ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት የተደነገገው ለፌስቡክ ብቻ ነው?


በሰለሞን ጥበቡ
በዚህ ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ቴክኖሎጂ በፈጠረልን ምቹ ሁኔታ መረጃን በፍጥነትና በፈለግነው ቦታ መለዋወጥ አመቺ ሆኗል፡፡ ከእነዚህ መረጃን የመለዋወጫ መንገዶች ውስጥ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ይገኙበታል፡፡ ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ታግድና የመሳሰሉት ከማኅበራዊ ድረ ገጾች የተወሰኑት ናቸው፡፡ እኔ በግሌ እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ማኅበራዊ ድረ ገጾች አካውንት ቢኖረኝም፣ በአንድ ወር አንድ ጊዜ እንኳን የማልከፍታቸውም አሉ፡፡ እንዲያውም ትዊተርን ከፍቼ አላውቅም ብል ይሻለኛል፡፡
ይህም የሆነበት ምክንያት ትዊተር ስለማልወድ አይደለም፡፡ ይልቁንም የትዊተር ተጠቃሚ ጓደኞች ስለሌሉኝና ምንም ዓይነት መረጃ ማግኘት ስላልቻልኩ ነው፡፡ ታዲያ ምንም ዓይነት መረጃ የማይገኝበትን አካውንት መክፈት በድንጋይ ላይ ውኀ እንደማፍሰስ ነውና ላለመክፈት ወሰንኩ፡፡ አሁን እንዲያውም ፓስወርዱ ጠፍቶብኛል፡፡ ስለዚህ ከትዊተር ጋር ፍቺ ፈጽሜያለሁ፡፡

ትኩስ መረጃዎች የማይገኙባቸው ሌሎች ድረ ገጾችም ዕጣ ፈንታቸው ይህ ነው፡፡ ከእኔ ጋር መፋታት፡፡ በኢትዮጵያ ብዙ ተጠቃሚ እንዳለው ወደሚነገርለት ፌስቡክ ስንመጣ ግን ከላይ ከጠቀስኳቸው ማኅበራዊ ድረ ገጾች በተቃራኒው ነው፡፡ ምክንያቱም ፌስቡክ ላይ ምን የሌለ ነገር አለና? ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ስፖርትና ሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች እንደወረዱ የሚገኙበት ብቸኛው ቦታ ፌስቡክ አይደለም እንዴ? እውነቴን ነው የምላችሁ “መርካቶ ምን ጠፍቶ” የሚለው ማስታወቂያ ለሸቀጣ ሸቀጥ እንደሆነ ሁሉ፣ ትኩስ መረጃዎችን ለማግኘት ደግሞ ፌስቡክ ምን ጠፍቶ ማለት ይቻላል፡፡ የአገራችን ሚዲያዎች መረጃን ቶሎ አያደርሱም እየተባለ ይታማሉ፡፡
“ትዝብት ነው ትርፉ” ያለው ማን ነበር? መተዛዘብ ነው እንጂ ፌስቡክ ተጠቃሚ የሆነ እነርሱን ማን ይለምናቸዋል፡፡ ፌስቡክን ለአንድ ደቂቃ መጎብኘት በቂ ነው፡፡ የቢቢሲ፣ የአልጄዚራና የሌሎችም የውጭና የአገር ውስጥ ዘገባዎች እንደወረዱ ማግኘት እየተቻለ የምን መለማመጥ፡፡

ምናልባት የአገር ውስጥ ሚዲያዎችን ለማበረታታት ካልሆነ በስተቀር ፌስቡክ እያለ ደግሞ ለመረጃ፡፡ ለነገሩ የአገር ውስጥን ምርት መጠቀምም አልተለመደ እንኳን የአገር ውስጥ ሚዲያ፡፡ እኔ ግን የሚገርመኝ እነዚህ ፌስቡክ ላይ የሚለቀቁ መረጃዎችና ሐሳቦች በጋዜጦችና በሌሎች ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ለምን እንደማይወጡ ነው፡፡
በእርግጥ አንዳንድ ፌስቡክ ላይ የሚወጡ መረጃዎችና ሐሳቦች በፎቶ ኤዲቲንግ የታገዙና የተጋነኑ ናቸው፡፡ ግለሰብንም ዒላማ አድርገው የሚወጡ የተቀነባበሩ ፎቶዎች አሉ፡፡ ይህ ዓይነት አገላለጽ ተገቢ ባይሆንም በኤዲቲንግ የታገዘውን ፎቶ ትተን በፎቶው ላይ የሚጻፉ ሐሳቦችን ስንመለከት ጥሩ መረጃ ይሰጡናል፤ በጣም አስተማሪዎችም ናቸው፡፡

በነገራችን ላይ የአንድን ሰው የአስተሳሰብ ብስለትም በተወሰነ ፌስቡክ ላይ ፖስት በሚያደርጋቸው ነገሮች መረዳት ይቻላል፡፡ አሁን አሁንማ ሳስበው በፌስቡክ ሱስ ከተጠመድኩበት ወጥመድ መውጣት ሁሉ የምችል አይመስለኝም፡፡ ግን ወድጄ እኮ አይደለም፡፡ ይህ የደራው የመረጃ የሐሳብ ገበያ አለቅ ብሎኝ እንጂ፡፡ ገና አሐዱ ብዬ ኢንተርኔት ስከፍት መጀመሪያ የማየው የፌስቡክ አካውንቴን ነው፡፡ ዛሬስ ምን አዲስ ነገር አለ? የፌስቡክ ዘመዶቼስ ምን አሉ? የሚለውን ካላየሁ ሌላ ሥራም አይያዝልኝ፡፡ ሌላ ሥራ እየሠራሁም በየደቂቃዎች ፌስቡኬን አያለሁ፤ ለምን ብትሉኝ መልሴ ፌስቡክ እኮ ነው፡፡

ፌስቡክ እንደ ኢትዮጵያ ሬዲዮኖችና ቴሌቪዥን አሥር ጊዜ ዜና አይደግምም፤ መረጃ ፌስቡክ ላይ በየሰከንዱ ነው የሚለዋወጠው፡፡ ለዚያውም ያለምንም መሸማቀቅና መፍራት ማንም የመሰለውን ሐሳብና ያገኘውን መረጃ እንደወረደ ማሰራጨት የፌስቡክ ልዩ ባህሪው ነው፡፡ ታዲያ ይህን የመሰለ አስተሳሰብን የሚያሰፋ “ፕሮቲን” አይቼ እንዴት ሳይበላ ይቀራል? “እንዴት አይከንፍ ሰው ይህን ለምዶ” ብሎ ነበር ሙዚቀኛው ለድሬ የዘፈነው፡፡ እኔስ ይህን የፌስቡክ ነፃነት ለምጄ እንዴት ወደ ፌስቡክ አልከንፍ? አንድ የፌስቡክ ጓደኛዬ ፖስት አድርጎት ያየሁት ምን ይላል መሰላችሁ? “ፌስቡክ ልተው ብዬ ተናነቀኝ እምባ” ይላል፡፡ እርሱን ብቻ ቢሆን አሪፍ አልነበር ችግሩ፤ የእኔም መሆኑ ነው እንጂ፡፡ ይህን ሁሉ የነጻነት ድግስ ትቶ እንዴት ይኖራል? ድሮ ድሮ “ሆድ ያባውን ጌሾ ያወጣዋል” ይባል ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን ሆድ ያባውን ፌስቡክ ያወጣዋል መባል ተጀምሯል፡፡ ሁሉም የፌስቡክ ተጠቃሚ በውስጡ ያለውን ብሶትም ሆነ ደስታ ያለምንም መሸማቀቅ ፌስቡክ ላይ ቁጭ ነው፡፡ አቦ ፌስቡክ አሁንም ዕድሜህን ያርዝምልን እንጂ ገና ብዙ እናይብሃለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ሌላው ነገር ደግሞ ፌስቡክ ላይ ፖስት የተደረጉትን ማየት ብቻ ሳይሆን ፖስት በተደረጉ ጉዳዮች ላይ የተጻፉ አስተያየቶችን ማየትም በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ፖስት የተደረጉ ሐሳቦች ፖለቲካዊ ከሆኑ የአስተያየት ሰጪዎች ብዛት ይጨምራል፡፡ አንዳንዴማ ምን አስባለሁ መሰላችሁ ምን ነው ይህን ሁሉ አስተያየት መሪዎቻችን ቢያዩት የሚል ሐሳብ ድቅን ይልብኛል፡፡ ከዚህ መረዳት የምንችለው ነገር ቢኖር እነዚህ አስተያየት የሚጽፉ ሰዎች ደግፈውም ይሁን ተቃውመው ሐሳቡ በውስጣቸው እንደነበረና እንዴት መግለጽ እንደሚችሉ ሲያስቡ እንደነበር አያጠራጥርም፡፡ ምን አለበት ከዚህ ሁሉ ድግስ ትንሽ በጋዜጦችና በሬዲዮኖች ላይም ጣል ብናደርግባቸው? እውነቴን ነው የምላችሁ ጋዜጦችና ሬዲዮኖቻችን እኮ በመረጃና በነፃ ሐሳብ ድርቅ ተመትተዋል፡፡ ፌስቡክ ላይ የዘነበው ጋዜጦችና ሌሎች ሚዲያዎቻችን ላይ እንዴት አያካፋም? ምናልባትም ጃንሆይ ያሠሩትና አንድ ለእናቱ የሆነው ማተሚያ ቤት ፌስቡክ ላይ ፖስት አላስደርግም ማለት ስለማይችል ይሆን እነዚህ ሁሉ ሐሳቦች በነፃነት የሚንሸራሸሩት? ወይስ እኛ ፌስቡክ ካልሆነ ሐሳብ የሰጠን አይመስለንም? ከሆነ ግን ይገርማል፡፡

የዚህ ማተሚያ ቤት ነገር ከተነሳ አይቀር አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ እንደሚታወቀው ማተሚያ ቤቱ ሁለት ጋዜጦችን በቅርቡ ቀይ ካርድ አሳይቷቸዋል፤ ያውም ቢጫ ሳያሳይ ቀጥታ ቀይ፡፡ ቆይ ግን ምን ዓይነት “ፋዎል” ቢሠሩ ነው እንደዚህ የጨከነባቸው? በተለይ ግን የሁለተኛዋ ጋዜጣ ለምን ቀይ ካርድ እንዳየች ስትጠየቅ ከአዘጋጁ የተሰጠው መልስ በጣም አስገርሞኛል፡፡ በአንድ ጋዜጣ ተጠይቆ ሲመልስ ጋዜጣዋ የታገደችው ትክክለኛ ጽሑፍ ስላልያዘች ነው እንደተባለ ጠቅሷል፡፡ እንዴ ይህ ቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) የሚባለው ተመልሶ መጣ ብዬ ውስጤ በጣም ጠረጠረ፡፡ መልስ ግን አላገኘሁም፡፡ አይ ፌስቡክ ሳንሱር የለ፣ አላትምም የለ፣ ምን ገዶ ሐሳብን በነፃነት ቦግ ማድረግ ብቻ፡፡ ግን እነዚህ በድፍረት የሕዝብን ሮሮ የሚያስደምጡንና መንግሥት ስህተት ከሠራ አሠራሩን እንዲያስተካክል የሚተቹ ጋዜጦች ቀይ ካርድ እያዩ ካለቁ አመራሮችስ እንዴት ነው ሥራቸውን የሚገመግሙት? መስተካከል ያለበትንስ ማን ይነግራቸዋል ብዬ አሰብኩ፡፡

እውነቴን እኮ ነው መቼም ደፍሬ እነርሱም ፌስቡክ አካውንታቸው ላይ ፖስት የሚደረጉ ነገሮችን ይመልከቱ አልልም፡፡ ቢመለከቱ ስህተት ነው እያልኩ ሳይሆን በመጀመሪያ የፌስቡክ አካውንት ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ሌላው ደግሞ አካውንት ቢኖራቸውስ የፌስቡክ ጓደኞቻቸው ሌሎች ጥቂት ባለሥልጣናት እንጂ ተራው ሕዝብ ሊሆን አይችልም፡፡ ግን ይህን ቢያደርጉት ትክክለኛ የሕዝብን ስሜት መረዳት ይችሉ ነበር፡፡ እውነት ለመናገር የካድሬ ሪፖርት ብቻ ከማየት እንደ ፌስቡክ ባሉ አጋጣሚዎች የተራውን ሕዝብ ስሜት መረዳት የአመራር ብቃትን ይጨምራል እንጂ አይቀንስም፡፡ መቼም ሥራ አጥተዋል ወይ እንዳንተ ፌስቡክ የሚከፍቱልህ ልትሉኝ ትችሉ ይሆናል፡፡ ግን የሕዝብን ሐሳብ ከማየት የበለጠ ለአገር ገንቢ ነገር የለም እላለሁ፡፡

ሐሳቤን ሳጠቃልል ይህ በፌስቡክ ላይ ያለ ሐሳብንና መረጃን በነፃነት የመግለጽ ባህል ለምን በጋዜጦቻችንና በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ላይ አይዳብርም? ጋዜጦች ተዘጉብን ብለን ማማረር ብቻ ሳይሆን የቀሩትም እስኪዘጉ ድረስ ያለንን ሁሉ ሐሳብ በነፃነት ባሉት ጋዜጦቻችን መግለጽ መቻል በጣም ጠቃሚና ትምህርት ሰጪ ነው፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት የተደነገገው ለፌስቡክ ብቻ ነው? እንደኔ እንደኔ ቀይ ካርድ ባላዩ ጋዜጦቻችንና ሌሎች ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎቻችን ይህን ዕድል ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡-  ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው esksta@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር