ለምርጫው ስኬት የፍትህ አካላት ቅንጅታዊ ጥረት ተጠየቀ



ሐዋሳ (ኢዜአ)፡- ዘንድሮ የሚካሄደው የአካባቢ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፍትህ አካላትን ቅንጅታዊ ጥረት እንደሚሻ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና በደቡብ ክልል ለሚገኙ የፍትህ አካላት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በተዘጋጀው የአቅም ግንባታ ስልጠና ላይ እንደተናገሩት የሀገሪቱ ምርጫ አፈጻጸም ዓለም አቀፍ መርሆዎችን በተከተለና የህዝቡን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መጥቷል፡፡
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የሀገሪቱ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በማንኛውም ሁኔታ ልዩነት ሳይደረግባቸው በቀጥታ በነፃነት በመረጧቸው ተወካዮቻቸው አማካይኝነት ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ህገመንግስታዊ መብታቸውን መጠቀም ችለዋል ብለዋል፡፡
በአገሪቱ በምርጫው በኩል የታዩ መልካም ውጤቶችን የበለጠ ለማጠናከር መንግሥት ለነፃና ፍትሃዊ ምርጫ አፈጻጸም ዓለምአቀፍ መስፈርቶችን ያካተቱ አዋጆችን በማውጣትና ምርጫውን የሚያስፈጽሙ ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ በማቋቋም በርካታ ለውጦች እንዲመዘገቡ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡
የፍትህ አካላት በተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና በግል ዕጩዎች መካከል ለሚከሰቱ አለመግባባቶች መፍትሄ በመስጠት እንዲሁም ለነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አፈፃፀም ሥርዓት መስፈን ገንቢ አስተዋጽኦ በማበርከት ለሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጎልበት የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ምርጫው ሠላማዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ለማስፈፀም የተዘጋጁ የህግ ማዕቀፎችን መሰረት በማድረግ በቦርዱ ዕውቅና ያገኙ 75 የፖለቲካ ፓረቲዎች እንዳሉ የገለጹት ሰብሳቢው እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመልካም አስተዳደር መስፈንና ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጎልበት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በ2005 በሁሉም ክልሎችና በሁለቱም የከተማ አስተዳደሮች የሚደረገውን የአካባቢ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ቦርዱ ህግን መሰረት ያደረገ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው ለዚሁ ሁሉም የፍትህ አካላት የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል፡፡
ቦርዱ ሰላማዊና ነፃ ምርጫ ለአገሪቱ ዲሞክራሲ እደገት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመሆን በተለ ያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች የተዘጋጁ በርካታ ደንቦችና መመሪያዎችን ለሁሉም ክልሎች መሰራጨቱን አመልክተዋል፡፡
በምርጫው ወቅት ለሚከሰቱ ችግሮች ፍትሃዊ መፍትሄ ለመስጠት የፍትህ አካላት እዚህን መመሪያዎችን ጠንቅቀው እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡
የደቡብ ክልል ጠቅላይ 
ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ታረቀኝ አበራ በበኩላቸው በአስተማማኝ መሰረት ላይ የተገነባ ፍትሀዊ ሰላማዊና ነፃ ምርጫ ለማስፈን መድብለ ፓርቲ ውድድር እንዲጎልብት የፍትህ አካላትን ጨምሮ ሁሉም የባለድርሻ አከላት ርብርብ ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች አስተባባሪ አቶ አብርሃም ገዴቦ በበኩላቸው በክልሉ ምርጫው ነፃ፣ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ በየደረጃው የሚገኙ የፍትህ አካላት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡
እንዲሁም በክልሉ በ2005 ለሚደረገው የአካባቢ ምርጫ ከ8 ሺ በላይ የምርጫ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው የፍትህ አካላት ምርጫው በሚካሄድባቸው ቦታዎች የሚከሰቱ አለመግባባቶችን ነፃና ፍትሃዊ በሆነ መልክ መፍትሄ በመስጠት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
በሃዋሳ ለሁለት ተከታታይ ቀናት እየተካሄደ ባለው ስልጠና ላይ በክልሉ ከሚገኙ የተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ ከ300 በላይ የፍትህ አካላት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ናቸው፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር