የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማቃለል አገራዊ የህዝብ ንቅናቄ ይካሄዳል



አዲስ አበባ፡-በየሥራ መስኩ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማቃለል የሚያስችል ሕዝባዊና አገራዊ ንቅናቄ በተያዘው ዓመት እንደሚካሄድ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ አስታወቁ።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ትናንት የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የአራተኛ ዙር የሥራ ዘመን ሦስተኛ ዓመት የጋራ ስብሰባ በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማስወገድና የተገኙ ስኬቶችን ለማስጠበቅ የሚያስችል አገራዊ እንቅስቃሴ በዚህ ዓመት ይካሄዳል። በአገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው መልካም አስተዳደርን የማጐልበት ሕዝባዊ ንቅናቄ የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸ ውን ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል።
ሕዝባዊና አገራዊ ንቅናቄው በአሁኑ ወቅት በተጨባጭ የሚታዩ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት የመፍታትና የሕዝብን እርካታ የማረጋገጥ ግብ ያለው መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አመልክተው፤ ለዚህ ግብ መሳካት ሁሉም ሕዝብ በንቃትና በተደጋጋፊነት እንዲሣተፍና የመልካም አስተዳደር ራዕዩን እውንነት እንዲረጋገጥ የዘርፉ ተዋናዮች ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ፤ ላለፉት 21 ዓመታት በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊና መልካም አስተዳደር የሰፈነበት ሥርዓት ለመገንባት በተደረገው ጥረት የዜጎችና የሕዝቦችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማስከበር ሰፊ እንቅስቃሴ ተደርጓል። ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በፅናት ከማክበር ጀምሮ በነፃ የሕዝብ ምርጫ መንግሥትን እስከመመሥረት ድረስ በርካታ መሠረታዊ የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ተግባራት ተከናውነዋል።
ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስጠበቅና ለማጠናከር ሲባል የተቋቋሙት በየደረጃው ያሉት ምክር ቤቶች፣ የሕግ ተርጓሚና የአስፈፃሚው አካላት በሀገሪቱ የግልፅነትና የተጠያቂነት ሥርዓትን ከማጠናከራቸውም በላይ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው በአስተማማኝነት እንዲቀጥል ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን አስታውሰዋል።
በዚህም ላለፉት ዓመታት የተጀመረው የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ በተቀመጠለት አቅጣጫ መሠረት እንዲፈፀም መደረጉን የገለጹት ፕሬዚዳንት ግርማ፤ የሕዝቡን ቀጥተኛ ተሣትፎ ለማረጋገጥ ልዩ ልዩ መድረኮች ለመክፈት መቻሉ ለዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ መዳበር ዓይነተኛ አስተዋፅኦ እንደነበረው አመልክተዋል።
በተመሳሳይም ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ሕጋዊ ዋስትና አግኝቶ በተግባር እንዲተረጐም ጥረት መደረጉን ጠቁመው፤ በመድብለ ፓርቲ ሕልውናና ውድድር ላይ የተመሠረተ መንግሥት ለመመሥረት በየአምስት ዓመቱ አገር አቀፍና የአካባቢ ምርጫ በነፃና ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን አውስተዋል።
በዚህም መሠረት ዘንድሮ በሚካሄዱት የማሟያ ምርጫን ጨምሮ በአዲስ አበባና በሁሉም ክልሎች የቀበሌና የወረዳ እንዲሁም በአንዳንድ ክልሎች ደግሞ የዞን ምርጫዎች የሀገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌውን አክብረው በመወዳደር ዴሞክራሲውን እንደገና አንድ እርምጃ ወደፊት ያራምዱታል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን አመልክ ተዋል።
በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊ ልማትን ከማስፈን አኳያ ከፍተኛ መሻሻሎችና እድገቶች መመዝገባቸውን ፕሬዚዳንቱ አመልክተው፤ በተለይም በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ቀያሽነት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ተግባራዊ ከሆነበት ከ2003 ዓ.ም ወዲህ እንደተለመደው በየዓመቱ ከ11 ነጥብ 7 በመቶ እድገት መመዝገቡን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት የግብርና ልማትን ለማፋጠን በክልልና በፌዴራል ደረጃ ከመቼውም ጊዜ የላቀ ተመጋጋቢ ሥራ መከናወኑን አስታውሰው፤ የግብርና ልማቱን ለማስጠበቅ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች በስፋት መከናወናቸውን አስረድተዋል። ከሕዝቡ ጋር ለመመካከር በተካሄደው የልማት ሥራ አርሶ አደሩ በዓመቱ በአማካይ ከአርባ እስከ ሃምሳ ቀናት የሚደርስ ነፃ የጉልበት አገልግሎት ማበርከቱን ጠቁመዋል።
በመሆኑም በበጀት ዓመቱ በአቶ መለስ ዜናዊ መሪነት በተካሄደው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ አርሶ አደሩ በቆፈራቸው የውሃ ማስረጊያና ማቆያ ጉድጓዶች አስተማማኝ የውሃ ባንክ እንዲኖር መሠረት መጣሉን አመልክተዋል።
የማዳበሪያና ምርጥ ዘር ተጠቃሚነት ዕድገት እንዲያሳይ በመደረጉና አርሶ አደሩ ዘመናዊ የግብርና ዘዴዎችን በተሻለ ደረጃ በመጠቀሙ በተያዘው ዓመት ከዘርፉ የተሻለ የምርት ጭማሪ እንደሚጠበቅ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
መንግሥት በከተሞችም የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች እንዲስፋፋ አመራር ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው፤ በተለይም በከተሞች አካባቢ ያለውን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን ገልጸዋል።
በዚህም ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድሎች መፈጠራቸውን አመልክተው፤ መንግሥት በሀገሪቱ ፈጣንና ሕዝቡ የሚጠቀምበትን ልማት ለማስቀጠል እንዲቻል የመሠረተ ልማት አቅርቦቶችን ለማሟላት ጥረት ሲያደርግ በመቆየቱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ የቴሌ ኮም አውታሮች ዝርጋታና የመንገድ ልማት ሥራዎች ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ እድገትና መሻሻል ማሳየታቸውን አስረድተዋል።
የዜጐችን የቁጠባ ባህል ለማሳደግና አገራዊ የልማት ጥረቱን የሚደግፍ የፋይናንስ አቅም ለመገንባት በተካሄደው ጥረት የአገር ውስጥ ቁጠባ ላይ መልካም መሻሻል መታየቱን ጠቁመዋል። 
http://www.ethpress.gov.et/ethpress/main/news.php?newsLocation=home&newsInstruction=headline&newsId=9552

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር