በሀዋሳ ከተማ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች እየተካሄዱ ነዉ

አዋሳ ጥቅምት 28/2005 በሀዋሳ ከተማ ለዘንድሮ በጀት አመት በተመደበ ከ700 ሚሊዮን ብር በጀት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች እየተካሄዱ መሆናቸውን የከተማው አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ገለጸ ። 
ለፕሮጀክቶቹና ፕሮግራሞቹ ማስፈፀሚያ የሚዉለዉ ወጪ በአብዛኛው በከተማው አስተዳደር ገቢ የሚሸፈን መሆኑ ተመልክቷል ። 
የመምሪያው ምክትል ሃላፊ አቶ አሻሬ ኡጋ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት እየተካሄዱ ካሉት የልማት ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞቹ መካከል አስፓልት መንገድ ግንባታን ጨምሮ የመጠጥ ውሃ፣ የተቀናጀ የቤቶች ልማት፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የግብርናና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ 
በተለይ በመንገድ ልማት ዘርፍ የ6 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር አዲስ አስፓልት ግንባታና የ4 ኪሎ ሜትር የነባር አስፓልት ጥገና፣ የ160 ኪሎ ሜትር አዲስ የጠጠር ምንገድ ስራና የ144 ኪሎ ሜትር የነባር መንገዶች ደረጃ የማሻሻል ተግባራት እንደሚከናወኑ አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም የከተማው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሻሻል ከ253 ሚልዮን ብር በላይ የስድስት ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ ፣ የፓምፕ ተከላ ፣ የዉሀ ቧንቧ መስመር መዘርጋትና ሌሎች ተጓዳኝ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸዉን አቶ አሻሬ አስታዉቀዋል ። የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለል ቀደም ብለው የተጀመሩ የ1ሺህ 890 ቤቶች ግንባታ በማጠናቀቅ ለህብረተሰቡ የማሰረከብ ስራ እንደሚካሄድም ተናግረዋል፡፡

 የከተማው ጤና አገልገሎት ሽፋንም አሁን ካለበት 70 በመቶ ወደ 92 በመቶ ለማሳደግ የአንድ አዲስ ጤና ጣቢያና ሌሎች ቀደም ብለው የተጠናቀቁ ጤና ጣቢያዎችን በሰው ሃይልና በቁሳቁስ በማደራጀት ለአገልገሎት የማብቃት ስራ እንደሚከነወንም ገልጠዋል ። በከተማው አስተዳደር በየደረጃው የሚሰጠው ትምህርት ጥራቱን ለማስጠበቅ ውስጣዊ ብቃቱንና ተገቢነቱን ለማሻሻል እንዲሁም ፍትሃዊ የትምህርት አቅርቦት እንዲረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል ። 
የከተማው የመሬት አጠቃቀም ስርዓት ዘመናዊ በማድረግ የነዋሪውን እርካታ ለማሳደግ የከተማው ዕድገት በዘመናዊ የከተማ ፕላን እንዲመራ ይደረጋል ብለዋል፡፡ በከተማው ስምንቱም ክፍለ ከተሞችና 32 ቀበሌዎች ያለው ሲቪል ሰርቪሱ የልማት ሃይልነቱን ለማጎልበት በመንግስት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂ ላይ ስልጠና በመስጠት የማስፈፀም አቅሙን ለመገንባት ትኩረት መሰጠቱንም አስረድተዋል፡፡ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መነሻ በማድረግ በ2005 የበጀት ዓመት የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ በቱሪዝምና ኢንቨስትመንት፣ በመልካም አስተዳደር ሁሉ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የሚደረገው የተቀናጀ ርብርቦሽ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡ በዘመኑ ለሚካሄዱት ለእነዚህ ዘርፈ ብዙ የልማት ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ ወጪ በአብዛኛው በከተማው አስተዳደር የውስጥ ገቢ የሚሸፈን ቢሆንም በተወሰነ ደረጃ የመንግስት ድጎማ፣ የውጭ ብድርና ዕርዳታ እንደሚታከልበት አቶ አሻሬ አመልከተዋል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=3235&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር