የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአማራ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች በ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጪ የርብና ጊዳቦ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እያካሄደ መሆኑን ገለጸ።


አዲስ አበባ ህዳር 09/2005 የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአማራ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች በ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጪ የርብና ጊዳቦ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እያካሄደ መሆኑን ገለጸ። ግንባታው ሲጠናቀቅ 26 ሺህ ሄክታር የሚደርስ የመስኖ መሬትን ማልማት እንደሚያስችል ተገልጿል። የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስተማማኝ የውኃ አቅርቦት እንዲኖር ለማስቻል የርብና የጊዳቦ መስኖ ልማት ፕሮጀክቶች የግድብ ግንባታ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በደቡብ ጎንደር ዞን በእብናትና ፋርጣ ወረዳዎች እንዲሁም በፎገራ ሜዳማ አካባቢ የሚገነባው የርብ ግድብ 234 ሜትር ኩብ ውኃ የመያዝ አቅም እንዳለው ገልጸዋል፡፡ የግድቡ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 14 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ የማልማት አቅም የሚኖረው ሲሆን ከ28 ሺህ በላይ አባዎራዎቸን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ በግድቡ ግንባታ ወቅት 400 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የታቸለ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 75 ያህሉ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል። የርብ ግድብ ግንባታ አጠቃላይ ወጪ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ የግድቡ ግንባታ በያዝነው ዓመት ሰኔ ወር እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋዕል፡፡ በተመሳሳይም በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልሎች በሲዳማና ቦረና ዞን አዋሳኝ በሚገኙ ዓባያና ለኮዓባያ ወረዳዎች 117 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ የመያዝ አቅም ያለው የጊዳቦ የመስኖ ልማት ግድብ ፕሮጀክት በመገንባት ላይ እንደሚገኝ አቶ ብዙነህ አመልክተዋል፡፡ የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ 11 ሺህ 924 ሄክታር ማልማት የሚያስችል ሲሆን ከ79 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍልን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡ የሁለቱ ግድቦች ግንባታ በአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመካከለኛና ሰፋፊ መስኖ ልማት መርሃ ግብር ውስጥ ተካተው በመገንባት ላይ ያሉ ናቸው፡፡ የመካከለኛና ሰፋፊ መስኖ እርሻ ሽፋን በዕቅዱ መጨረሻ በ2002 ዓ.ም ከነበረበት 2 ነጥብ 4 በመቶ ወደ 15 ነጥብ 3 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=3419&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር