ጉዳዩ፡-ስለ ፍትሕ መጓደል አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠን መጠየቅ


ቀን፡15/01/2005
ቁጥር፡ቄለተድሮ01/2005
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞከራሲዊ ሪፐብሊክ
ለጠቅላይ ሚኒስተር ጽ/ቤት
አዲስ አበባ፡-
ጉዳዩ፡-ስለ ፍትሕ መጓደል አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠን መጠየቅ ይሆናል::


ከላይ በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው በኢ...ሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ሕገ-መንግስት የህጎች የበላይ ህግ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ማንኛውም የመንግስት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ-መንግስት ጋር የሚቃረን ከሆኔ ተፈፃሚነት እንደማይኖራቸው ይገልፃል፡፡ (The Constitution is the supreme law of the land. Any law, customary practice or a decision of an organ of state or a public official that contravenes this Constitution shall be of no effect)፡፡
በተጨማሪም በዚህ ህገ-መንግስት በአንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉአላዊ ሥልጣን ባለቤቶች መሆናቸውን ይደነግጋል (All sovereign power resides in the nations, nationalities and peoples of Ethiopia)፡፡
ይሄ ሕገ-መንግስት ከደነገገው ውጪ የደቡብ ብሔሮች በሔረሰቦችና ሕዝቦች ከልል የሚገኙ አንዳንድ ከፍተኛ አመራሮች ለሕዝብ መልካም አስተዳደርና ልማት ማረጋገጥ ካለመቻላቸውም በላይ በሕዝብና በመንግስት መካከል ያለውን አመኔታ የሚሸረሽሩ ድርጊቶችን፣ ክራይ ሰብሳቢነትንና ምግባረ-ብልሹነትን ለረጅም ጊዜያት ከመፈፀማቸው ጋር አያይዞ ሕዝቡ አኝኮ ስለተፋቸው ይህንን ለማስለወጥ የህዝብ አገልጋይ የሚያስመስል ጭንብል በማጥለቅ ነገር ግን ህዝቡን የሚጎዱና የሚቀሰቅሱ አጀንዳዎችን አንስተው በሕዝቡ መካከል እንደነዙ ይታወቃል፡፡
ነገር ግን ያሰቡትና የዶለቱት ሁሉ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኝ በመቅረቱ ምክንያት ላያገግሙ በመንገዳገዳቸው ያንኑ ህዝብ መልሰው እንሸንገል በሚል አጀንዳ ህዝቡን እያመሱ፣ ሰራተኞች ተረጋግተውና ውጤታማ በሚያደርግ አኳኋን እንዳይሰሩና የታለመውን የልማት ግብ እንዳያሳኩ በማሸማቀቅ ማነቆ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ ከዚም በተጨማሪ በተመሳሳይም ሁኔታ ተማሪዎች ተረጋግተው በመማር ፋንታ የሚያስተምሯቸው ቤተሰቦቻቸው በተለያየ ተጨባጭ ባልሆነ ምክንያት እየታሰሩና እየተሰደዱ በመሆኑ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ቤታቸው ለመመለስ ተገደዋል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ አርሶ አደሮችና ነጋዴዎች ልጆቻችሁን ከልል እንዳይጠይቁ ማድረግ አልቻላችሁምና በብራችሁ ህዝብን የመቀስቀስ ሥራ በመስራት ላይ ናችሁ በሚል ሰንካላ ምክንያት ንጹሐን ዜጎች የእንግልት ጽዋ እየቀመሱ ይገኛሉ፡፡
በተሣሣተ መንገድ የመንግስትን ታአማንነት ለማግኘት ስሉም የህዝብንና የመንግስትን ውስን ሀብት በከፍተኛ ደረጃ በማባከን ላይ ታች ሲሉና የሥልጣን እድሜ ሲያራዝሙ ቆይተዋል፤ ለመቆየትም እየዳዳቸው ይገኛል፡፡
እንደማነኛውም ኢትዮጵያዊ ብሔረሰቦች ህገ-መንግስቱ ለሲዳማ ህዝብ ካጎናፀፈለት መብቶች አንዱ ባህሉንና ትውፊቱን ማሳደግ ነው፡፡ በዚህ መነሻም የብሔሩን ዘመን መለወጫ ባህል የሆነውን የፍቼ-ጫምባላላ በዓል በአደባባይ (ጉዱማሌ) ለዘመናት ሲያከብር እስከዛሬ ደርሷል፡፡ በነቂስ የሚወጣው ህዝብም በዚህ በዓል በባህላዊ ጭፈራ(ቄጣላ) የሚወደውን አወድሶ፣ ያልተመቸውንና ህግጋትን (ሴራን) የተላለፈውን ግለሰብ ወይም ድርጅት ወቅሶና እንዲታረም አስጠንቅቆ በሰላም ወደቤቱ ይመለሳል፡፡
ከነሐሴ 8-9/2004 .ም የዋለው የፍቼ-ጫምባላላ በዓልም በሲዳማ ዞን አስተዳደር ጋባዥነት በዓሉን አከብሮ በዋለበት ወቅት በዲሞክራሲያዊና በጨዋ ሁኔታ ከማክበሩም በተጨማሪ እንደተለመደው ባልተመቸውና ህገ-መንግስታዊ መብታችን ነክቶብናል፣ ፍላጎታችንን አልጠበቀም፣ የልብ ምታችንን አላዳመጠም፣ በሙስናና ምግባረ-ብልሹነት አዋርዶናል ያለውን ወቅሶ መንግስትን ግን አሞጋግሶ ወደየቀዬው በሰላም ተመልሷል፡፡ ይህ ሰላማዊነት ደግሞ የሲዳማ ባህልም ስለሆነ በነቂስ የወጣው ህዝብ በዓሉን በሰላም አከብሮ ተመልሷል፡፡ ይሁንና እነዚህ የመልካም አስተዳደር ሽታ በአጠገባቸው ያላለፈባቸው መንግስትንና ህዝቡን የሚያጣላ ሥራ የሚሠሩ አመራሮች በለመዱት የአምባገነትና የአፈና ባህርያቸው በመጠቀም ተንኮል በወለደው (አንድ ባለሥልጣን ተሰደበ የሚል) የድርሰት ክስ በማዘጋጀት በሰላማዊ መንገድ መደበኛ ኑሮውን አየመራ ይህች አገር ለተያያዘችው ልማትና እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ደፋ ቀና የሚለውን የሲዳማ ህዝብ በፍቼ-ጫምባላላ በዓል ላይ ተገኝታችሁ የክልሉን ርዕሰ መስተዳደር የሚነካ(የሚወቅስ) ሐሳብ አንፀበርቃችኋል በሚል ሰንካላ ምከንያት ህዝቡን በማሸበር፣የገጠርና የከተማ ነዋሪዎችን ሁሉም ይታሠራል የሚል ሽብር በመንዛት ህዝቡ መንግሥት ከተያያዘው የልማት አንቅስቃሴ ጎዳና ውጪ የማድረግ ሥራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ከማሸበርም አልፈው የሲዳማ ብሔር አባላትን ከሽማግለዎች፣ ከተማሪዎች፣ ከነጋደዎች ከመንግሥት እና ከግል ድርጅት መሥሪያ ቤት ሰራተኞች ብዙ ሰዎችን ኢ-ሕገመንግስታዊ በሆነ መልኩ በሁሉም ወረዳዎችና በሐዋሳ ከተማ በእስር ቤት በማጎር ከመደበኛ ሥራዎቻቸው በማስተጓጎል በዚህ ኑሮ ውድነት ቤተሰቦቻቸውን የመበተን አደጋ ላይ ጥለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ህዝቡን በከፍተኛ ምሬት ውስጥ የመክተት ሥራ እየሠሩ በመቆየታቸው የሀገር ሽማግሌዎች ከዚህ እኩይ ተግባራቸው እንድመለሱ እና ታሣሪዎቹን እንድፈቱ ብጠይቋቸውም “እኔን 18 ሚሊዮን ህዝብ የማስተዳድረውን ንጉስ ስሜን በክፉ ያነሱትን እበቀላቸዋለሁ፣ ገና አደኀያቸዋለሁ፣ በእግሬ ሥር እስኪንበረከኩ ድረስ በወኂን ቤት አወርዳቸዋለሁ” እና ወ..ተ ብሎ እሰከመዛት የለየላቸውና ፍፁም አምባገነን ሆነው በአሁኑ ሰዓት ያለክስ ታሰረው በበሽታና እንግልት እየተሰቃዩ የሚገኙት ምሁራን ወንድሞቻችን በርካታ ናቸው፡፡
እነዚህ ወገኖች ወደ ፍርድ ቤት ቀርበው ከሚነገርባቸው የክስ ሁኔታ እና ክስ የተመሰረተባቸው ርዕስ ለመረዳት እንደሚቻለው ሕገ-መንግስቱን በኃይል ለመናድ፣ መንግስትን በኃይል ለመገልበጥ፣ ሕዝብን በመንግስት ላይ በማነሳሳት ወዘተ በሚሉ ሐሰተኛ የክስ ርዕሶች የተከሰሱ ቢሆንም በወንጀል እንጂ በፖለቲካ አመለካከታቸው እንዳልታሰሩ በተለያዩ ሚዲያዎች ይገልፃሉ፡፡ ነገር ግን እኚህ ዜጎች የፖለቲካ እስረኞች መሆናቸው ከላይ የገለፅነውን የክሱ ርዕስ መረዳት ቀላል ነው፡፡
ዘመኑ ሲዳማ በሙሉ የሚታሰርበት ነው እስኪባል ድረስ ፍርድ ቤት በነፃ ያሰናበታቸው ግለሰቦች ሁሉ እንደገና እየታደኑ ወደ እስር ቤት እየታጎሩ ይገኛሉ፡፡ የነዚህን ሰዎች ስም ዝርዝር በቀጥታ መንግስት ከማረሚያ ቤቶችና ፍርድ ቤቶች ማግኘት የሚችል ሲሆን ፍርድ ቤቶችም የባለስልጣናት ተላላኪዎች በመሆን በስልክ ትዕዛዝ ተጨማሪ ቀጠሮዎች እንዲሰጡ በማድረግና በግልፅበችሎት ላይ በስልክ እየተነጋገሩ የሚወስኑ ሆነዋል፡፡
እንግዲህ ሕዝብን የማፈን ስራ እስከመቼ እንደሚዘልቅ ማወቅ አልቻልንም፡፡ ምን ያህልና ለምን ያህል ጊዜ ማስተንፈስ እንደሚችልም አላወቅንም፡፡ ዜጎችን በስልክ ትዕዛዝ ብቻ እንደ እንሰሳት አፍኖ ማሰር እስከመቼ እንደሆነም አልገባንም፡፡ ማሰርና መግደል መፍትሄ የሚያመጣ ቢሆን ደርግ ባልወደቀ ነበርና ይህ መንግስት የሚያስተውልና ከታሪክ የሚማር ከሆነ ይህንን ማወቅ የሚሳነው አይመስለንም፡፡ ሕዝቡ መሰረታዊ የሚባሉ ሕገ-መንግስታዊ ጥያቄዎቹን ባነሳ ቁጥር መገደሉ፣ መታሰሩ፣ መሰደዱ እና መታፈኑ ከኢህአዴግ ምን ያህል እየራቀ መሆኑን ማወቅ ለማንም አያዳግትም፡፡
ስለሆነም የተሻለ የህገ-መንግስት መተግበር በምንጠብቅበት በዚህ አዲስ ዓመትና አመራር የሚከተሉት ቁልፍ ጉዳዮች ለዚህ ጭቁን ሕዝብ ምላሽ እንዲሰጠው በትህትና እንጠይቃለን፡፡
  1. በቅድሚያ ያለ ክስ እና ድርሰታዊ በሆነና ሆን ተብሎ በተቀነባበረ ክስ ታፍነው የታሰሩ የፖለቲካ እስረኛ ዜጎቻችን ቁልፍ የምንላቸው ምሁራንና የለውጥ ተስፋዎቻችን ናቸውና ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ ከእስር እንዲፈቱልን፣
  2. የሲዳማን ሕዝብ "እሾህን በእሾህ" እንዲሉ በራሳችን እጅግ ደካማ ሰው እንዲጠቃ የሚሰራው ሴራ እንዲመክን እንዲደረግ፣()በራሱ የቆመ፣ ቆራጥ የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደርና የትምህርት ዝግጅት ያለው ለራሱ ሳይሆን ለሕዝቡ የሚሰራ በዚህም የሲዳማን ሕዝብና መንግስትን የሚያቀራርብ አመራር እንዲተካልን፣
  3. የሲዳማ ብሔር በኢትዮጵያ ታላላቅ (በቁጥር) ከሚባሉ 5 ብሔሮች ውስጥ አንዱ ሆኖ ሳለ በፖለቲካው፣ ኢኮኖሚው፣ ማህበራዊና ቁሳዊ የመጨረሻ ሆኖ የሚኖርበት ዘመን እንዲያበቃና ራሱን ችሎ በክልል ደረጃ እንዲዋቀር፣ በዚህም ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር የበለጠ ተከባብሮ፣ በራሱ ጉዳይ ላይ ራሱ እየወሰነ፣ መንግስትን በልማትና መልካም አስተዳደር ረገድ እያገዘ እንዲኖር እንዲደረግ፣ በዚህም በደቡብ ክልል ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ነፃነት ሲጠይቅ የመጀመሪያው ብሔር እንዳልሆነና ከዚህ ቀደም በሌሎች ብሔሮች ላይ ተፈፃሚ የተደረገው ሕገ-መንግስት ወደ ሲዳማ ብሔር ድንበርም ዘልቆ እንዲገባ እንዲደረግ፤ ለምሳሌም ወጋጎዳ (ሰሜን ኦሞ) ዞን የነበረው አሁን 4 ዞኖች የሆነው (ወላይታ፣ ዳውሮ፣ ጋሞ እና ጎፋ)፣ ስልጤና ጉራጌ፣ አዲሱ የሰገን ሕዝቦች ዞን፣ ከንባታ ጠንባሮና ሀዲያ ወዘተ.
በመጨረሻም መንግስት በተለይም ጽ/ቤታችሁ ከላይ በግልፅ ያስቀመጥነውን ጥያቄያችንን እንዲመልስልን በመጠየቅ ጉዳዩን በአንክሮ በመመልከት ምላሽ በአጭር ጊዜ እንደሚሰጠን ተስፋ እናደርጋለን።()
ከሰላምታ ጋር
ህገ-መንግስታችን ይከበር!
ግልባጭ፡-
  • ለፌዴሬሽን ም/ቤት
  • ለኢህአዴግ ጽ/ቤት
  • ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን
  • ለሁሉም በኢትዮጵያ የሚገኙ ዲፕሎማቲክ ሚሽኖች
አዲስ አበባ፡-

የማመልከቻውን ሙሉ ቃል

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር