የሲዳማ ህዝብ ክልል የመሆን ጥያቄ በማይመለከታቸዉ ግለሰቦችና የዉሸት መረጃዎቻቸዉ አይቀለበስም

ከማህበራዊ መረብ ላይ የተገኘ ጽሁፍ
Giwoommo Gimbi ተጻፈ


!የሲዳማ ህዝብ ክልል የመሆን ጥያቄ በማይመለከታቸዉ ግለሰቦችና የዉሸት መረጃዎቻቸዉ አይቀለበስም

በቅርቡ የተካሄደዉ የሲዳማ ዞን አመራሮች ስብሰባ መላዉ የሲዳማ ህዝብ አቋሙን ለይቶ ከምን ጊዜዉም በተለየ መልኩ ራስን በራስ የማስተዳደር ወይም ክልል የመሆን ጥያቄዉን አጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያደርገዉ ነዉ፡፡ ይህ ጉዳይ በሁለት መልኩ ሊታይ ይችላል፡፡ 
Requests

አንደኛዉ ሟቹ ጠቅላይ ሚንስቴር በህይወት በነበሩበት ወቅት ለሲዳማ ህዝብ ቃል የገቡት የክልል ጥያቄ መልስ ሳያገኝ ቢያልፉም የተኳቸዉ ጠቀላይ ሚንስቴር አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ የተጠበቀዉ ከንቱ መሆኑ ነዉ፡፡ በአቶ ሽፈራዉ ሽጉጤ የተመራዉ የሲዳማ አመራሮች ስድስት ቀናት የፈጀዉን ስብስባ ሲያጠናቅቁ የሲዳማ ህዝብ የክልል ጥያቄ አስፈላጊ ያልሆነና የህገወጦች እንደሆነ አስምረዉበታል፡፡ በተጨማሪም የሀዋሳ ከተማ አስተዳደርም በስብጥር እንዲሆን በሙሉ ድምጽ ተስማምተዋል፡፡

ሁለተኛዉ ጉዳይ አቶ ሽፈራዉና ተከታዮቻቸው የሲዳማን ህዝብ እድገትም ሆነ ክልል መሆን የማይቻል እንደሆነ ለማስመሰል የዉሸት መረጃዎቻቸዉን አደራጅተዉ በሁሉም ሀይላቸዉ እንቅስቃሴ መጀመራቸዉ ነዉ፡፡ ለዚህም ባለፈዉ ስብሰባቸዉ ሲዳማ ክልል ከሆነ አሁን ያለዉ የበጀት ድጎማ ይቀንሳል፡ ልማት አይኖርም፡ የስራ አጥነት ይጨምራል ወዘተ በሬ ወለደ መረጃ እያቀረቡ ነበር፡፡
አቶ ሽፈራዉንና ተከታቻቸዉን ግን እረፉ! እዉነት ነጻ ስለምታወጣችሁ እዉነትን ያዙ እንላቸዋለን! ሁሌም የሚቀርቧቸዉ መረጃዎቸ ዉሸት ስለመሆናቸዉ መላዉ የሲዳማ ህዝብ የሚያዉቀዉ ስለሆነ የዚህ ጽሁፍ ዋና አላማ የበጀት ክፍፍሉን ብቻ በሚመለከት አንዳንድ መረጃዎችን ማቅረብ ነዉ፡፡ 
ወደ ዋናዉ ገዳይ ከመግባታችን በፊት አንዳንድ መንደርደሪያ ሐሳቦችን እናቅርብ፡፡ በአገራችን ክልሎች የተደራጁት ብሄር ብሄረሰቦችን መሰረት አድርገዉ (የኦሮሞ፣ የአማራ፣የትግራይ፣ የአፋር ወዘተ ክልል) መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህንን እዉነት ይዘን ብንነሳ…ዋናዉና ትልቁ መከራከሪያ ከሲዳማ ብሄር እዉቅና ዉጭ ተጨፍልቆ ደቡብ ተብሎ በአቅጣጫ ስም መጠራት በራሱ በህዝብ ላይ በሳለቅ/ስድብ ነዉ፡፡ የብሄርን ስብዕና ጨፍልቆ በአቅጣጫ ስም (ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምስራቅ ምዕራብ) መጥራት/መሰየም አስፈላጊ ቢሆን ኖሮ ትግራይንና አማራን አንድ ላይ ሰሜን ክልል፣ ሶማሌንና ሐረሪን ምስራቅ ክልል፣ ጋምቤላና ቤንሻንጉልን ምዕራብ ክልል ወዘተ ማለት ይቻል ነበር፡፡ ለስያሜም የሚመቸዉ በምንም የማይገናኙትን ሲዳማ፣ ወላይታ፣ከፋ ወዘተ አንድ ላይ መጨፍለቅ ሳይሆን በዘር ሀረግ፣ በባህልና በሀይማኖት የሚቀራረቡትን ትግራይንና አማራዉን የሰሜን ክልል ብሎ መሰየም ነበር፡፡ ይህ በቀላሉ የሚያሳየዉ ደቡብ ተብለዉ የተደራጁ ብሄር ብሄረሰቦች ላይ ያላቸዉን ዝቅተኛ አመለካከት ነዉ፡፡ 
በአሁኑ ወቅት የሲዳማ ህዝብ ደቡብ ተብሎ በመደራጀቱ ብቻ በአገሪቱ ደረጃ ያለዉ እዉቅናም ሆነ ዉክልና በዞኑ ዉስጥ በሚገኙ ወረዳዎች የአንዱን ወረዳ ያክል የህዝብ ብዛት ያላቸዉ ነገር ግን ክልል ተብለዉ እራሳቸዉን በእራሳቸዉ ከሚያስተዳድሩ ክልሎች ያነሰ መሆኑ ገሀድ የወጣ ሀቅ ነዉ፡፡ የደቡብ ክልል አወቃቀር እኛ ሲዳማዎች የመጣንበትን አከባቢ ስንጠየቅ እንኳን ብለን እንድንመልስ የሚያስገድድ በመሆኑ ሲዳማነታችንን በአገር ደረጃም ሆነ በዉጭዉ አለም እንዳናስታዉቅ የሚያደርግ ነዉ፡፡ ባህልን ከማሳደግና ማስተዋወቅ አንጻር የሚዲያ አጠቃቀም ሊጠቀስ ይችላል [ሁሉም ክልሎች በመንግስት ሚዲያ በራሳቸዉ ቋንቋ የአየር ሰዓት አላቸዉ]፡፡ በፌደራል መስሪያ ቤቶች፣ በአዲስ አበባ መስተዳድር እንዲሁም በኤምባስዎች ለሲዳማ የተሰጠዉ ዉክልና አለ የማይባል መሆኑም ለአብነት የሚጠቀስ ነዉ፡፡ ይሄስ ክልል የመሆንን ጥያቄ ለማቅረብ ማስረጃ አይሆንም? 
Requests


የበጀት ድልድሉን በሚመለከት አቶ ሸፈራዉና ተከታዮቻቸዉ የሚነግሩን የሲዳማ ህዝብ አሁን እያገኘ ያለዉ በጀት ክልል ቢሆን ከሚያገኘዉ የተሻለ እንደሆነ ነዉ፡፡ አቤት ዉሸት! መዋሸትን ለምደዉት እንጂ የኃጥአቶች ሁሉ ቁንጮ ኃጥአት መሆኑን ማን በነገራቸዉ!!

ክልል ባለመሆናችን ያጣንዉ ነግር የለም ለሚሉት ለነሽፈራዉና ጓዶቹ፤ ሌሎች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶች ባሉበት ሆነዉ በጀት ክፍፍሉን በሚመለከት ትንሽ አብነት ማቅረብ አስፈላጊ ሆኗል፡፡ (ሰንጠረዠ 1 ይመልከቱ)
ሰንጠረዠ 1 የ2005 የክልሎች በጀት ድጋፍ


የመረጃዉ ምንጭ፡ http://www.csa.gov.et/ እና http://www.mofed.gov.et/

በአገሪቱ ደረጃ የፌደራል በጀት በቀጥታ ድጎማ የሚደረግላቸዉ አዲሰ አበባንና የደሬዳዋን ከተሞች ጨምሮ 11 ክልሎች አሉ፡፡ ከላይ በሠንጠረዠ 1 እንደተመለከተዉ በህዝብ ብዛት በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ባለስልጣን መረጃ መሠረት አሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሌ እና ትግራይ ከ1ኛ እስከ 4ኛ [5ኛዉ ሲዳማ ነዉ] ያለዉን ደረጃ ሲይዙ፤ በመሬት ስፋት ደግሞ አሮሚያ፣ አማራ፣ ቤንሻንጉል እና ትግራይ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ያለዉን ደረጃ ይይዛሉ፡፡ በህዝብ ጥግግት (population Density) አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ እና አፋር ከፍተኛዉ 164 ሰዉ በካሬ ኪ. ሜ አነስተኛዉ 22 ሰዉ በካሬ ኪ. ሜ በመሆን እስከ አራተኛ ያለዉን ደረጃ ይይዛሉ፡፡ የበጀት ክፍፍሉ ሲታይ አሮሚያ (18,320,035,577) ፣ አማራ (13,060,776,134) ፣ ደቡብ (11,330,237,388) ፣ ሶማሌ (4,588,464,296) እና ትግራይ (4,047,318,629) ከ1ኛ እስከ 5ኛ ያለዉን ደረጃ በመያዝ የአንበሳዉን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ 
ከላይ የተዘረዘረዉ መረጃ መንግስት በይፋ ያወጣዉ/ያሳተመዉ መረጃ ነዉ፡፡ በዚሁ መሰረት ምንም እንኳን የሲዳማ ህዝብ ብዛት ከ5ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ቢታወቅም መንግስት ባወጣዉ መረጃ መሰረት ከትግራይ ቀጥሎ በ4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የ ካሬ ኪ.ሜ የሰፈር ሰዉ ብዛት ሲታይ 521 ሰዉ በአንድ ካሬ ኪ.ሜትር በማስፈር ከሁሉም ክልሎች አንደኛ ደረጃ ሲይዝ ይህም ህዝብ ተጠጋግቶ ኖረ ማለት ብዛት ያለዉ መሰረተ ልማት ይፈልጋል ማለት ነዉ፡፡ ሌላኛዉና ዋነኛዉ የበጀት ክፍፍል ፍትሀዊነት አመልካች የነፍስ ወከፍ በጀት ወይም በጀት ለህዝብ ብዛት ተካፍሎ የሚገኘዉ ዉጤት ነዉ፡፡ በዚሁ ዉጤት መሰረት እነ ሐረሪ፣ ጋምቤላ፣ ድሬዳዋ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ እና አፋር ከ 1100 ብር በግለስብ/በነፍስ ወከፍ የሚደርሳቸዉ ሲሆን ሶማሌ፣ ትግራይ፣ አማራ፣ ከኦሮሚያ (585) በስተቀር እያንዳንዱ ሰዉ በነፍስ ወከፍ ከ600 ብር በላይ ይደርሰዋል፡፡ የሲዳማ ህዝብ ግን በነፍስ ወከፍ የሚደርሰዉ ብር 345 ብቻ ነዉ፡፡ ይህ ጉዳት አይደለም?
በሌላ በኩል የሲዳማ ዞን በ2005 ዓ.ም የደረሰዉ በጀት ብር 1,174,548,789 ሲሆን ከሲዳማ ዞን በህዝብ ብዛትም ሆነ በሌሎች አመልካቾች ብዙም ልዩነት የሌላቸዉ፤ ነገር ግን ክልል በመሆናቸዉ ብቻ የሲዳማን ሦስትና አራት እጥፍ በጀት እንደተመደበላቸዉ ከሰንጠረዠ 1 መመልከት ይቻላል፡፡ ይሄስ ጉዳት አይደለም? በቀላል አገላለጽ፡- እራሳቸዉን በራሳቸዉ በማስተዳደር ለፌደራል መንግስት ተጠሪ የሆኑት ክልሎች ከዋናዉ ኬክ/ዳቦ ድርሻቸዉን የሚያገኙ ሲሆን ሲዳማዎች ግን ከቁራሹ እንደገና ተቆራርሶ የሚሰጣቸዉ መሆኑ በራሱ ፍትሃዊነት የሌለዉ ከመሆኑም ባሻገር ድርሻችንንም ዝቅተኛ አድረጎታል፡፡
ከፌደራል መንግስት ከሚገኘዉ በጀት ሌላ የሲዳማ ህዝብ ባለቤትነት ያላቸዉ የልማት ድርጅቶች (ኤስ ዲ ፒ፣ ኤስ ዲ ሲ፣ ፉራ ኮሌጅ፣የሲዳማ ልማት ማህበርና ማይክሮ ፋይናንስ) ተሽመድምደዉ እንዲወድቁ በማድረግ ህዝቡ በራሱ ተማምኖ አካባቢዉን እንዳያለማ አድርገዋል፡፡ በቅርብ ጊዜ የሲዳማ ቡና በአገር አቀፍ ገበያ እንዲወድቅ የተደረገዉም የሲዳማ ነጋደዎችን የገንዘብ አቅም በማዳከም በባንኮች ዕዳ ተይዘዉ የመብት ጥያቄ እንዳያነሱ ለማድረግ ነዉ፡፡ 
የበጀቱን በዚሁ እናብቃና በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለዉ እስራትና እንገልትስ? በተለይም በክልልም ሆነ በፌደራል የሉት ‹የደቡብ ክልል› ተወካዮች በሲዳማ ህዝብ የዉስጥ ጉዳይ ላይ እየወሰኑ ህዝብ ወደ ልማት እንዳይገባ በየወቅቱ ሰይጣናዊ አጀንዳ እየፈበረኩ ህዝብ በስጋት ውስጥ እንዲኖር እደረጉ አይደለምን?


የተከበርከዉ የሲዳማ ሕዝብ፡- እኛ የተሻለ ነገር ስንጠብቅ እነ ሽፈራዉ አቋማቸዉን ለይተዉ ክልል መሆን እንደማንችል እንዲሁም የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በስብጥር እንዲሆን ወስነዉ በመንግስት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ነግረዉናል፡፡ በነገራችን ላይ ይህንን ዉሳኔ ያስተላለፉ እንጂ በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ የሲዳማን ህዝብ ወክለዉ የመወሰን ስልጣን የሌላቸዉ መሆናቸዉን ልናዉቅ ይገባል፡፡ 

እኛ ግን በሁሉም መስፈርት እራሳችንን በራሳችን የማስተዳደር ወይም ክልል የመሆን መብታችንን ለማስከበር ከምን ጊዜዉም በበለጠ መነሳት ይኖርብናል፡፡ ስለዚህም በየደረጃዉ የዉሸት አጀንዳቸዉን ይዘዉ ለሚመጡ የሽፈራዉ ተላላኪዎች እዉነቱን አስረግጠን ልንነግራቸዉ ይገባል፡፡ እዉነት የሆነዉና እዉነትንም የሚወድ አምላክ መከናወን ይሰጠናል፡፡
http://www.facebook.com/groups/289317227830513/permalink/339853706110198/


Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር