በሲዳማ ዞን 25 የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ይካሄዳል


አዋሳ ህዳር 6/2005 በሲዳማ ዞን የሚሊኒየሙን የልማት ግብ ለማሳካት በበጀት ዓመቱ ከ89 ሚልዮን ብር በሚበልጥ በጀት 25 የመጠጥ ውሃ ፐሮጀክት ግንባታ እንደሚካሄድ የዞኑ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ገለጸ፡፡ የመምሪያው ሃላፊ አቶ አብሩ ዳቃሞ ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ከፕሮጀክቶቹ መካከል 20ዎቹ ጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ ቀሪዎቹ ማከፋፈያ፣ የማጠራቀሚያ ጋን፣ የውሃ ቦኖና ምንጭ ማጎልበት ናቸው፡፡ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶቹ የሚሰሩት በመንግስት፣ በዋሽ፣ በዩኒሴፍ ፕሮግራምና በህብረተሰብ ተሳተፎ መሆኑን ጠቁመው ወደ ስራ ለመግባት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹ በተያዘው የበጀት ዓመት መጨረሻ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው አገልገሎት እንዲሰጡ ከዞን ምክር ቤት ጀምሮ በየደረጃው ለሚገኙ አመራር አካላትና ህብረተሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠቱን ተናግረዋል፡፡ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከ380ሺህ የሚበልጡ የዞኑ ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶቹ በዞኑ 50 በመቶ ላይ የነበረውን አጠቃላይ የዞኑን የመጠጥ ውሃ ሽፋን ወደ 62 በመቶ እንደሚያሳድግ ገልጸዋል፡፡ በዞኑ ወረዳዎች በሚገኙ 32 ቀበሌዎች ለ2006 የበጀት ዓመት ከመንግስት በተመደበ 75 ሺህ ብር 312 ፕሮጀክቶች ጥናትና ዲዛይን ስራ 24 ተቋማት የጣራ ላይ ውሃ ማሰባሰብ፣ 2ሺህ ነባር ተቋማትን መልሶ የማደራጀት ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ የቦርቻ፣ አለታ ወንዶና አለታ ጩኮ ወረዳ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት መጠጥ ውሃ ፍለጋ ረጅም ርቀት በመጓዝ ያባክኑት የነበረውን ጊዜ ለልማት በማዋል ምርትና ምርታማነታቸውን ለመጨመር እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ በ2004 በዞኑ አስራ ሁለት ወረዳዎች በተሰራው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ከ406ሺህ በላይ ነዋሪ በአቅራቢያቸው አገልገሎት ማግኘታቸውን የገለጹት አቶ አብሩ 4ሺህ 500 ማገዶ ቆጣቢ ምደጃ ፣ 73 የሶላር ኢነርጂ ተከላና 108 የባዮ ጋዝ ግንባታ ስራዎች መከናወኑን ተናግረዋል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=3354&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር