በመላ ሃገሪቱ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ተወካዩን መረጠ



አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) ዛሬ በመላው ሀገሪቱ የተካሄደው የኢትዮጵያ ኡላማዎች የፈትዋና ዳዕዋ የወረዳና የቀበሌ ምክር ቤቶች ምርጫ በሰላም ተጠናቀቀ።

በምርጫው በርካታ የእምነቱ ተከታዮች ከማለዳ  ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማና በተለያዩ የክልል ከተሞች በየምርጫ ጣቢያዎቹ በመገኘት፥ ይወክለናል ያሉትን እጩ ሀይማኖታዊ ስነ ሰርአቱ በሚያዘው መሰረት ሲመርጡ አርፍደዋል።

በየምርጫ ጣቢያው 25 እጩዎች የተጠቆሙ ሲሆን ፥ ከመካከላቸው አብላጫ ድጋፍ ያገኙ 20ዎቹ የምክር ቤት አባላት ሆነዋል። አብላጫውን ድጋፍ ያገኙትና በከፍተኛ ድምጽ የተመረጡት አምስቱ የምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ በመሆን፤ የስራ ድርሻቸውን እዚያው በህዝቡ መካከል የስራ ድልድል በማድረግ ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

የእምነቱ ተከታዮችም በምርጫው ንቁ ተሳታፊ በመሆን ፥ ዕምነቱ የሚፈቅደውንና የአመራር ስርዓቱን  አጠናክረው ያስቀጥላሉ የሚሏቸውን እጩዎች ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ዲሞክራሲያዊ እና አሳታፊ በሆነ መልኩ መርጠዋል።

በምርጫው ወቅት የምርጫ ካርድ ያልወሰዱ መራጮች በመመዝገብ የመረጡ ሲሆን ፥ የመራጩ ቁጥርም ከተጠበቀው በላይ እንደነበር ነው የምርጫ አስፈጻሚዎቹ የጠቆሙት።

በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለ ከተሞችና በጅማ፣ በሃረር፣ በደሴ፣ በሻሸመኔ፣ በጎንደር እና በመቀሌ ሪፖርተሮቻችን በተዘዋወሩባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ፥  ያነጋገሯቸው ድምጽ ሰጭዎች አፍራሽ ሃይሎች ያደርጉት የነበረው ቅስቀሳና በምርጫው ወቅት ያዩት ነገር የተለያየና ፍጹም ሰላማዊ እንደነበር ነው የገለጹት።

ተመራጮቹ የእስልምና ምክር ቤቶች አባላት የመረጣቸውን ህዝብ በቅንነት እና በታማኝነት እንዲያገለግሉ መራጮቹ የጠየቁ ሲሆን ፥ ተመራጮቹም የተጣለባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት በአላህ ስም ቃል እንገባለን ማለታቸውን የተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎችን የጎበኙ ባልደረቦቻችን ዘግበዋል።

በሌላ በኩል የዛሬው ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ እንዲሁም ውጤታማ እንደነበር ፥ የኢትዮጵያ ኡላማዎች ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ ሸህ ኢዘዲን ሸህ አብዱልአዚዝ ተናግረዋል።

መንግስት የሙስሊሙ ተቋም ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል ላደረገው አስተዋጽኦ እና ፤ ሙስሊሙ ህብረተሰብ በምርጫው ወቅት ላሳየው ዲሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ ተሳትፎ በምክር ቤቱ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር