በደቡብ ክልል ከ320 ሚልዮን ብር በሚበልጥ በጀት የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ስራ ይካሄዳል ተባለ


አዋሳ ጥቅምት 24/2005 በደቡብ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ከ320 ሚልዮን ብር በሚበልጥ ወጪ 123 ኪሎ ሜትር የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ግንባታ እንደሚካሄድ የክልሉ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡ ግንባታው ከ36ሺህ ለሚበልጡ ስራ አጥ ወጣቶች የስራ እድል እንደሚፈጠር ተጠቁሟል፡፡ የቢሮው የመሰረተ ልማት አቅርቦትና አስተዳደር ዋና የስራ ሂደት ባለቤት አቶ አምሩላህ ጠለሀ ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ግንባታ ስራው የሚከናወነው በክልሉ 14 ዞኖችና 4 ልዩ ወረዳዎች በሚገኙ 22 ከተሞች ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ በሚገነባው የድንጋይ ንጣፍ መንገድ በሚፈጠረው የስራ ዕድል ከ36ሺህ በላይ ስራ አጥ ወጣቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በመጠቆም ከእነዚህም መካከል ወደ 13ሺህ የሚሆኑት ሴቶች ይሆናሉ ብለዋል፡፡ በከተሞች የሚሰራው መንገድ በአማካይ 8 ሜትር ስፋትና 123 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው እንደሚሆን ገልጸው የዚሁ ግንባታ ወጪ 140 ሚልዮን ብር በክልሉ መንግስት ቀሪው በከተሞች ማዘጋጃ ቤቶች፣ከአለም ባንክና ከጀርመን መንግስት ድጋፍ ነው ብለዋል፡፡ የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ከአስፓልት የማይተናነስና በዝቅተኛ ወጪ ለረጅም ዓመታት ያለብልሽት የሚያገለግል ከመሆኑም ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ነባር መንገዶች፣ ጥርጊያና ጥገና፣ የጎርፍ መውረጃ ቦዮች ግንባታና ማሻሻያ፣ የቱቦ ቀበራ፣ የእግረኛ መተላለፊያ ፣ የመንገድ መብራትና የውሃ መስመር ዝርጋታን ጨምሮ ከ2ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍኑ የመሰረተ ልማት ስራዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡ በደቡብ ክልል ባለፈው በጀት ከ146 ሚልዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ከ59 ኪሎ ሜትር በላይ የድንጋይ ንጣፍ መገንባቱንና ከ26ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ ዕድል መፈጠሩን አቶ አምሩላህ ገልጸዋል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=3140

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር