ክልሎች ከፌዴራል መንግሥት በሚጋሯቸው ገቢዎች ላይ ጥያቄ አነሱ


በዮሐንስ አንበርብር
ክልሎች ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሚጋሯቸው የተለያዩ የገቢ ዓይነቶች መከፋፈያ ቀመር ጊዜው ያለፈበትና አሁን ያለውን የዕድገት ደረጃ ያላገናዘበ በመሆኑ እንዲሻሻል ጥያቄ አቀረቡ፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ለፌዴራል መንግሥቱ ከሚሰጣቸው ሥልጣኖች አንዱ ከክልል መንግሥታት ጋር ያለውን የጋራ ገቢ እንዲሰበስብና ለክልሎቹ የሚገባቸውን ድርሻ እንዲያስተላልፍ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የፌዴራል መንግሥትና የክልሎች የጋራ ገቢዎች የሚባሉት በሕግ ተወስነው ተለይተዋል፡፡ እነዚህም በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች የጋራ ባለቤትነት ከተመሠረቱ የልማት ድርጅቶች የሚገኝ ገቢ፣ በክልል የተመሠረቱ ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማኅበራት (ፒኤልሲ) እና በክልሎች የሚገኙ የተለያዩ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለማውጣትና ለመጠቀም ፈቃድ የተሰጣቸው ድርጅቶች ከሚከፍሉት ሮያሊቲ የሚገኝ ገቢ ናቸው፡፡

ከእነዚህ ዘርፎችና የገቢ ዓይነቶች የሚገኘውን ሀብት ክልሎች ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሚከፋፈሉት በ1989 ዓ.ም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ፀድቆ በሥራ ላይ እንዲውል በተደረገው ቀመር አማካይነት ነው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትናንትናው ዕለት ባደረገው ስብሰባ በዚህ ቀመር ላይ በዋነኝነት ተወያይቷል፡፡ የምክር ቤቱ የድጎማ፣ የበጀትና የገቢዎች ድልድል ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የክልሎችን ጥያቄ በመንተራስ፣ በዚህ ዓመት የገቢ ማከፋፈያ ቀመሩን ለመፈተሽ ዕቅድ ይዟል፡፡

የኮሚቴው ሰብሳቢ የሆኑት የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንቱ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት፣ ቀመሩ አሁንም በሥራ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ቀመሩ ግን በቂ ግንዛቤ ያልተጨበጠበት እንደሆነ፣ ባለድርሻ አካላትና ክልሎች በቀመሩ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እንዲሰጣቸውና እንዲሻሻል ተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በፌዴራልና በክልል መንግሥታት በጋራ የተመሠረተ የልማት ድርጅት ባይኖርም፣ እንዲህ ዓይነት ድርጅት ቢኖር ግን ገቢን እኩል ለእኩል መከፋፈል እንደሚቻል በቀመሩ ላይ መጠቀሱን አቶ ሽፈራው ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ይልቅ ግን ቀመሩ በክልል መንግሥታት ከተመሠረቱ የግል ንግድ ድርጅቶች የሚገኝ ገቢን፣ እንዲሁም የሮያሊቲ ክፍያን ለማከፋፈል በቀመሩ የተወሰነው ምጣኔ የክልሎች ጥያቄ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልል ከተመሠረቱ የግል ንግዶች የሚገኝ የትርፍ ግብርን 50 በመቶ ለፌዴራሉ ቀሪው 50 በመቶ ድርጅቱ ለሚገኝበት ክልል እንዲከፈል ቀመሩ የሚያዝ ሲሆን፣ ከእነዚህ ድርጅቶች የሚገኝ የአገልግሎት ኤክሳይዝ ታክስን ግን ፌዴራል መንግሥቱ 70 በመቶ እንዲወስድ፣ ለክልሎች ደግሞ ቀሪው 30 በመቶ እንዲከፋፈል ቀመሩ ያዛል፡፡

ከሮያሊቲ ክፍያ የሚገኝ ገቢን በተመለከተ ደግሞ 60 በመቶውን የፌዴራል መንግሥቱ 40 በመቶውን ደግሞ ክልሎች እንዲወስዱ ቀመሩ ያዛል ሲሉ አቶ ሽፈራው በሪፖርታቸው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በቀመሩ የተካተቱትን መስፈርቶች በተገቢው መንገድ መገምገምና አሁን ከተደረሰበት የዕድገት ደረጃ አንፃር መፈተሽ ተገቢ መሆኑን ኮሚቴው እንደሚያምንና የዚህ ዓመት ትኩረቱ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም በተገቢነቱ ላይ በማመን ተግባራዊ እንዲሆን በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/8022-2012-10-10-06-16-08.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር