በሀገሪቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በማዕድን ፍለጋና ልማት ላይ ተሰማርተዋል


ሃዋሳ ጥቅምት 09/2005 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በማዕድን ፍለጋና ልማት ላይ መሰማራታቸውን የማዕድን ሚኒስትሯ ገለጹ፡፡ ስለማዕድን ኢንዱስትሪ ግልጽነት ኢኒሼቲቭ አሰራር ለበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ግንዛቤ ለማስጨበጥ በሀዋሳ ከተማ ትናንት በተዘጋጀው አውደ ጥናት ላይ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ስንቅነሽ እጅጉ እንደገለጹት ባለሀብቶቹ በዑጋዴን፣ በመቀሌ፣ በአባይ፣ በኦሞና በጋምቤላ በርካታ ኩባንያዎች በማዕድን ቆፋሮ ላይ ተሰማርተዋል፡፡

ማዳበሪያ፣ መስተዋት፣ ሳሙናና ሌሎችን ለማምረት በግብዓትነት የሚጠቅሙ በርካታ የማዕድን ሃብቶች እንዳሉ ያስረዱት ሚኒስትሯ በነዳጅ ዘርፍም በተለያዩ ሥፍራዎች ፍለጋው መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡ 
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው የምርት ዓይነቶች የማዕድን ሃብት 20 በመቶውን እንደሚይዝና ለሀገሪቱ ዘላቂ ልማት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማጎልበት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ብቻ የወርቅ ፣ የታንተለም፣ የጌጣጌጥና የመሳሰሉት የማዕድን ጥሬ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ከ460 ሚልዮን በላይ ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱንና በዚሀ ዓመትም ይህንን በእጥፍ ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በማዕድን ፍለጋና ምርመራ ስራ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት ሀገር ናት ያሉት ሚኒስትሯ የማዕድን ሃብት አለኝታ ጥናት በተለያዩ ወቅቶች በውጭና በሀገር ውስጥ የስነ ምድር ባለሙያዎች ሲከናወን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ እስከአሁን በተደረጉ ጥናቶች የኢንዱስትሪ፣ የኮንስትራክሽን፣ የጌጣ ጌጥ ፣ የወርቅ፣ የብረታ ብረት፣ የሃይድሮ ካርቦን ክምችትና የጂኦተርማል ማዕድናት መኖራቸው መረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡ 
የማዕድን ኢንዱስትሪ ግልጽነት ኢንሼቲቭ አላማ ኩባንያዎች አምርተው ከሚያገኙት ገቢ ለመንግስት የሚከፍሉትና መንግስትም ከኩባንያዎች የሚቀበለውን ገቢ በግልፅነት ለማስተዳደርና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡ 
የኢትዮጵያ መንግስት የማዕድን ሃብታችንን ለህዝብ ጥቅም ለማዋል ከባለድርሻ አካላት ጋር ስምምነት በመፍጠርና በጋራ በመስራት የማዕድን ኢንዱስትሪ ግልፅነት ኢንሼቲቭ አሰራሩን ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኝነት እንዳለውም አስረድተዋል፡፡
 በዓለም አቀፍ የኢንሼቲቩ መመሪያና መስፈርት መሰረት ከመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ከማዕድን አምራች ኩባንያዎች የተውጣጣ 15 አባላት ያቀፈ ብሄራዊ ስቲሪንግ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ ከገባ ሶስት ዓመት ማስቆጠሩን ተናግረዋል፡፡ የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ በማዳበርም ለማዕድን አምራች ኩባንያዎች፣ ለማዕድን ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች፣ ለፌዴራልና ለክልል ፍቃድ ሰጪና ገቢ ሰብሳቢ መስሪያ ቤቶች በአዲስ አበባና በአዳማ በቅርቡ ስልጠና መስጠቱን አስረድተዋል፡፡ 
በተፈጥሮ ሃብታችን ዙሪያ የግልፅነትና የተጠያቂነት አሰራር ለማስፈን ብሎም ዘርፉ ለሀገሪቱ ዘላቂ ልማት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማበርከት መንግስት ትኩረት መስጠቱንም ተናግረዋል፡፡ በሀዋሳ ከተማ ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው አውደ ጥናት ላይ 80 የሚጠጉ የሲቪል ማህበራትና ድርጅት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር