ዞኑ በመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

አዋሳ ጥቅምት 28/2005 ከተለያዩ የገቢ አርእስቶች ከ52 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የሲዳማ ዞን ገቢዎች ባለስልጣን አስታወቀ። በመጀመሪያ ሩብ ዓመት የተሰበሰበው ይኸው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ6 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው ነው። ገቢዉ የተሰበሰበው ከቀጥተኛና ቀጥተኛ ካልሆኑ ታክሶች ፣ከማዘጋጃ ቤት ገቢና ከሌሎች የገቢ አርእስቶች መሆኑን የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተሻለ ቡላዶ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጠዋል ። ጽህፈት ቤቱ ከሩብ ዓመቱ ዕቅድና ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ብልጫ ያለው ገቢ ለመሰብሰብ የቻለዉ በዞኑ ለሚገኙ ግብር ከፋዮች የግንዛቤ ማጎልበቻ ስልጠናዎችን በመስጠት፣ የታክስ ስርዓቱን በዞኑ ወረዳዎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች ተደራሽ በማድረግና ዘመናዊ የታክስና ቀረጥ መረጃ ስርዓት በመዘርጋት መሆኑን አስታዉቀዋል ። በዞኑ በሚገኙት የይርጋለምና አለታ ወንዶ ከተማ አስተዳደሮች ያሉ ግብር ከፋዮች የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ መጠቀም እንዲችሉ ለማድረግ የኔት ወርክ ዝርጋታ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝና ለግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ስለመሣሪያው ስልጠና በመስጠት በሁለት ወራት ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አቶ ተሻለ ገልጸዋል። ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ አዳዲስ ግብር ከፋዮችን ወደ ታክስ ስርዓቱ በማስገባትና ቀድሞ የነበሩ ግብር ከፋዮችን ደረጃ ገምግሞ በማሳደግ በተያዘው የበጀት ዓመት 344 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። በሩብ ዓመቱ 1ሺ600 አዲስ የደረጃ ሐመሩ ሐ ግብር ከፋዮች ወደ ስርዓቱ መግባታቸውንና 923 የደረጃ ሐመሩ ሐ ግብር ከፋዮች ወደ ደረጃ ለ ግብር ከፋይነት ማሳደግ መቻሉን አስታውቀዋል።
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=3224&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር