካላትም የሕዝቡ ጥያቄ የጋራችን በመሆኑ ባለፉት 15 ዓመታት በሲዳማ ውስጥ የነበረው የጥሎማለፍ ፖለቲካ እንዲወገድ፣ የእርስበርስ ሽኩቻና መወነጃጀል እንዲቀር ማድረግ፣
ብቃትን መሠረት ያላደረገ ምደባና ሹመት በተለያየ ተልካሻ መስፈርት አለማካሄድ፣
ማስታወሻ ለአንዳንድ ወገኖች!እናንተም እንደሚታውቁት የሲዳማ ሕዝብ እንግዳ ሰው አክባሪ፣ ሠላማዊና የፀጥታ ችግር በሚኖር ጊዜ እንኳን አስተማማኝ መረጋጋት የሚታይበት፣ ለራሱ ተወላጅ ከሚሰጠው ክብር ይልቅ ለመጤው ሕዝብ ቅድሚያ ክብር የሚሰጥና የሚሳሳ ፈርሃ-እግዚአብሔር ልብ ያለው በAffini-Wo’mitini Seera ሥርዓት የሚተዳደር ሕዝብ ነው:: ስለዚህ ህዝቡ ተገቢ ያልሆኑ ጫናዎች ስደርሱበት የመብት ጥያቄ ባነሣ ቁጥር ወደተሳሳተ ድምዳሜ አትድረሱ፣
እባካችሁ የሲዳማን ሕዝብ ታሪካዊ አመጣጥና ከህዝቡ ጋር ለረዥም ጊዜ በሰላም አብሮ መኖራችሁን ዘንግታችሁ ህዝባችንን ዘራፊ፣ ሌባ፣ ሁከትና ሽብር ፈጣሪ፣ ለሕዝብ ሠላምና ፀጥታ አስጊ አድርጋችሁ አትቁጠሩት፣ ከባለሥልጣናቱ ጋርም ከበሮ አትደልቁ፣ ይልቁንም የሲዳማ ሕዝብ የመብት ጥያቄዎች እንዲመለሱ ድጋፋችሁንና አጋሪነታችሁን በእውነት እና በማስተዋል አረጋግጡ::
ማጠቃለያ፤
ከላይ እንደተጠቀሰው ለዚህ ጽሑፍ መሠረታዊ መነሻ የሆኑትን ሁለቱን የሲዳማ ብሔር ቁልፍ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎች ማለትም፣

1
. የሲዳማ ብሔር ክልላዊ መንግሥት የመመሥረት ጥያቄ፣
2
. የብሔሩ መሪ የፖለቲካ ድርጅት የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት ተግባራዊ 
እንዲደረግ ኢህአዴግ፣ የተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 
የተጣለባቸውን ህዝባዊና ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነት እንዲወጡ አጥብቀን 
እንጠይቃለን:: 


Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር