የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለተባበሩት መንግስታት እውቅና ያቀረበው ጥያቄ በቅርቡ ምላሽ ያገኛል


አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2/2005/ዋኢማ/ - የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በተባበሩት መንግስታት ያቀረበው የእውቀና ጥያቄ በመጪው ህዳር ወር ምላሽ ሊያገኝ እንደሚችል ኮሚሽኑ አስታወቀ።

ኮሚሽነር አምባሳደር ጥሩነህ ዜና በተለይ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ኮሚሽኑ በመጪው ህዳር ወር ውሳኔ ከሚያገኙ ሀገራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ዝርዝር ውስጥ ይገኛል። 

ጥያቄው ተቀባይነት ካገኘ በ2000 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የአለም አቀፉ የብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋማት መረብ አባል ይሆናል። 

የዓለም ዓቀፉ መረብ አባል መሆን የሚያስገኘውን ጠቀሜታ አስመልክተው ኮሚሽነሩ ሲናገሩ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ እንደ የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን ሳይሆን እንደ ባለ ሙሉ መብት አባል በሀገሪቱ ውስጥ ስላለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማቅረብ  እድሉን ይከፍትለታል። 

በተባበሩት መንግስታት መድረኮች ላይም ኮሚሽኑ መድረክ ተሰጥቶት አቋሙን ማንፀባረቅ እንዲችል ያደርጋል። ይህም የተቋሙን ተሰሚነት እንደሚያሳድገው ኮሚሽነሩ አክለው ገልፀዋል።

ብሄራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋማት የአባልነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት የሚያገኘው የፓሪስ መርሆዎች የሚያስቀምጠውን ትንሹን መስፈርት ማሟላት ከቻሉ ነው። በዚህም መሰረት የ’ኤ’ እና ‘ቢ’ ደረጃ ይሰጣቸዋል።

የአባልነት ጥያቄ ከማቅረብ በፊት የኮሚሽኑን ተቋማዊ ደረጃ የማሻሻል ስራዎች እንደተሰሩ የገለፁት ኮሚሽነር ጥሩነህ፤ በአሁኑ ወቅትም ኮሚሽኑ በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ተደራሽነት በማስፋት፣ አቅሙን በማሳደግና የምርምርና ሪፖርት ስራዎችን በማሳተም ረገድ ብዙ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የዛሬ አምስት አመት ስራውን በአዲስ አበባ ብቻ የጀመረው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፤ በአሁኑ ወቅት በአዋሳ፣ ባህርዳር፣ መቀሌ፣ ጂማ፣ ጋምቤላና ጅጅጋ ቅርንጫፎችን ከፍቷል። የነበሩትንም ባለሙያዎች ከ20 ወደ 200 ማሳደግ ችሏል።

ከዩኒቨርስቲዎችና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበርም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማህበረሰቡ ክፍሎች ነፃ የህግ አገልግሎት የሚሰጡ 112 የህግ አገልግሎት ማዕከላት በመላው ሀገሪቱ መከፈታቸውንም ኮሚሽነሩ ለዋልታ ገልፀዋል።

በቀጣይም ኮሚሽኑ ተደራሽነቱን የማስፋት ስራውን አጠናክሮ በመቀጠል በየወረዳው ስምንት የነፃ ህግ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ለመክፈት እንደሚፈለግና ሶስት አዲስ ቅርንጫፎችንም በሌሎች ክልሎች ለመክፈት እቅድ መያዙን አክለው ተናግረዋል።

በኮሚሽኑ አነሳሽነትም በፍትህ ሚኒስቴር የሚመራ የብሔራዊ ሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሀ ግብር የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ ሲሆን፤ የብሔራዊ ሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሀ ግብሩ ረቂቅ ዝግጅት መጠናቀቁን አምባሳደር ጥሩነህ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት የሶስት ዓመት የድርጊት መርሀ ግብሩ ለፍትህ ሚኒስቴር መቅረቡንም አክለው ጠቁመዋል።

ፍትህ ሚኒስቴር ካየው በኋላ በሚኒስትሮች ምክር ቤት አማካኝነት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ከፀደቀ የህግ ሰነድ ሆኖ ያገለግላል።

የድርጊት መርሃ ግብሩ ፀድቆ መውጣት የኮሚሽኑ የሚያካሄዳቸውን በርካታ ስራዎች በማሟላት በኩል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የተናገሩት ኮሚሽነር ጥሩነህ፤ ኮሚሽኑ ለተግባራዊነቱ ከመንግስት ጎን ሆኖ እንደሚሰራ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ገልፀዋል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር