ኢትዮጵያ ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፈውን የኤች.አይ.ቪ/ስርጭት ስርጭት ለመግታት ብዙ መሥራት ይጠበቅባታል


አዲስ አበባ ጥቅምት 17/2005 ኢትዮጵያ ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፈውን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ቫይረስ ስርጭት በመግታት ረገድ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡ 
ቢሮውና ኢንትራ ሄልዝ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ከእናት ለእናት አመቻች ቡድን ጋር በመስራት ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ከእናት ወደ ልጅ /ጽንስ/ እንዳይተላለፍ በተሰጠው አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ የ200 ሕጻናት እናቶች ዛሬ የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡ 
የቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ፋንቱ ጸጋዬ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭትን በመከላከል ውጤታማ እየሆኑ ከመጡ ጥቂት አገሮች አንዷ ብትሆንም፤ ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፈውን ስርጭት ለመከላከል የተጠናከረ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅት ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ በመግታት ረገድ ያለውን ክፍተት ለመድፈን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሕጻናት ላይ የሚኖረውን የቫይረሱን አዲስ ስርጭት ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት የተያዘውን እቅድ በመቀበል ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ጠቁመዋል፡፡ 
የእቅዱ መተግበሪያ ዋነኛው መንገድም እናቶች በእርግዝና ወቅት ምርመራ እንዲያደርጉና ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ከሆነም አስፈላጊውን ሕክምናና የምክር አገልግሎት አግኝተው መከላከያ በመውሰድ ከቫይረሱ ነፃ የሆነ ሕጻን እንዲወልዱ ማድረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ለዚህም የጤና ተቋማትን ማስፋፋትና በሁሉም ተቋማት አገልግሎቱ እንዲሰጥ ማድረግ ወሳኝነት እንዳለው ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ከተማዋ የነበሯትን የጤና ጣቢያዎች ቁጥር በማሳደግና አገልግሎቱን በማጠናከር ሰፊ ሥራ መከናወኑንና በግል ጤና ተቋማት ጭምር አገልግሎቱ መስፋፋቱን አመልክተዋል፡፡ የጤና ተቋማቱን ቁጥር ወደ 111 መድረሱንም ወይዘሮ ፋንቱ አብራርተዋል፡፡ 
የኢንትራ ሄልዝ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ወይዘሮ ምስራቅ መኮንን እንደገለጹት ፕሮጀክቱ እ.አ.አ ከ2009 ጀምሮ በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይና በደቡብ ክልሎች እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ 
በአገር አቀፍ ደረጃም በ519 ጤና ጣቢያዎች ላይ ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ በመከላከል፣ በእናቶች ድጋፍ ፕሮግራምና በማህበረሰብ ቅስቀሳ ዙሪያ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአዲስ አበባም በቦሌ፣ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ በኮልፌ ቀራኒዮ፣ በጉለሌ፣ በቂርቆስና በየካ ክፍለ ከተሞች በ22 ጤና ጣቢያዎች ውስጥ ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የመከላከል አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ 
እንዲሁም በ47 ወረዳዎችና በ13 ጤና ጣቢያዎች የእናቶች ድጋፍ ቡድን፣ በ13 ወረዳዎች ደግሞ የፍላጎት ፈጠራና የማህበረሰብ ቅስቀሳ ስራ እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዕለቱ የምስክር ወረቀት የተቀበሉትና ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩት 200 እናቶችም ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ /ጽንስ/ እንዳይተላለፍ በተሰጠው አገልግሎት ተጠቅመው ከቫይረሱ ነጻ የሆኑ ሕጻናትን የወለዱና ለአንድ ዓመት ተኩል የተሰጣቸውን ትምህርት ተከታትለዋል፡፡ 
ፕሮግራሙ እናቶቹ ከቫይረሱ ጋር የአኗኗር ልምዳቸውን በማሳደግ ለልጆቻቸውና ለቤተሰቦቻቸው በቂ እንክብካቤ የሚያደርጉበት አቅም እንዲኖራቸው እንዳስቻላቸው መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=3003&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር