ባለፉት ሁለት ዓመታት የአምስት ዓመቱ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም ስኬታማ ነበር-ፕሬዚዳንት ግርማ


አዲስ አበባ መስከረም 28/ 2005 ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ የአምስት ዓመቱ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ያለፉት ሁለት ዓመታት ዕቅድ አፈጻጸም ስኬታማ እንደነበር ገለጹ።
አራተኛው ዙር የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽ ምክር ቤቶች 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን የጋራ ስብሰባ የተከፈተው በቅርቡ ከዚህ ዓለም በድንገት በሞት ለተለዩት ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የህሊና ፀሎት በማድረግ ነበር።
ለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ግርማ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ተግባራዊ መሆን ከመጀመረ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ አገሪቱ ከ11 በመቶ በላይ ፈጣን ዕድገት ተመዝግቧል።
ኢትዮጵያ ለ9ኛ ጊዜ ባለሁለት አሃዝ እድገት በማስመዝገብ ፈጣኑን እድገት ለማስቀጠል መቻሏንም ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት ልክ እንደ ኢኮኖሚው ሁሉ በዴሞክራሲና ማህበራዊ ልማትን ከማስፈን አኳያ ከፍተኛ መሻሻልና እድገት ተመዝግቧል።
ባለፈው ዓመት የማዳበሪያና ምርጥ ዘር ተጠቃሚዎች ቁጥር ከፍ እንዲል በመደረጉና አርሶ አደሩ ዘመናዊ የግብርና ዘዴዎችን በተሻለ ደረጃ በመጠቀሙ የተሻለ ምርት እንደሚጠበቅም ጠቅሰዋል። በ2004 በጀት ዓመት በተለያዩ የስራ ፈጠራ ስልቶች በመታገዝ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዚያዊ የስራ እድሎች መፈጠራቸውንም ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።
በከተሞች የቤቶች ልማትን አጠናከሮ ለማስቀጠል ጥረት መደረጉን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 100 ሺህ መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ቤቶችን የመገንባት እንቅስቃሴ በመካሄድ ላይ መሆኑን አመልክተዋል።
በፌዴራልና በክልሎች የተጀመሩ የቤቶች ግንባታን በጥራት ለማጠናቀቅ ጥረት እንደሚደረግም አስረድተዋል።
ፕሬዚዳንት ግርማ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና የጊቤ 3 የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑን በንግግራቸው አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር 18 ሚሊዮን መድረሱን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ የአገልግሎት ጥራቱን ለማሳደግም ተጨማሪ የማስፋፊያ ስራዎች እንደሚካሄዱ አስረድተዋል።
የመንገድና የባቡር መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ ያብራሩት ፕሬዚዳንት ግርማ በተያዘው ዓመት የተለያየ ደረጃ ያላቸው 70 ሺህ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው መንገዶች እንደሚገነቡም ጠቁመዋል። ፕሬዚዳንት ግርማ እንዳብራሩት ግብር የመሰብሰብና የማስከፈል አቅምን ለማሳደግ በተደረገ ጥረት መልካም መሻሻሎች ታይተዋል።
በአገሪቱ የቁጠባ ባህል በተወሰነ መልኩ መሻሻል የታየ ቢሆንም አገራዊ የቁጠባ አቅምን በከፍተኛ ደረጃ ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ግርማ ባለፈው ዓመት መጀመሪያ ላይ ታይቶ የነበረው የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ ከመሄዱም ባሻገር ከ40 በመቶ ወደ 21 በመቶ መውረዱን ተናግረዋል። የዋጋ ግሽበቱ ወደ አንድ አሃዝ ደረጃ ዝቅ እንዲል ለማድረግ የተጀመረው ጥረትም ተጠናከሮ ይቀጥላል።
ፕሬዚዳንት ግርማ በትምህርትና በጤና ረገድም እየተካሄዱ ያሉ እንቅስቃሴዎችን በመክፈቻ ንግግራቸው አንስተዋል።
ነባር ዩኒቨርሲቲዎችን ከማስፋፋት ጎን ለጎን የአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ በተያዘለት ዕቅድ መሰረት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥም የላቀ ትኩረት እንደሚሰጠው አመልክተዋል።
መንግሥት የሪፈራል ሆስፒታሎችን ጨምሮ የተለያዩ የጤና ተቋማት ግንባታን አጠናክሮ እንደቀጠለና ለተቋማቱም አስፈላጊውን የሰው ኃይል፣ መድኃኒትና ቁሳቁስ በማሟላት ላይ ነው።
ፕሬዚዳንት ግርማ በተያዘው ዓመት የማሟያ ምርጫን ጨምሮ በአዲስ አበባና በሁሉም ክልሎች ባሉ የቀበሌና የወረዳ ምርጫዎች እንደሚካሄዱ ገልጸው ኀብረተሰቡ በንቃት እንዲሳተፍም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር