የፖለቲካ ባህላችንን እንፈትሽ


በበላይ ዓለሙ
ይህችን አጭር ጽሑፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ ጳጉሜን 3 ቀን 2004 ዓ.ም. ማታ በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጣቢያ የተላለፈው የአቶ ተስፋዬ ሐቢሶና የቅንጅት አባል የሆኑ ግለሰብ ውይይት ነው፡፡ ከጳጉሜን 3 ቀን በፊት ሁለት ግለሰቦች ያደረጉት ውይይት ካለ አልሰማሁምና አስተያየት መስጠት አልችልም፡፡

በዕለቱ በተደረገው ውይይት ሁለት ተፃራሪ ስሜቶች ናቸው የተሰሙኝ፡፡ አንደኛው መልካም ስሜት ሲሆን፣ ሌላኛው ግን ተቃዋሚዎቻችን እነዚህ ናቸው? እነዚህ ናቸው የአገራችን ተስፋዎች? የሚል የተስፋ መቁረጥ ስሜት ነው፡፡ በእርግጥ የቅንጅቱ አባል የተናገሩት የግል አቋማቸውን ይሁን የድርጅታቸውን መለየት ቢያስቸግርም፣ የሳቸውን የሚመስል ተመሳሳይ አቋም ከሌሎችም አንቱ ከተሰኙ ተቃዋሚዎች የሰማሁ ስለሆነ፣ የድርጅቱ አቋም ሊሆን ይችላል የሚል ኃይለኛ ጥርጣሬ ጭሮብኛል፡፡

የምሽቱ ውይይት ያተኮረው በቅርቡ በሞት የተለዩንን የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን አመራርን በተመለከተ ነበር፡፡ በእርግጥ አቶ መለስ ዜናዊን የሚያደንቋቸው ብዙ ኢትዮጵያውያንና የውጭ አገር ዜጎች እንዳሉ ሁሉ፣ በኃይለኛ የሚነቅፏቸውም በርካቶች ናቸው፡፡ በእነዚህ ሁለት ጽንፎች መሀል ያሉም አሉ፡፡

በምሽቱ በተደረገው ውይይት አቶ ተስፋዬ የኢሕአዴግ አባልና ደጋፊ ሳይሆኑ ስለ አቶ መለስ የሰጡት አስተያየት እጅግ አስደምሞኛል፡፡ በአንፃሩ የቅንጅት አባሉ የሰጡት አስተያየት እኚህ ሰው በእውነት የኢትዮጵያን ሁኔታ የተረዱ ሰው ናቸው ወይ? በእንደዚህ ዓይነት የተሳሳተ አመለካከት ነው ወይ አገርን መምራትና ሕዝብን ማሰለፍ የሚቻለው? አስብሎኛል፡፡ የጠራ የፖለቲካ መስመር ተጨባጩን አገር አቀፋዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታን በትክክል ከመገንዘብ ስለሚመነጭ፣ ምን ዓይነት መስመር ይሆን እነዚህ የተቃዋሚ ድርጅቶች የሚቀይሱልን የሚል ሥጋት አሳድሮብኛል፡፡

‹‹አቶ መለስ ዜናዊና ድርጅታቸው ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ከሞላ ጎደል አስከብረዋል፤ በአገሪቱ አንፃራዊ ሰላም አስፍነዋል፤ ከዜሮ በታች የነበረውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ሊካድ በማይቻል መልኩ አሳድገዋል፤ በአጎራባች አገሮች የሰላምን ተልዕኮ ፈጽመዋል፤ በታላላቅ የዓለም መድረኮች የአፍሪካና የኢትዮጵያ አፍ ሆነው አስደናቂ ሥራ ሠርተዋል፤ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት እንዲኖራት አድርገዋል፤›› ሲሉ ነበር አቶ ተስፋዬ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አመራር ያላቸውን ግንዛቤ ያቀረቡት፡፡ ‹‹ከዚህ በተጨማሪም የአቶ መለስ መንግሥት ጎደሎ የሌለው መንግሥት ነው ብዬ አላምንም፤ ሊሠሩ፣ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉ ሁነው አገር መምራት ቀላል እንዳልሆነ ልናውቅ ይገባናል፡፡ መልካም የሆኑትን መካድ ወይም አክብሮት አለመስጠት አይጠቅምም፤ የጎደለውን ደግሞ መሙላት የኢሕአዴግ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ኃላፊነት ነው፤›› ሲሉ ነበር ሐሳባቸውን ከሞላ ጎደል ያቀረቡት፡፡

ውይይታቸውን ያደመጠ አንድ ግለሰብ ኢሕአዴግ ዲሞክራሲያዊ ነው ብለው ያምናሉ ወይ ከሆነስ እንዴት? ካልሆነስ ለምን ሊሆን አልቻለም? ብሎ ለጠየቃቸው ሲመልሱ፣ ‹‹እኔ የኢሕአዴግ አባል ስላልሆንኩ ድርጅቱ ዲሞክራሲያዊ ይሁን አይሁን አላውቅም፡፡ በአገራችን ዲሞክራሲ እንዳይስፋፋ ችግር የሆነው ኋላቀርነታችን ጭምር ነው፡፡ ዲሞክራሲ የሕይወት ዘይቤ ነው ስለዚህ ኋላቀር በሆነ ኅብረሰብ ዲሞክራሲን ማስፈን ከባድ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የቅንጅቱ አባል ለዚህ ለአቶ ተስፋዬ አስተያየት የሚሉት ነበራቸው፡፡ ‹‹አቶ መለስ ለአገር ዳር ድንበር ግድ የማይሰኙ ኢትዮጵያዊነታቸው የሚያጠራጥር መሪ ነበሩ፡፡ አገሪቷዋንም በዘር ከፋፍለው ከአንድነትና ከሰላም ይልቅ መለያየትንና ግጭትን ያሰፈኑ፣ ከአገራቸው አልፈው በሌሎች አገሮች የውስጥ ጉዳይ እየገቡ አገርን የወረሩ መሪ ናቸው፡፡ ለሰላም የተላከውም የኢትዮጵያን ጦር በዶላር የሚያከራዩ ከመሆናቸው ባሻገር የአገሪቱም ኢኮኖሚ አደገ ለማለት አይቻልም፤ የተሠራው መንገድና ፎቅ ነው፡፡

እውነተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ከጠቅላይ ሚኒስትሩም እንደሰማሁት ኢንዱስትሪ በብዛት ሲኖር ነው፡፡ የዓለም መሪዎችም በተለይ የአፍሪካ መሪዎች አቶ መለስን ቢያደንቋቸው አይደንቀኝም፤ አምባገነን አምባገነንን ማድነቁ አዲስ አይደለም፤›› ብለዋል ከሞላ ጎደል፡፡

ይህን ጽሑፍ የማዘጋጀት ሐሳብ ስላልነበረኝ ውይይታቸውን በድምፅ መቅረጫ አልቀረፅኩትም፡፡ ስለዚህም አንኳር ሐሳባቸውን እንጂ ሁሉን ነገር መዳሰስ ስላልቻልኩ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡

ከዚህ በመቀጠል በዚህ ላይና በተዛማጅ ሐሳቦች ላይ ያለኝን ሐሳብ በጥቂቱ አቀርባለሁ፡፡ ዓላማዬ የኢሕአዴግን ፖሊሲና ዕቅድ የማብራራት፣ ደግሞም በምሽቱ ለተነሱት ነጥቦች ሁለ አመለካከቴን ለማቅረብ ሳይሆን የፖለቲካ ባህላችንን እንድንፈትሽ በጥቂቱ ለማሳየት ነው፡፡

መቼም አቶ መለስና ድርጅታቸው ኢሕአዴግ ምንም መልካም ነገር ለኢትዮጵያ አላደረጉም የሚል ግለሰብም ሆነ ድርጅት ካለ፣ በእርግጠኝነት መናገር የምችለው እየተነጋገርን ያለነው ይህች ኢትዮጵያ ብለን የምንጠራት እኛ የተወለድንባት፣ ያደግንባትና አሁን እየኖርንባት ያለችውን በምሥራቅ አፍሪካ በምትገኘው አገር ሳይሆን፣ ሌላ ደግሞም አቶ መለስና ድርጅታቸው ይህችን አገራችን ኢትዮጵያ እያልን የምንጠራትን እየመራ ያለ ድርጅት ሳይሆን ሌላና የሌላ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡

አቶ መለስና ድርጅታቸው ኢሕአዴግ ፋሽስታዊ ደርግን ለመጣል በተደረገው መራራ ትግል ውስጥ ግንባር ቀደሙን ሥፍራ የያዙ ናቸው፡፡ ይህን የተከፈለ ዋጋ ማጣጣልና ለድርጅቱም የሚገባውን የክብር ሥፍራ አለመስጠት ከፍፁም ጥላቻ የሚመነጭ አመለካከት ወይም ደርግ ኢሠፓነት ነው እንጂ ሌላ አልለውም፡፡ ትውልድ እንደ ውሻ አስከሬኑ በአስፋልት ላይ ሲጣል፣ የሕዝቦች ደም በየገደሉና ሜዳው ሲፈስ፣ ወላጆች ጠዋሪ ቀባሪያቸውን በርስ በእርስ ጦርነት ሲያጡ፣ ሕዝብ ያለ ፍርድ ሲታረድ፣ ትግል ብለው የጀመሩ ድርጅቶችን በአንድም በሌላ ምክንያት ደርግ ቁርስና ምሳ ሲያደርጋቸውና ሲፈራርሱ፣ የተረፈው ኑሮውን ለማሳካት ትግል በቃኝ እያለ ወደ አሜሪካና አውሮፓ ሲያቀና፣ ከአገር መውጣት ያልቻለውም ወደ ዩኒቨርሲቲውና ወደየሥራው ገብቶ ኑሮውን ሲያሞቅ፣ በፅናትና ተስፋ ባለመቁረጥ የትግል መስመርን ቀይሶ ግዙፉን የደርግ ሠራዊት ያሽመደመደና የደርግ መንግሥትን የደመሰሰው ኢሕአዴግ ነው! ይህን መካድ ለዚህ ስኬት ለተከፈለው ዋጋ ዕውቅና አለመስጠትና የሚያሳዝን ነገር ነው፡፡ የብዙዎቹ የ60ዎቹ ፖለቲከኞች ትልቁ በሽታ ይህ ነው፡፡

መልካም የሆኑትን የተቃዋሚ ድርጅት ክንውኖችን ጎሽ አለማለት፡፡ ጭፍን የሆነ ድጋፍና ጭፍን የሆነ የተቃውሞ ባህል፡፡ ይህ በሽታ ዛሬም መኖሩን ስመለከት ለልጆቻችን የምናወርሰው ባህል ይህንኑ ነው? እላለሁ፡፡

በአገሪቱና በአካባቢው አገሮች ሰላምን ለማስፈን የተደረገውን ጥረት ዶላር ለማግኘት የተደረገ ዕርምጃ ነው ብሎ መደምደም አስቸጋሪ ነው፡፡ መቼም የሰላም አስከባሪው ኃይል በነፃ ይሰማራ የሚል ጥያቄ ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡

‹‹የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር›› ተብሎ የለ? ለምን ተኬደ የሚባል ከሆነም ያሳዝናል፡፡ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን በዘመነ ሥልጣናቸው ከሚያዝኑበት ነገር አንዱ በቱትሲና በጡቱ ጎሳዎች መካከል በተደረገው የ100 ቀን ግጭት ወደ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ሲያልቁ መንግሥታቸው ምንም ለማድረጉ እንደሆነ እኚሁ መሪ ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ ገልጸዋል፡፡ ለአፍሪካውያን ወገኖቻችን ሰላም የድርሻችንን ብናደርግ ሌላው ቢቀር ከሞራል አንፃር እንኳን ተገቢ ብቻ ሳይሆን የሚያኮራ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ሶማሊያን በተመለከተ አቶ መለስና ድርጅታቸው የወሰዱት አቋምና ዕርምጃ አግባብነት ያለው፣ ይህም ዕርምጃቸው ኢትዮጵያ በፀረ ሽብርተኝነት ላይ ያላትን ፅኑ አቋም ለዓለም ኅብረተሰብ ያሳየችበትና ደምቃ የወጣችበት ነው፡፡ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል፣ በፖስታ ቤት፣ በየታክሲው፣ በሐረር ራስ ሆቴልና በሌሎችም ሥፍራዎች አሊትሃድ የሽብር ተግባር ሲፈጽም ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ነበር ወደ ሶማሊያ የተገባው፡፡

በወቅቱም አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች አገሮች ዕርምጃውን በፅኑ ቢቃወሙም የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ብቻ ሳይወሰን፣ ችግሩን ለዓለም ኅብረተሰብ ለማሳየት ያላሰለሰ ጥረት አድርጎ በኋላም የችግሩን እውነተኛነትና አደጋ የተገነዘበው የዓለም ኅብረተሰብ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን ሊቆም ችሏል፡፡ አልሸባብ የተባለው ሽብርተኛ ቡድን በኢትዮጵያ ላይ የጅሃድ ጦርነት በይፋ ሲያውጅ እንደ ኢትዮጵያዊ ይህንን ድርጅት ለመዋጋት አለመቆምና የተወሰደውን ዕርምጃ አለመደገፍ የታሪክ ስህተትን መድገም ነው (በኢትዮ ኤርትራና በደርግ ጊዜ በተካሄደው የኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት ወቅት የአንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶችን አቋም ያስቧል)፡፡

የኢትዮጵያና የአፍሪካ ኅብረት ጦር አልሸባብን በመዋጋትና በሶማሊያ ሰላምን አስፍኖ ወደ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንድትጓዝ ለተከፈለው የደም ዋጋ የሶማሊያ ሕዝብ የኢትዮጵያና የሌሎች አፍሪካ አገሮች ውለታ አለበት፡፡

ስለ ኢኮኖሚው ዕድገት እውነተኛነት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በመንገድ፣ በእርሻ፣ በኢንዱስትሪና በሌሎችም የተገኘውን ዓለም ሁሉ የመሰከረው ስለሆነ እዚህ ላይ ማንሳት አያስፈልገኝም፡፡

ሌላው ያልተገጸው የአቶ መለስና ድርጅታቸው ኢሕአዴግ ሊመሰገኑበት የሚገባው ክንውን የሃይማኖት ነፃነትና ከአገር ወደ አገር የመዘዋወርን ነፃነትን ማስከበራቸው ነው፡፡ ከአገር ወደ አገር መዘዋወርን በተመለከተ የተገኘውን ነፃነት ያጣጣሙት በአሜሪካና በአውሮፓ ያሉት ወገኖቻችን ስለሚያውቁት ብተወው ይሻላል፡፡

በደርግ ዘመን እንኳን ከኢትዮጵያ ውጭ በአገር ውስጥም ጉዞ አስቸጋሪ እንደነበር አንረሳም፡፡ በደርግ ዘመን የአምልኮ ነፃነታቸውን ተነፍገው ንብረታቸው የተወረሰባቸውና ለእስር ሲዳረጉ የነበሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችና ቤተ እምነቶች ለተሰጣቸው የእምነት ነፃነት በመጀመርያ ፈጣሪያቸውን፣ ቀጥለውም አቶ መለስንና ድርጅታቸውን ከልብ ያመሰግናሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕመማቸው ድነው ወደ አገር እንዲመለሱ ማንም ሳያስገድዳቸውና ሳይቀሰቅሳቸው በፈቃዳቸው ያደርጉ የነበረውን በዕንባ የተሞላ ፀሎት የተመለከተ ሰው፣ ይህ ሕዝብ ውለታውን የማይረሳ ነው የሚያስብል ነው፡፡

በዚህ መካከል ደግሞ አቶ መለስና ድርጅታቸው ኢሕአዴግ ሊያደርጓቸው የማይገቡ፣ ደግሞም ሊሠሯቸው የሚገቡ ለአገር የሚጠቅሙ ክንውኖች እንዳሉ አለመቀበል ደግሞ የዚያኑ ያህል ጭፍን ደጋፊነትን ያሳያል፡፡ ዲሞክራሲን ከዚህ በላይ መገንባት ከኢሕአዴግ ብዙ ይጠበቃል፤ ጥቅሙ ለሁሉም ነው፡፡ ይህን ተገንዝቦ በሚያልፍ ሕይወት የማያልፍ ታሪክ ሠርቶ ማለፍ እንዴት ያስደስት ይሆን?

አቶ ተስፋዬ ዲሞክራሲ በአገራችን እንደሚገባው ያላደገበት ምክንያት በኋላቀር ባህላችን ነው ያሉትን እስማማለሁ፡፡ ይህ ደግሞ የቅንጅቱ አባል እንዳሉት ሕዝብን መናቅ አይደለም፡፡ እንዲያውም ሕዝብ ያልሆነውን ነህ ማለት ይመስለኛል ንቀት፡፡ እያሞኘኸው እንደሆነ እንደማይረዳ ቆጥረኸዋልና፡፡

በአገራችን ዲሞክራሲያዊ ባህል እንዳያድግ ካደረጉት ተጨማሪ ምክንያቶች አንዱ ፖለቲከኞቻችን በማርክሳዊ ሌኒናዊ ርዕዮተ ዓለም የተጠመቁ መሆናቸው አስተዋጽኦ አለው እላለሁ፡፡ ተቃዋሚን እንደ ጠላት የሚፈርጀው ይህ ርዕዮተ ዓለም ተቃዋሚን በጥይት እንጂ በውይይት ለመርታት አይፈጥንም፡፡ አሁንም የምናየው የስም ማጥፋትና እስር የዚህ ውልድ ነው፡፡ ለመሆኑ ዛሬ በሠለጠነው አገር የሚኖሩ የተቃዋሚና የኢሕአዴግ ደጋፊዎች እንደ አገር ዜጋ ይተያያሉ? እንዲያው እውነቱን እንነጋገርና በአሜሪካ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች የተቃዋሚዎች ወከባ፣ ግልምጫና ስም ማጥፋት ሳይደርስባቸው በነፃነት ሐሳባቸውን ያራምዳሉ? ኢሕአዴግን የመደገፍ አዝማሚያ ያለው አርቲስት በአሜሪካና በአውሮፓ መልካም አቀባበል ይደረግለታል?

ከዚህ በተጨማሪ የሕዝቡ አለመደራጀት ዲሞክራሲያዊ ባህል እንዳይዳብርና ለዲሞክራሲያዊ መብት በፅኑ እንዳይታገል እንዳደረገው መካድ አይቻልም፡፡ ለተቃዋሚዎችም ትልቁ የቤት ሥራ ይህ ይመስለኛል፡፡ ዋጋ ከፍሎ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ ማደራጀት፡፡ ዋጋ ሳይከፍልና ሕዝብ ሳይደራጅ ሥልጣን መያዝ በአጋጣሚ ካልሆነ በስተቀር አይቻልም፡፡ በአጋጣሚም ቢያዝ የሚመሠረተው መንግሥት ፅኑ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ሊሆን ያዳግተዋል፡፡

እንዳንደራጅ ኢሕአዴግ አላሠራንም መቼም አይባልም፡፡ ለነገሩ ኢሕአዴግም ተቃዋሚውን እንደ ጠላት ስለሚያየው ይህን ለማድረግ ወደ ኋላ የሚል አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ለመብትና ለነፃነቴ መደራጀት አለብኝ ብሎ ዋጋ የማይከፍል ትውልድ ከሆነ ይህ ትውልድ፣ እንግዲያው ሌላው ዋጋ በከፈለበት ነፃነትን ሊጎናፀፍ የሚሻ ነውና ቆም ብሎ እንደ ሻማ ለመቅለጥ መወሰን፣ ወይም ደግሞ መተው ይሻል ይመስለኛል፡፡ እኔ ግን የመብት ረገጣ እስካለ ድረስ ለመረገጥ ፈቃደኛ ያልሆነ ሕዝብ ይኖራል ብዬ አምናለሁ፡፡ መቼም ሁሉም ለመብቱ እኩል ተቆርቋሪ ላይሆን ይችላል፡፡ ‹‹ጎመን በጤና›› የሚልም አይጠፋም፡፡ ቁምነገሩ ያለው ሕዝቡን በጠራ የፖለቲካ መስመርና ባህል በሩቅ አስቦ አሁን ሥራን በትጋት መወጣት ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አብዮት ሁሌም ችግሩ ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታ አለመዛመድ ነውና፡፡ ስለዚህ ሕዝቡን ማደራጀት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ የተደራጀ ሕዝብ ምን ዓይነት ዋጋ እንደሚከፍል የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ደርግን ለመፋለም ያንን ሁሉ ዋጋ የከፈለው ትውልድ የተለየ ትውልድ ሆኖ አይደለም፤ የተደራጀ እንጂ፡፡ የ1997 ዓ.ም. ምርጫን ተመልክቶ በአገራችን የተነሳው እንቅስቃሴ በቀላሉ የተዳፈነው በበቂ የተደራጀ ሕዝብና በሳል አመራር ባለመኖሩ እንደሆነ ይታመናል፡፡

በመጨረሻም አቶ መለስና ድርጅታቸው ለዚህ ሕዝብና አገር ታላቅ ውለታ የሠሩና እየሠሩ ያሉ ናቸው፡፡ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ወገኖች ይህንን መካድ አይገባቸውም፤ (ለነገሩ ሁሉም ተቃዋሚ አይክድም) አለመካድ ብቻ ሳይሆን በጥሩ ክንውኖች ላይ ማበረታታትና ከጎን መቆምን ሊያስተምሩን ይገባል፡፡ ዛሬ እኛ ያላደረግነውን ልጆቻችን ከየት አይተው ያደርጉታል? ከአሜሪካ ሕዝብ ሳይሆን ከእኛው ከአባቶቻቸው ይህን እየተማሩ ማደግ አለባቸው፡፡ በተረፈ ግን የጠራ የፖለቲካ መስመር ለመያዝ ተጨባጩን የኢትዮጵያና የዓለም አቀፍ ሁኔታ በአግባቡ ማወቅ እጅግ አስፈላጊ ስለሆነ፣ ተፎካካሪዎች ይህን አጥብቀው ቢመለከቱት እመክራለሁ፡፡ (አንተን ማን መካሪ አደረገህ ካልተባልኩ!)

እግረ መንገዴን አንድ የታዘብኩትን ነገር ልንገራችሁ፡፡ ብዙዎች የኢሕአዴግ የቀድሞ አባላት ስለ አቶ መለስ አመራር፣ ብሩህ አዕምሮና ስትራቴጂስትነት ሲናገሩ፣ እንዴት አድርገው ድርጅቱን ከጠባብ ብሔርተኛነት ትግል ወደ ብሔራዊ ትግል እንደቃኙት፣ ከማርክሳዊ ሌኒናዊ (አልባኒያኒዝም) ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኝነት ወደ ቀኝ ኃይል እንዴት ዘመም እንዳደረጉት፣ የደርግ ሠራዊትን ለመጣልና የሻዕቢያ ወረራን ለመቀልበስ ዋና ወታደራዊ ስትራቴጂስት እርሳቸው እንደነበሩ ሲናገሩ፣ ለዚህ ሁሉ ነገር በእርግጥ እርሳቸው ብቻ ነበሩ ባለ ራዕይ? ብዬ እንድጠይቅ ተገድጃለሁ፡፡ በእርግጥ ለሁሉም ጉዳይ ባለ ራዕይና ቀዳሚ ቀያሽ እርሳቸው ብቻ ከነበሩ፣ የሞቱት አቶ መለስ ዜናዊ ብቻ ሳይሆኑ ኢሕአዴግም ነው አስብሎኛል፡፡ ከዚህም ተነስቼ ኢሕአዴግ በቀደመው ጥንካሬ እንዲጓዝ ትልቅ የቤት ሥራ ከፊቱ እንዳለ መገንዘብ ያለበት ይመስለኛል፡፡ መቼም መሪን ከሁሉ ነገር በላይ ትልቅ የሚያደርገው ተተኪዎችን ማፍራት መቻሉ ነውና አቶ መለስ ተተኪዎችን አዘጋጀቱው ከሆነ በእርግጥም ታላቅ መሪ ነበሩ፡፡

አቶ ክፍሉ ታደሰ የተባሉ የኢሕአፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ‹‹ያ ትውልድ›› በተሰኘ መጽሐፋቸው ‹‹የፓርቲው ዋና ፀሐፊ የአቶ ተስፋዬ ደበሳይን ሞት ስንሰማ የማዕከላም ኮሚቴ አባላት ሁላችንም ኢሕአፓ በቀድሞ ወቡቱና ጥንካሬው መቀጠል እንደማይችል በልባችን ተገንዝበን ነበር፤›› አሉ፡፡ ለኢሕአዴግም ሆነ ለተፎካካሪዎች ይህን አልመኝም፡፡ ኢትዮጵያ ጠንካራ መሪዎች ያሉባት ተፎካካሪ ድርጅቶች በእጅጉ ያስፈልጓታልና፡፡ ለመሆኑ መቼ ይሆን የፖለቲካ ባህላችን የሚለወጠው? እኛ ካልጀመርነው ማን ይሆን የሚጀምርልን?
ቸር ይግጠመን፡፡            

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር