የትናንቱ ጐዳና ተዳዳሪ የዛሬው ብሔራዊ ቡድን ፈርጥ



በደረጀ ጠገናው
ብራዚል ለዛሬው የእግር ኳስ ስፖርቷ፣ ክብሯንና ማንነቷን የገነባችው ትናንት ከየጐዳናውና ጉራንጉሩ ትመለምላቸው በነበሩ የኳስ ፈርጦቿ አማካይነት መሆኑ የአደባባይ ሚስጢር ነው፡፡
ከእነዚህ የምንግዜም ዝነኛ የኳስ ክዋክብት መካከል ጋሪንቻና ሌሎችም በርካታ ቁጥር ያላቸው ብራዚላውያን ታዳጊዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ገና በለጋ ዕድሜያቸው የሕይወት ውጣ ወረድ ገፈት ሊጋፈጡ የተገደዱት ጋሪንቻና ሌሎቹም የቱንም ያህል እግር ኳስን ቢወዱም፣ የቱንም ያህል ችሎታና ክህሎቱ ቢኖራቸውም በተለይ ጋሪንቻ ‹‹እግረ ደጋን›› እየተባለ ፈላጊ አልነበረውም፡፡ እግሩ ያነክሳልና ለእግር ኳስ አይመጥንም እየተባለ ብዙ ተንከራቷል፡፡

የኋላ ኋላ ግን የኳስ አምላክ ትክከለኛውን የኳስ ግጣም አገናኘና ጋሪንቻ በብራዚል ሜዳዎች ብቻ ሳይሆን በዓለም ዋንጫ መድረኮች ሁሉ ገነነባቸው፡፡ እንደ ጋሪንቻ ሁሉ ሌሎችም ከብራዚል ጐዳናዎች የተገኙ የእግር ኳስ ጠበብት ሮናልዶ ናዛሪዮ ሊዊስ ዴሌማ፣ ሮናልዲኒሆ ጐቹን ጨምሮ ለዓይን የሚታክት በርካታ ፈርጦች ልጥቀስ ይቻላል፡፡

ለመነሻ ያህል ስለብራዚላውያን የጐዳና ፈርጦች አወሳን እንጂ ልናወራ ያሰብነው፣ የኢትዮጵያ ጐዳናዎችም የጨርቅ ኳስን ከእግራቸው አፋቅረው የመንገደኞችን ቀልብ እየገዙ ኳስን የሚያንከባልሉ ጥቂት አይደሉምና የምንለውን ለማለት ነው፡፡

በርካቶች ግን ፈላጊ እያጡ ችሎታቸውን አይቶ ተገቢ ቦታ የሚሰጣቸው ባለማግኘታቸው እየደበዘዙ ሲጠፉ ቆይተዋል፡፡ በዚህ ዘመን ግን አንድ ያልተጠበቀ ጮራ በድንገት ፈንጥቋል፡፡ አስገዳጁና እንዲያም ሲል በጐዳና የጨርቅ ኳሶች ላይ ሲሾሩ የቆዩት የታዳጊ ወጣት እግሮች ቦታቸውን እንዲያገኙ ግድ ብሏል፡፡ በአሁኑ ጊዜም የአገርን ባንዲራ አስከብረው የባላንጣ ውጋት እየሆነ እግሮቹ ምትሀት እያሳዩ ይገኛሉ፡፡ ከነዚያ እግሮች የታዳጊ ወጣት ታዲዮስ ተሰማ ይጠቀሳል፡፡

ታዳጊው በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ 03 ይወለድ እንጂ እንደ ሰፈሩ ልጆች የወላጆቹን ቁጥጥርና እንክብካቤ ግን አላገኘም፡፡ ወላጅ አባቱን በሞት የተነጠቀው ወላጆቹን መለየት በማይችልበት በጨቅላ ዕድሜው ነው፡፡ እናቱም ቢሆኑ የአባቱን እግር ተከትለው ወደ ማይቀረው ዓለም ያመሩት ብዙም ሳይቆዩ ስለመሆኑ ያስረዳል፡፡

ሕፃን ታዲዮስ ቀጣይ ዕጣ ፈንታውን መወሰን በማይችልበት ሁኔታ ለአሳዳጊ ተላልፎ እንዲሰጥ ግድ ብሎታል፡፡ ታዲዮስ በአሳዳጊው እጅ እያለ ቆይቶ እንደሰማው ወላጅ አባቱ ከመሞታቸው በፊት ከወላጅ እናቱ ጋር ተለያይተው በመሀል በትዳር የያዟቸው ሴት ወይዘሮ ነበሩ፡፡ አባቱ ከእኚሁ ወይዘሮ ሴቶችን  ያፈሩ ነበሩ፡፡ ታዳጊው ከአባቱ ካገኛቸው እህቶቹና እንጀራ እናቱ ጋር ብዙም ሳይቆይ የጐዳና ሕይወትን ለመጀመር እንደተገደደም ያስረዳል፡፡

የጐዳና ሕይወትና እግር ኳስ
የጐዳና ሕይወትን እየመራ በሚያገኘው ትርፍራፊና ልቅምቃሚ እየታገዘ ትምህርቱን እስከ 7ኛ ክፍል እንደተማረ የሚገልጸው ታዳጊ ታዲዮስ፣ የሁኔታዎች መለዋወጥና በተለይም ከሕፃንነቱ ጀምሮ ለእግር ኳስ ባለው ፍቅር ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገዷል፡፡ ሒደቱን ሲገልጸውም ‹‹የጐዳና ሕይወትና ትምህርትን አጣጥሞ መሔድ በጊዜው አዳጋች ሆኖብኝ ለማቋረጥ ተገደድኩ፤›› ይላል፡፡

ያም ሆኖ የሚለው ታዳጊው፣ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች ዘወትር በጐዳና ላይ ከጨርቅ ኳስ ጋር የነበረውን ቁርኝት ይከታተሉ ስለነበረ፣ እግር ኳሱንም እንደትምህርቱ አቋርጦት እንደ ሌሎቹ የጐዳና ባልደረቦቹ ለተለያዩ ሱሶች ተገዥ እንዳይሆን ከተማሪዎች የሚተርፈውን ምግብ ያለስስት ለእሱም ለጓደኞቹም መስጠታቸው አግዞታል፡፡

‹‹የጐዳና ባልደረቦቼ አንዳንዶቹ ጫትና ሲጋራ ይዘው በየጥጋጥጉ ሲቀመጡ እኔና ጥቂት የሰፈር ልጆች ባህር ዳር መስቀል አደባባይ እየሔድን ኳስ ስናንከባልል እንውላለን፤›› የሚለው ታዳጊ ታዲዮስ ይህንኑ ፍላጐቱንና ምኞቱን የረዱት የጐዳና ባልደረቦቹ እንደሚያከብሩለት ይናገራል፡፡ እንዲያውም ይላል ታዳጊው፣ ‹‹አብረን የጐዳና ሕይወትን ከምንኖረው በርካታ ታዳጊዎች አብዛኛዎቹ እኔ ለእግር ኳስ ያለኝን ፍቅርና ፍላጐት ስለሚያውቁ እነሱ ሱሰኛ የሆኑባቸውን እንደ ጫትና ሲጋራ የመሳሰሉትን እንዳልላክ፣ የሚልከኝም ካለ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ከጐዳና ማኅበር እንዲሰናበት አቋም የያዙ ናቸው፤›› ሲል የጐዳና ጓደኞቹ በእሱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ የነበራቸውን እምነት ነግሮናል፡፡

እንዲህ እያለ የጐዳና ሕይወትን ሲመራ የቆየው ታዲዮስ፣ የእግር ኳስ ቆሌ ከእሱ ነበረችና በባህር ዳር ቀበሌ 04 አካባቢ ታዳጊዎችን እየመለመለ ያሠለጥን የነበረው ያሬድ ዘነበ በአንድ አጋጣሚ ተመልክቶት ምንም ጥያቄ ሳያቀርብለት ከሚያሠልጥናቸው ልጆች ጋር እንዲቀላቀልና መሠረታዊ የእግር ኳስ ክህሎትን እንዲቀስም ዕድል እንደሰጠው ይናገራል፡፡

‹‹በወቅቱ አጋጣሚውን መጠቀም የማንም ሳይሆን የእኔ መሆኑን ስለተረዳሁ ለእግር ኳስ የነበረኝ ተነሳሽነት በእጥፍ ሲያድግ ይሰማኝ ነበር፤›› ሲል የጐዳና ሕይወት ውጣ ውረዶችን የተረከልን ታዳጊው፣ በመሀል የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ካቋቋማቸው 24 ፕሮጀክት ጣቢያዎች አንዱ በባህር ዳር ይገኝ ስለነበረ በፕሮጀክቱ ለመታቀፍ ጊዜ አልወሰደበትም፡፡

ከባህር ዳር ጐዳና እስከ አዲስ አበባ
በአሁኑ ወቅት በአውሮፓና በሌሎችም አገሮች ለምንመለከታቸው የእግር ኳስ ፈርጦች ምንጩ ፕሮጀክትና ፕሮጀክት ብቻ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ የፕሮጀክት ጽንሰ ሐሳብ በኢትዮጵያ በወረቀት ደረጃ ቢታወቅም፣ ነገር ግን መሬት ላይ መውረድ ባለመቻሉ የአገሪቱ እግር ኳስ የጀማሪ መጨረሻ ለመሆን የተገደደበት ዘመን ላይ ደርሷል፡፡ ከባህር ዳር ከተማ የጐዳና ሕይወት የተገኘው ታዳጊ ታዲዮስ፣ ለአገሪቱ እግር ኳስ ውድቀት ዕቅዶች የአጭርና የረጅም ተብለው ስላልተገበሩ እንጂ በእግር ኳስ ክህሎት ያበዱ፣ ነገር ግን ተመልካች ባለማግኘታቸው ከወላጅ ጋር የሚኖሩ ብቻ ሳይሆን ልክ እንደእሱ በጐዳና የሚኖሩ በርካታ ስለመሆናቸው ያምናል፡፡ የኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ያሬድ ቶሌራም የታዳጊውን አባባል ይጋራል፡፡

ስለፕሮጀክትም ሆነ ስለእግር ኳስ የዘርፉ ሙያተኞች፣ ‹‹ሙያን ለባለሙያ›› የሚሉት አባባል ሳይገባው ይሁን አውቆ የተኛ . . . እንደሚባለው ለዓመታት ጆሮውን ነስቶት የቆየው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ካለፈው የውድድር ዓመት ጀምሮ ግን ስለታዳጊ ፕሮጀክት ማውራት ይዟል፡፡ ከማውራትም በላይ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በውድድር ዓመቱ ለሚያከናውነው ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ታዳጊዎች ሻምፒዮና፣ የአህጉሪቱን አገሮች እያሳተፈ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያም ከእነዚሁ አንዷ ናት፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሸን ለዚሁ ሻምፒዮና እንደቀደሙ ዓይነት ጢማቸውን በቶፓዝ ፈግፍገው የቀረቡት ሳይዝ ከየክልሉ በሙያተኞች የተመለመሉ ታዳጊዎችን በማሰባሰብ ከእነዚያ የተሻሉትን በመምረጥ ነው ተሳትፎውን አንድ ብሎ ጀምሯል፡፡ ይበል የሚያሰኝ ስለመሆኑም መግለጽ እንወዳለን፡፡

በዚሁ ቅኝት ወደ ባህር ዳር ያመሩት መልማዮች አነሳሳቸው መልካም ነበርና በክልሉ ፕሮጀክቶች ከታቀፉት ታዳጊዎች፣ ታዳጊ ታዲዮስን አይተው ተሰጥዎውና ክህሎቱን ማድነቅ ብቻ ሳይሆን የዕቅዳቸው አካል ለማድረግ አላቅማሙም፡፡

የእግር ኳስ ቆሌና የታዲዮስ ዕጣ ፈንታ የገጠማቸው ታዳጊዎች፣ አዲስ አበባንና ድሬዳዋን ጨምሮ ከሁሉም ክልሎች ተመልምለው ወደ አዲስ አበባ፣ ከዚያም ወደ አዳማ እንዲጓዙ ተደርጐ በአጠቃላይ ወደ 80 የሚጠጉ ታዳጊዎች የባህር ዳሩን የጐዳና ወጣት ጨምሮ በፌዴሬሽኑ ሙሉ ወጪ ምርጫ ተደርጐ የዛሬው የኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ለመዋቀር በቃ፡፡

ብዙ ጊዜ ስለአካዴሚዎችና ፕሮጀክቶች ሲታሰብ ቀድሞ የሚቀርበው መሰናክል ‹‹አቅም›› እንደሆነ የሚናገረው ታዳጊው፣ ፍላጐቱና ተነሳሽነቱ ካለ የጐዳና ልጆችን ጨምሮ በየሠፈሩ ለሚገኙ ታዳጊዎች ሸራ ጫማና ጥርጊያ መዘውተሪያ ሥፍራ ይበቃል፡፡ መሠረታዊ የእግር ኳስ ክህሎቶችን ለማግኘት ነገሮችን በሒደት ማሟላት እንደሚቻልም ይገልጻል፡፡

በዋናነትም የጐዳና ሕይወትን የሚመሩ ታዳጊዎች ሙሉ በሙሉ የተበላሹ አድርጐ መውሰድ ስህተት መሆኑን የሚያስረዳው ታዲዮስ፣ ይልቅስ እነዚያ ታዳጊዎች የኅብረተሰቡ አንድ አካል ተደርገው ቢታዩ በሒደት አገሪቱን ሊጠቅሙ የሚችሉ ተተኪዎችን ማግኘት እንደሚቻል ያስረዳል፡፡ ‹‹ለዚህ ሩቅ መሔድ ሳያስፈልግ በእርግጥ ብዙ የሕይወት ውጣ ውረድ እንደሚጠብቀኝ ባምንም መንገዱን ጀምሬዋለውና የእኔ ተሞክሮ ማስረጃ ነው›› ይላል በጐዳና ልጆች ላይ ያለውን እምነት ሲያስረዳ፡፡

ከ16 ዓመት በኋላ አባት ማግኘት
ታዳጊው በጐዳና ሕይወት በነበረበት ወቅት ከትምህርት ይልቅ ትኩረቱ ለእግር ኳስ ስለመሆኑ አሁን የሚገኝበትን ሁኔታ በመመልከት መልሱን መገመት አያዳግትም፡፡ ይህንኑ ተከትሎም ይመስላል ታዳጊውና ትምህርት ቁርኝታቸው ከሰባት መዝለል ያልቻለው፡፡

ይሁን እንጂ ዕድልና የእግር ኳስ ቆሌ የከፈቱትን በር የሚዘጋው አይኖርምና ታዳጊው ታዲዮስ ተሰማና ትምህርት እንደገና ሊቆራኙ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ መንገዱም የተመቻቸ ይመስላል፡፡ ታዳጊው ትምህርቱን ብቻ ሳይሆን፣ በጨቅላ ዕድሜው ያጣውን የወላጅ ፍቅር ማግኘት ይችል ዘንድ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይም ለአገሪቱ እግር ኳስ ትንሣኤ ገንዘባቸውንና አቅማቸውን ሳይቆጥቡ አለኝታቸውን እያረጋገጡ የሚገኙት ኢንጂነር ተክለብርሃን አምባዬ በአባትነት ሊያሳድጉት ቃል ገብተውለታል፡፡

ስለጉዳዩ ያነሣንለት ታዲዮስ፣ የኢንጂነር ተክለብርሃን አምባዬን ቸርነትና መልካም ፈቃደኝነት ከማውራት ይልቅ ‹‹ከ16 ዓመት በኋላ አባት አገኘሁ›› ብሎ በሁለቱም ዓይኖቹ እምባ ሲያቀር ለተመለከተው ቀጣዩን መናገር ይከብዳል፡፡

ቀጥሎ ‹‹እኔም›› አለ ታዳጊው፣ በዓይኖቹ ያቀረሩት እምባ እየጠራረገ፣ ‹‹ለዚህ ያበቃች ፈጣሪ በጀመረልኝ መንገድ የእኔም ጥረት ታክሎበት ለቁም ነገር ከበቃሁ፣ የመጀመርያ ዕቅዴ የማገኘውን ገንዘብ እንደ ኢንጂነር ተክለብርሃን ሁሉ በተለይም አሁን ለደረስኩበት እንድደርስ መኖርያቸውን በባህር ዳር ጐዳናዎች ላደረጉና በየክልል ከተሞች ተመሳሳይ የሕይወት ዕጣ ለሚመሩ ታዳጊዎች መርጃ የሚሆን ነገር ላይ ማዋል ነው፤›› ሲል በአባትነት ለተረከቡት ኢንጂነር ተክለብርሃን አምባዬ ያለውን ልባዊ ምስጋና አቅርቦ ከቱኒዝያው የደርሶ መልስ ጨዋታ በኋላ ወደ ባህር ዳር አምርቶ የትምህርት ማስረጃውን አምጥቶ ትምህርት ለመቀጠል መወሰኑን ያስረዳል፡፡

የአውሮፓ ኳስ ተፅዕኖ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግም ሆነ ብሔራዊ ሊግና ሌሎችም ጨዋታዎች በአገሪቱ ቴሌቪዥን የመመልከት ዕድሉ ስለሌለ ታዳጊውን ጨምሮ የአገሪቱ ታዳጊዎች በአውሮፓና በሌሎች አገሮች እግር ኳስ ተፅዕኖ ሥር ገብተዋል፡፡ ስለዚሁ እውነትነት ታዳጊው፣ ‹‹እኔን ጨምሮ በአገሪቱ የምንገኝ ታዳጊ ወጣቶች ሞዴል አድርገን የምንመለከተው የውጭ ተጫዋቾችን ሆኗል፡፡ ለዚህ ምክንያት ከተባለ በአገሬ የሚጫወቱ ክለቦች በዝና ካልሆነ አንዳቸውንም አላውቅም፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የምደግፈው ክለብም ሆነ ተጫዋች የለም፡፡ እውነቱን ለመናገር እኔ በአካል የማውቀውን ያህል ቅርቤ እንደሆነ የሚሰማኝ የአውሮፓ ኳስ ነው፡፡ ለእንግሊዙ ማንችስተር ዩናይትድ በተለይም ለዋይኒ ሩኒ ነው የተለየ ክብርና አድናቆት ያለኝ፤›› ሲል የፈጠረበትን ተፅዕኖ ያስረዳል፡፡

መፍትሔውን አስመልክቶ ታዳጊው፣ ‹‹እግር ኳስ በእያዳንዱ ኅብረሰብ አእምሮ ተቀርጾ፣ እንዲያም ሲል የእኔነት ስሜት እንዲመጣ ከታች ከቀበሌ ጀምሮ አቅምን ያገናዘቡ ፕሮጀክት መመሥረት፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን መጥፎ አመለካከት እንዲሊወጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ማመቻቸት፡፡ ታዳጊዎች መሠረታዊ የእግር ኳስ ክህሎቶችን ቀስመው እንዲያድጉ የተለያዩ አካዴሚዎችና ፕሮጀክቶች የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅድ ተይዞላቸው ተገቢውን ትኩረት ሲያገኝ ነው፤›› ይላል፡፡

የኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ያሬድ ቶሌራ በበኩሉ፣ ይህ አሁን የተጀመረው ተነሣሽነት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ስለፕሮጀክት ጽንሰ ሐሳብ መወራት ያለበት በፌዴሬሸን ደረጃ ብቻ ሳይሆን የፕሪሚየርና ብሔራዊ ሊግ ክለቦች አጀንዳቸው አድርገው ሊተገብሩት እንደሚገባ ያስረዳል፡፡

ከፕሮጀክቶች ጋር ተያይዞ ለሚነሡ የተለያዩ አመለካከቶች የፕሪሚየርና ብሔራዊ ሊግ ክለቦች የተዋቀሩበት ሥርዓት በተለይ ታዳጊዎችን ከማፍራት አኳያ ክፍተት ያለበት መሆኑም ይጠቀሳል፡፡ የአገሪቱ ክለቦች የመንግሥቶቹም ሆኑ የግሎቹ በተለይ የተጫዋቾችን ዝውውር የሚፈጽሙበት ሥርዓት ታዳጊዎችን የሚያበረታታ አለመሆኑ ደግሞ የአገሪቱ እግር ኳስ አሁን ለሚገኝበት ደረጃ የመጀመርያው ተጠያቂ ተደርጐ ይቀርባል፡፡ ተጫዋቾች ከክለብ ክለብ እንዲዘዋወሩ ሲደረግና ለሚወጣባቸው የዝውውር ክፍያን ጨምሮ ዕድሜና ችሎታቸው ግምት ውስጥ ገብቶ እንዳልሆነ፣ ይህ ዓይነቱ አሠራር ደግሞ ክለቦች ተተኪዎች ላይ ትኩረት ሰጥተው ከመንቀቀስ ይልቅ በጊዜያዊ ውጤት ተወስነው እንዲቆዩ አድርጓቸዋል የሚሉም በርካቶች ናቸው፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር