ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የተቀናጀ ዘመቻ



ተስፋዬ ለማ

ከዛሬ አራት ቀን በፊት ማለትም ጥቅምት 2/2005 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ አጀንዳ አምድ በዚሁ ርዕስ ከታላላቅ የሀገራችን ልማት ሥራዎች የስኳር ልማት ፕሮጀክት እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ጽሑፍ ማቅረባችን ይታወሳል። በጽሑፉ በአገራችን በመስፋፋትና በመገንባት ላይ ያሉ ነባርና አዳዲስ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ የምትመራ በትን የግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያስችል መሠረት ለመጣል ከተያዙ ታላላቅ ሀገራዊ የኢንዱስትሪ ልማቶች በዋናነት የሚጠቀሱ መሆኑን ዳስሰናል። 
በአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሠረት ነባሮቹን የማስፋፋትና አዳዲሶች የመገንባት አቅጣጫ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ለማየትም ተሞክሯል። ከእዚሁ ጋር ተያይዞ የአገሪቱ የስኳር ፍላጎት ከሚመረተው ምርት ጋር ባለመጣጣሙ መንግሥት ከተለያዩ አገራት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ስኳር እያስገባ መሆኑን ጠቁመን ከሦስት ዓመታት በኋላ ግን አገሪቱ የሕዝቧን የስኳር ፍላጎት አሟልታ የተረፈውን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ የምታስገባበት ሁኔታ እንደሚፈጠር አይተናል። 
ከስኳር ልማት ፕሮጀክቶቹ ጋር ተያይዞ በተለያዩ ወገኖች የሚነሱ መሠረት የለሽ አሉታዊ ዘገባዎች የአገራችንን የልማት አቅጣጫ ለማስቀየስ እንጂ መሠረታዊ ጠቀሜታ ኖሯቸው እንዳልሆነና በአሁኑ ወቅት ልማታችንን ለማደናቀፍ የሚሰነዘሩ አሉባልታዎችን የሚሰማ ጆሮ ያለው ኢትዮጵያዊ አለመኖሩንም ለማስገንዘብ ተሞክሯል። የኢትዮ ጵያ ሕዝብ ዋነኛ ጠላት ድህነት መሆኑን መግባ ባት ላይ መደረሱንም ነው በመጀመሪያው ጽሑፍ የቃኘነው። 
በዛሬው ጽሑፍ በሀገራችን እየተገነቡ ካሉ አዳዲስ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክትን እንመለከታለን። 
የወልቃይት የስኳር ልማት ፕሮጀክት ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባ ነው። አካባቢው ለሸንኮራ አገዳ ተስማሚ መሆኑ በጥናት በመረጋገጡ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለመገንባት ከታቀዱት አስር አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች አንዱ በወልቃይት እንዲሆን ተደርጓል፤ ከእዚህም አኳያ ከግድቡ ጋር ተያያዥነት ያላቸው መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ ሲሆን፤ በተለይም የፕሮጀክቱ አካል የሆነው የሜይዴይ ግድብ ግንባታ በመከናወን ላይ ይገኛል። ከአካባቢው የተገኘ መረጃ እንደሚያሳ የው እስከአሁን ባለው ሁኔታ የግድቡ 10 በመቶ ያህል ሥራ ተከናውኗል። 
የሜይዴይ ግድብ የዛሬማ ወንዝን መሠረት አድርጎ እየተገነባ ነው። የግድቡ አፈር ቁፋሮ ሥራ ከ90 በመቶ በላይ ተጠናቅቋል፤ ከእዚሁ ጎን ለጎን ወንዙን የመጥለፉና የመቀየስ ሥራም ከ70 በመቶ በላይ መጠናቀቁን መረጃው ያሳያል።
የሜይዴይ ግድብ የሚያርፈው 36 ሄክታር መሬት ላይ ሲሆን፤ በግድቡ ምክንያት በውሃ የሚሸፈነው መሬት ደግሞ 9 ሺ 6 መቶ 50 ሔክታር ነው። 1 መቶ 43 ሜትር ከፍታና 7 መቶ 20 ሜትር ርዝመትም ይኖረዋል። የግድቡ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ክዩቢክ ሜትር ውሃ የመያዝ አቅም እንደሚኖረው ይገመታል። 
ግድቡ በወልቃይት የስኳር ልማት ፕሮጀክት ከሚሠሩ ግድቦች ትልቁና ወሳኙ ነው። ከእዚሁ ጎንለጎን የቃሌማ ወንዝን መሠረት አድርጎ የሚሰራ የውሃ መቀልበሻ ውቅር አለ። መቀልበሻ ውቅሩ የሜይዴይን ያህል ግዝፈት ባይኖረውም የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው ይታመናል። መቅልበሻ ውቅሩ 15 ሜትር ከፍታ ሲኖረው ግንባታው ሲጠናቀቅ 12 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የማቆር አቅም ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል። ይህ ግድብ ለእርሻ ልማት እንደሚውልና ከ3 ሺ 3 መቶ ሔክታር መሬት በላይ የማልማት አቅም እንዳለው ለማወቅ ተችሏል። 
በአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ባለፉት ሁለት ዓመታት በወልቃይት የስኳር ልማት ፕሮጀክት ለማከናወን በተያዘው ፕሮግራም መሠረት መፈጸሙ ከአካባቢው የተገኘ መረጃ ያሳያል። በሚቀሩት ሦስት ዓመታት ደግሞ አጠቃላይ የፕሮጀክቱ ግንባታ ይጠናቀቃል። ይኸው ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ከሚኖረው አስተዋጽኦ ባሻገር ለአካባቢው ነዋሪዎች ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ ይሰጣል። የአካባቢው ነዋሪዎች የሚናገሩትም ይሄንኑ ነው። 
አቶ ታደለ ይልማ እና አቶ ተጠምቀ ገ/መድን ነዋሪነታቸው በወልቃይት ወረዳ ቃሌማ ገጠር ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነው። ነዋሪዎቹ በአካባቢው እየተካሄደ ያለውን የስኳር ልማት ፕሮጀክት በሚመለከት ተጠይቀው እንደገለጹት ልማቱ ከመጀመሩ በፊት መንግሥት ከሕዝቡ ጋር ተከታታይ ውይይቶችን አድርጓል። ከተደረገው ውይይት በኋላ ኅብረተሰቡ ከልማቱ ተጠቃሚ እንደሚሆን መገንዘብ በመቻሉ ከመንግሥት ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በመሥራት ላይ ይገኛል። 
ልማቱ ለሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚሰ ጠው ጠቀሜታ ባሻገር ለአካባቢው ኅብረተሰብ የሚሰጠው የተለየ ጥቅም ምንድን ነው? ከእዚህ ልማት ጋር ተያይዞ እየተነሳ ያለው አሉባልታ መሠረቱ ምንድን ነው? የሕዝቡ ምላሽስ ምን ይመስላል? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት በልማቱ አጠቃላይ ገጽታ ላይ ግንዛቤ ለመያዝ ያግዛል። 
የወልቃይት የስኳር ልማት ፋብሪካ ተጠናቅቆ ማምረት ሲጀምር አገሪቱ ያላትን የስኳር ፍላጎት ለማሟላት ከፍተኛ አቅም ያለው ነው። ሀገራችን ከተለያዩ አገራት ወደ አገር ውስጥ ለሚገባው ስኳር የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከማዳኑም ባሻገር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ያቀደችውን የስኳር ምርት ለማሟላት የሚኖረው ድርሻ የጎላ ይሆናል። ለአካባቢው ነዋሪዎች የሚሰጠው ጠቀሜታ ደግሞ ከእዚህም በላቀ ደረጃ ሊገለጽ ይችላል። 
የአካባቢው ነዋሪዎች ከልማት ፕሮጀክቱ ከሚያገኙት ጥቅም አንዱ ሰፊ የሥራ ዕድል ነው። የወልቃይት የስኳር ፕሮጀክት ከ46 ሺ ለሚልቁ ዜጎች የሥራ ዕድልን ይፈጥራል። የስኳር ልማት ፕሮጀክቱ ሌሎች የመሠረተ ልማትና የአገልግሎት ተቋማት ግንባታ ሥራዎችን የሚያካትት በመሆኑ ከቀን ሠራተኛ እስከ ከፍተኛ መሐንዲስ ድረስ የማሳተፍ አቅም ይኖረዋል። 
በአገራችን ከሚታዩ ችግሮች መካከል አንዱ ሥራ አጥነት ነው። ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ይህን ያህል የሰው ኃይል ሊያሰማራ የሚችል ፕሮጀክት በአካባቢው መገንባቱ ለነዋሪዎቹ የበለጠ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አያጠራጥርም። 
እናም የወልቃይትና አካባቢው ሕዝብ በሚፈጠረው የሥራ ዕድል ይበልጥ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ምናልባትም ከፕሮጀክቱ ማዕድ ተቋዳሽ ይሆናሉ ተብለው ከሚገመቱ 50 ሺ ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሆኑ አያጠያይቅም። በየደረጃው በሚመጥናቸው የሥራ መስክ በመሰማራት የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን ምቹ ሁኔታ ይፈጠር ላቸዋል። 
የአካባቢው ነዋሪዎች ከፕሮጀክቱ መመሥረት ጋር በተያያዘ የሚያገኙት ሌላው ጥቅም የመስኖ ገብ እርሻን ማልማት መቻላቸው ነው። መስኖ ገብ ልማት በአገራችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተለመደ የመጣና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዝ የግብርና ልማት አማራጭ ነው። 
ቀደም ሲል በነበረው ኋላቀር ግብርና እና ዝናብን ማዕከል ያደረገ የእርሻ ልማት ክንውን አርሶ አደሩ የተሻለ ምርት ተጠቃሚ ከመሆን ይልቅ ከእጅ ወደ አፍ በሆኑ ኑሮ ሕይወቱን ለመምራት የተገደደበት ሁኔታ መፈጠሩ ይታወሳል። 
ይሁንና ካለፉት 20 ዓመታት ወዲህ አርሶ አደሩ ውሃን የማቆር ተሞክሮን እየቀሰመ መምጣቱ ተስተውሏል። የወልቃይት የስኳር ልማት ፕሮጀክትም ይህንኑ ተሞክሮ በማጠናከር ነዋሪዎች በዓመት ሦስት ጊዜ የሚያመርቱበትን ሁኔታ መፍጠር የሚያስችል ዕድል ይከፍታል። 
ለሸንኮራ አገዳ ልማት የሚገደበው ግድብ የታቀደለትን ዓላማ ከመፈጸሙም ባሻገር በዙሪያው የሚገኙ አርሶ አደሮች የእርሻ ማሳን ጭምር ያለማል። በእዚህ መልክ የአካባቢው አርሶ አደር የዝናብ ውሃ ላይ ጥገኛ ከመሆን ይድናል። ዝናብ በጠፋ ቁጥር ለድርቅ መጋለጡም አብሮ ያከትማል። 
በእዚህ መልክ የአካባቢውን አርሶ አደሮች ለዘመናት ለችግር ሲዳርግ የነበረውን ዋነኛ ችግር ማቃለል ይቻላል። የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና የገቢ አቅማቸውን ለማጠናከር ሂደቱ የጎላ ድርሻ ይኖረዋል። 
የስኳር ልማት ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ነዋሪዎች የሚኖረው ሌላው ጠቀሜታ እንስሳትን ለማርባትና ለማድለብ አመች ሁኔታ መፍጠሩ ነው። የፋብሪካውን ተረፈ ምርት በመጠቀም የአካባቢው ነዋሪዎች እንስሳትን በማርባትና በማድለብ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ። በግድቡ ምክንያት በሚፈጠረው ሐይቅም ዓሣን በማምረት ተጨማሪ ጥቅም ያገኛሉ። 
በአብዛኛው የአገራችን ክፍል ዓሣን አምርቶ መጠቀም የተለመደ አይደለም። ይህ እየሆነ ያለው ከሁለት መነሻ ነው። አንደኛው ምክንያት ሐይቆችና ትላልቅ ወንዞች ያሉባቸው አካባቢዎች ውስን ናቸው። በሌላ በኩል የግንዛቤ ችግር አለ። ሐይቆች ባሉባቸው አካባቢዎች ያለው የዓሣ ምርትም ቢሆን አገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ያህል ጥቅም እየሰጠ እንዳልሆነ ይታወቃል። 
ይሁንና በወልቃይት የስኳር ልማት ፕሮጀክት በሚገነቡ ሰው ሠራሽ ሐይቆች ዓሣን በሰፊው ለማምረት የሚያስችል ሁኔታ ይፈጠራል። የአካባቢው ሕዝብ ዓሣን ለምግብ አማራጭነት ከመጠቀም አልፎ ለገቢ ማስገኛ ሊጠቀምበት የሚያስችል ሁኔታ ይኖራል። 
በወልቃይት እየተካሄደ ያለው ልማት የዋልድባ ገዳምን ፍፁም የማይነካ ነው። ይልቁንም የገዳሙ ማኅበረሰብ እንደሌላው የአካባቢው ሕዝብ ተጠቃሚ ከመሆን ባሻገር በሚገነባው መሠረተ ልማት ምክንያት የገዳሙ ጎብኚዎች ቁጥር እያደገ ስለሚመጣ የአካባቢው ገቢ በእዚያው ልክ ስለሚጨምር መነኮሳቱ የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናሉ። 
ከእዚህም በተጨማሪ የገዳሙ ማኅበረሰብ በመስኖ በመጠቀም የእርሻ ምርቱን በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ ለማምረት ዕድል ይፈጠርለታል። ስለሆነም የዋልድባ ማኅበረሰብ ከልማቱ ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ የሚሆንበት ዕድል የለም። 
እስከአሁን ባለው መረጃ መንግሥት በስኳር ልማት ፕሮጀክቱ 3 ሺ 5መቶ ያህል የሠራተኞች መኖሪያና 82 የአገልግሎት መስጫ ይገነባል። በስኳር ልማት ምክንያት ለሚነሱ ነዋሪዎች ደግሞ ከ5 ሺ በላይ ቤቶች ይገነባሉ። የመንገድ፣ የመብራት፣ የስልክ እና የንጹሕ መጠጥ ውሃ አገልግሎቶችም ይዘረጋሉ፤ ግንባታው ትምህርት ቤቶችና ጤና ተቋማትንም ያካትታል። 
ከእዚህም አኳያ በአካባቢው አስራ አንድ የገጠር መንደሮችና አንድ ከተማ ይመሠረታል፤ አራት ትምህርት ቤቶች፣ አንድ ደረጃውን የጠበቀ ጤና ጣቢያ፣ አስራ ሁለት መካከለኛ ጥልቀት ያላቸው የመጠጥ ውሃ ጉድጓዶች እና አስራ ስድስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ይገነባሉ። 
የስኳር ልማት ፕሮጀክቱ ከተጀመረ አንስቶ አንዳንዶች ብዥታ ለመፍጠር ቢሞክሩም ልማቱ የሕዝብ ድጋፍ አልተለየውም። በተለያዩ ጊዜያት በተካሄዱ የምክክር መድረኮች የልማቱ አስፈ ላጊነት በሕዝቡ ዘንድ በሰፈው ሰርጿል። ሕዝቡ ልማቱን ለማፋጠን ከመንግሥት ጋር ተባብሮ እየሠራም ይገኛል። 
እውነታው ይህ ሆኖ እያለ የዋልድባ ገዳምን አስታኮ እየተነሳ ያለው መሠረት የለሽ ወሬና አሉባልታ ሃይማኖትን ለፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ መሣሪያ አድርጎ የመጠቀም አባዜ ነው። 
በዋልድባ ገዳም ጉዳይ እየተነዛ ያለው ውዥንብር ከፖለቲካ ፍላጎት የመነጨ እንጂ በገዳሙ ላይ የደረሰ ተጨባጭ ችግር በመኖሩ እየተሰጠ ያለ አስተያየት አይደለም። ጉዳዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሃይማኖቱ ቀናኢ መሆኑን የተገነዘቡ፣ ነገር ግን ልማትና ብልጽግናችንን ማየት የሚያማቸው ብጥብጥ ናፋቂ ኃይሎች ልማታችንን ለማደናቀፍ እያቀነባበሩ የሚያቀር ቡት ዘመቻ ነው። 
ያም ሆኖ ልማቱን በማስተጓጎል ላይ ያነጣ ጠረው ዘመቻ በሀገራችን ሕዝብም ሆነ አጀንዳው በቀጥታ በተነጣጠረበት የወልቃይት ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የለውም። እንዲያውም የአካባቢው ነዋሪዎች ሕዝቡ በፈጠራና በሐሰት ፕሮፓጋንዳ የማይወናበድ መሆኑን ጠንከር አድርገው ይገልጻሉ።
አቶ ተጠምቀ ገ/መድን ይህንን አስመልክቶ ሲናገሩ፤ ልማቱ የራሳችን፣ ተጠቃሚዎችም እኛው መሆናችንን ያወቅነው አሁን ሳይሆን ገና ልማቱን ለመጀመር በታሰበበት ወቅት ባደረግነው ውይይት ነበር። ያኔ በልማቱ ዙሪያ ከመንግሥት አካላት ጋር ተከታታይ ውይይቶችን ባካሄድንበት ወቅት በቂ ግንዛቤ አግኝተናል ይላሉ። የስኳር ልማቱ በቀጥታ ከሚሰጠን ጥቅም ባሻገር ከእዚሁ ጋር ተያይዞ ከሚስፋፋው መሠረተ ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚዎች እንሆናለን ብለዋል።
እንደ ነዋሪዎቹ እምነት ከስኳር ፕሮጀክቱ ጋር የተያያዘው ልማት በመስኖ፣ በዓሣ ምርትና በእንስሳት ማድለብ ተግባራት በመሳተፍ ኑሯቸውን ለማሻሻል ያስችላቸዋል። ስለሆነም ልማቱን በሙሉ ልብ ይደግፋሉ። 
የወልቃይት ስኳር ልማት ከአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የቀጣይ ሦስት ዓመትን ትኩረት በተጠናከረ መልክ በመተግበር አገራችንን ከድህነት ለማላቀቅና መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ የተጀመረውን የተቀናጀ ዘመቻ ያጠናክራል። በአካባቢው መሠረተ ልማት መሟላትና ሌሎች ተቋማት መገንባትም የሕዝቡ ኑሮና ዕድገት ይሻሻላል፤ ይቀየራልም። ስለሆነም ከስኳር ፕሮጀክቱ ስኬት አኳያ በቀጣይ ሦስት ዓመታት የተጀመረውን ልማት አጠናክሮ መቀጠል ያሻል። 
የሰሜኑ የአገራችን ክፍል ለበርካታ ዓመታት በድርቅ የተጎዳ ነው። ተፈጥሮ ያደለውን ጸጋ በሚገባ መጠቀም የሚያስችለው ዕድልም ጠባብ ነበር። በተለይ በቅድመ 1983 የወልቃይትና አካባቢው ሕዝብ ለከፍተኛ ረሃብ፣ ስደትና ስቃይ ይዳረግ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። አሁን ላይ ሆነን በቀደሙት ሥርዓታት የነበረውን ሕዝብ ሁኔታ ስናስታውስ በእዚያን ወቅት ኖረንና ዓይተነው ካልሆነ በስተቀር ለማመን እንቸገር ይሆናል። 
የአካባቢው ሕዝብ የዕለት ጉርሱን ለመሸፈን ተቸግሮ ይሰደድ ከነበረበት ዘመን ወጥቶ አሁን ውሃ የማቆርና የእርሻ ልማትን በማጧጧፍ ሥራ ተጠምዷል። ከእዚሁ ጎን ለጎን ዘመናዊ የእንስሳት እርባታን በማስፋፋት ተጠቃሚ እየሆነ ይገኛል። 
አሁን በአካባቢው እየተገነባ ያለው የስኳር ልማት ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ደግሞ የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆን በቂ ግንዛቤ አግኝቷል። ለእዚህም ነው ሕዝቡ ልማቱን ለማፋጠን ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ የሚገኘው። 
እስከአሁን ያለው የመንግሥትና የሕዝባችን የተቀናጀ ተሞክሮ በድህነት ላይ ያነጣጠረው የተቀናጀ የፀረ ድህነት ዘመቻ ያለምንም እንከን በውጤት የሚደመደም ለመሆኑ አመላካች ነው። ሕዝቡ በባለራዕዩ የሀገራችን መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ቀያሽነት የተጀመሩና በስኬት እየቀጠሉ ያሉ ታላላቅ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ለማስፈፀም ቁርጠኝነቱን ያረጋገጠ በመሆኑም መጪው ጊዜ የዘላቂና ፈጣን ዕድገታችን ዘመን ለመሆኑ ጥርጥር የለንም። እናም ሕዝባችን በመሠረተ ቢስ ፈጠራና አሉባልታ ሳይዘናጋ ለሀገሩና ለተጠቃሚነቱ ርብርቡን እያጠናከረ የማደግና የመለወጥ ትልሙን ያሳካል። 
http://www.ethpress.gov.et/ethpress/main/viewsOpinion.php

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር