ሲዳማን ማነው የወከለው?


ስሞኑን ከፌደራል እስከ ወረዳ ደረጃ የምገኙ የሲዳማ ኣመራር ኣባላት በሃዋሳ ከተማ በሲዳማ የወደፊት እጣ ፋንታ ላይ መክረው ባለ ዘጠኝ ነጥብ የኣቋም መግለጫ በማውጣት ኣጠናቀዋል። ኣንዳንዶች እንደምሉት ከሆነ የሲዳማ ኣመራሮች ዳግመኛ በሃዋሳ ከተማ ላለመሰባሰብ የወሰኑ ይመስላል፤ ምክንያቱም የሃዋሳን ከተማ ኣስተዳደር በሌሎች በሳል በምባሉ ብሄሮች እንድተዳደርላቸው ተሰማምተዋል እና ሃዋሳ ከእንግድህ የሲዳማ ኣስተዳደር ኣካል ባለመሆኑ በሃዋሳ ከተማ በሲዳማ ስም የመሰባሰብ እድል የላቸውም ይህንን እንኳን ኣርቆ ማየት ብሳናቸውም።

ወደ ቁምነገሩ ስንመለስ የሲዳማ ህዝብ ኢህኣደግ ይጠቅመኛል በመልካምኣስተዳደር በኩል ያለብኝን ችግር ይፈታልኛል በማለት በተደጋጋሚ በችግሩ ጊዜ ፈጥኖ በመድረስ ሲመርጠው ብቆይም፤ ደኢህዴን/ ኢህኣዴግ የሲዳማን ህዝብ ሲያሳዝን የሰሞኑ ክስተት የመጀመሪያው ኣይደለም። የዛሬ ኣስር ኣመት ደምኣፍሳሹ የደኢህዴን መንግስት የጸጥታ ኃይሎቹን ኣሰማርቶ በንጽሃን የሲዳማ ተወላጆችን ላይ በጠራራ ጸህይ የጥይት መዓት ኣውርዶ በርካታዎቹን በመግደል ሌሎቹን ኣቁስለዋል ፤ በድርግቱም የሲዳማ ህዝብ ክፉኛ ኣዝኗል፤ ሆኖም ከስህተቱ ይማራል ዳግመኛ መሰል ተግባር ኣይደግምም በማለት በባለፈው ምርጫ በነቅስ ወጥቶ እንደመረጠው ይታወሳል። ሰሞኑን ደግሞ ከባለፈው ስህተቱ ያልተማረው ደኢህዴን የሲዳማ ህዝብ ላሳየው ክብር እና ፍቅር የፓርቲው ኣመራሮች የሰጡት ምላሻ ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱን በመንጠቅ የራሱን ከተማ በተቀጣሪዎች እንዲያስተዳድር ማድረግ ሆኗል።

የምገርመው ደግሞ የሲዳማ የክልል ጥያቄን የሚያነሱ ኣካላት የሲዳማን ህዝብ የማወክሉ ናቸው ብለዋል። ለሲዳማ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ መብት መከበር ሲሉ በደኢህዴን እስር ቤቶች የሚማቅቁት ብሎም ተሰደው በባዕድ ኣገራት የስደት ጉሮ የምገፉት ውድ የሲዳማ ልጆች ጸረ ሲዳማ ተብለዋል። በተገላብጦሽ ፤የሲዳማ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በመንጠቅ በሃያ ኣመቱ የኢህኣደግ ኣስተዳደር ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ህገመንግስታዊ መብቱን በማስነጠቅ የተማረ ሰው የለህም፤ የሃዋሳን ከተማ ማስተዳደር ኣልቻልክም፤ወዘተ በማለት ለዘመናት በህዝቦች ዘንድ ተከብሮ የኖረውን ህዝብ ያዋረዱት የሲዳማ ተወካዮች ናቸው ተብለው ተሞካሽተዋል። እነዚሁ የሲዳማ ህዝብ ተወካዮች ነን ባይ ኣመራሮች የሲዳማ ህዝብ ህልውናማንነት ኣደጋ ላይ ጥለዋል፤ ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱን ጥያቄ ውስጥ ከተዋል፤ ሲዳማን ሌሎች እንዲያስተዳድሩት ያለ ህዝቡ ፍላጎት ጋብዘዋል፤ የሲዳማ ህዝብ ራሱን ማስተዳደር ያልቻለ ህዝብ ነው የምል ኣመለካከት ኣብሮት በምኖሩ በሌሎች ብሄሮች እንድፈጠር ኣድርገዋል፤ የሲዳማን ህዝብ የራሱን ግዛት ማስተዳደር ያልቻለ በሃያ ኣንድኣመት የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ታሪክ የመጀመሪያው ብሄር እንድሆን ኣድርገውታል፤ ወዘተ።


እዚህ ላይ ኣንድ የሲዳማ ሃዮ ወይም ምሳሌያዊ ታሪክ ማንሳት እወዳለሁ ። ይሄውም፦ ኣንድ ወቅት የኣንድ የሲዳማ ኣባት መንገድ እየተጓዙ በቃቻ መሃል (በመንደር መካከል) ሲያልፉ ኣንድ ህጻን ምርር ብሎ ስያለቅስ ሰምተው የኣባትነት ኣንጀት ኣላስችል ብሎኣቸው፤ ህጻኑ ወደሚያለቅስበት ግቢ ተጠግተው በኣጥር ተንጠራሪተው ወደሚያለቅሰው ህጻን ሲያዩ ፤ ህጻኑ የምያለቅሰው እናቱ ጸጉሩን እየላጨችው መሆኑን ተረድተው፤ ጸጉርህን የምትላጨው እናትህ የያዘህ ደግሞ ኣባት እንግድህ እኔ ምን ላደርግ እችላለሁ ብሎ ኣለ ይባላል። እንግድህ ከምሳሌው እንደምንረዳው የሲዳማ ህዝብ እየለጩ ያሉት የራሱ ኣመራሮች ናቸው።

እነዚህ የሲዳማን ኣመራሮች እነማናቸው ብለን ሲናስብ እና የኣንዳንዶቹን የትናንትናውን ስብዕናቸውን ስንገመግም ትንግርት ነው የምሆነው። ትናንትና የምያውቋቸው ዛሬ ላይ ሆነው በሲዳማ ህዝብ የያዙትን ኣቋም ላስተዋለ ሰው በኣስተሳሰባቸው ላይ ያሳዩት ለውጥ እንዴት ልፈጠር እንደቻለ ለማሰብ በራሱ ኣስቸጋር ነው። ለኣብነት ያህል በዩኒቨርስቲ ህይወታቸው ለሲዳማ ህዝብ መብት መከበር የምታገሉ የነበሩት የዛሬዎቹ ኣብዘኛዎቹ የሲዳማ ኣመራሮች፤ ዛሬ ደግሞ በተቃራኒው ቆመዋል። ትናንትና በራሳቸው ያስቡ የነበሩት እነዚሁ ግለሰቦች ዛሬ የሌላ ግለሰብ ኣመለካከት ተቀብሎ ከማራመድ ውጭ ያንን የመሰለ የህዝብ ተቆርቋሪነታቸውን ያንጸባረቁበት ኣመለካከት ውሃ በልቶታል። እንዳው ከደኢህዴን ኣመለካከት ውጭ ማሰብ ኣቅቷቸዋል ማለት እውነታ ኣለው።

እኔ እንደምመስለኝ ከሆነ እንዚህ ኣመራር ኣባላት ባለፉት ጥቂት ኣመታት ማለትም በደኢህዴን መስመር ውስጥ ገብተው መስራት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምረው በራሳቸው ማሰብ በማቆማቸው የተባሉትን ከማድረግ ውጭ የራሳቸውን ኣቋም መያዝ ኣቅቷቸዋል።

ለመሆኑ በተለይ በዚህ ሳምንት ያወጡት የኣቋም መግለጫም ሆነ ወሳኔዎቹ በርግጥ የሲዳማን ህዝብ ይጠቅማሉ? ወይስ የሲዳማን ህዝብ ጥቅም ባያስጠብቁም የደኢህዴን ፖሊስ ለማስፈጸም ያህል የተወሰዱ እርምጃዎች ናቸው? ቀጥዬ ማነሳቸው ነጥቦች ናቸው ፤ እመለስበታለሁ።

ክቡራን ኣንባቢያን ከላይ በተነሳው ሀሳብ ላይ ያላችሁን ኣስተያዬቶች በብሎጉ ኣድራሻ ላኩልን

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር