የእስልምና ምክር ቤት ምርጫ ዛሬ ይካሄዳል



-    ሁለቱም ምክር ቤቶች ክስ ቀርቦባቸዋል
በታምሩ ጽጌ
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አገር አቀፍ ምርጫ ዛሬ ይካሄዳል፡፡ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሙስሊሙን የሚመሩ የሃይማኖት መሪዎች ለመምረጥ በአዲስ አበባ በሁሉም ወረዳዎች ምርጫው እንደሚደረግ የኡላማዎች ምክር ቤት አስታውቋል፡፡

የሃይማኖት መሪዎቹ የምርጫ ጊዜ ማለፉን በመጥቀስና ሕዝቡ ያልመረጣቸው መሪዎች ሊወክሏቸው እንደማይችሉ ሲገልጹ የነበሩ ከ50 በላይ ተጠርጣሪዎች በእስር ላይ ናቸው፡፡

በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጥያቄና ፊርማ መቋቋሙን የገለጸ 17 አባላት ያሉት ኮሚቴ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትና የኢትዮጵያ ኡላማዎች ምክር ቤት እንዲበተኑና ለምክር ቤቱ የሚደረገው ምርጫ በገለልተኛ አካል እንዲደረግ፣ ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ፍትሐ ብሔር ችሎት ክስ አቅርቧዋል፡፡

በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 408 መሠረት ምክር ቤቱ የራሱ የሆነ የመመሥረቻና የመተዳደሪያ ደንብ ያለው መሆኑንና ከተጣሉበት ኃላፊነቶች መካከልም፣ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከሌላ እምነት ተከታዮችና ከመንግሥት ጋር እምነታቸውን በተመለከቱ ጉዳዮች ግንኙነቶችን ማስተባበር መሆኑን ክሱ ይገልጻል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሥራ አመራሮች የሚሾሙት በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት በግልጽ በየአሥር ዓመቱ በሚደረግ ሕዝባዊ ምርጫ መሆኑን የሚገልጸው ክሱ፣ ተመራጩም ያለምንም አድልኦ የመረጠውን የኅብረተሰብ ክፍል ለማገልገል ግዴታ መግባቱን ያብራራል፡፡

ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ በሥራ ላይ የሚገኘው ምክር ቤት በምርጫ ያልተሾመ ከመሆኑም በላይ፣ ሕግና ደንቡን በመተላለፍ ላለፉት 13 ዓመታት ምንም ዓይነት ምርጫ አለማድረጉን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ምክር ቤቱ እየፈጸማቸው የሚገኙት ተግባሮች በሙሉ ሕጋዊነት የሌላቸው መሆኑን ጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ኡላማዎች ምክር ቤትም የሕግና የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ድጋፍ በሌለው በኢትዮጵያ እስልምናዎች ምክር ቤት የተቋቋመ አካል መሆኑንና ምርጫ የማስተባበር ሥልጣን እንደሌለው የሚያብራራው ለፍርድ ቤቱ የቀረበው ክስ፣ የኡላማዎች ምክር ቤት ግን ዛሬ ለሚደረገው ምርጫ (መስከረም 27 ቀን 2005 ዓ.ም.) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አባላትን ምርጫ ለማድረግ ዝግጅት ማጠናቀቁን አሳውቋል፡፡ ድርጊቱ ግን ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 28 ይኼንን መሰል ምርጫ መደረግ ያለበት በዲሞክራሲያዊ አግባብ መሆኑን መደንገጉን፣ አሁን ምክር ቤቱ የተቋቋመበትን መመርያና ደንብ ብቻ ሳይሆን ሕገ መንግሥቱንም የጣሰ መሆኑን ክሱ ያብራራል፡፡

በመሆኑም በምክር ቤቱ መተዳደርያ ደንብና በፍትሐ ብሔር ሕጉ መሠረት ድርጊቱ እንዲታገድና የምክር ቤቱ አባላት እንዲበተኑ እንዲወሰንለት፣ የኡላማዎች ምክር ቤትም ሥልጣን የሌለው መሆኑ እንዲወሰንና ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን የሚወክል ገለልተኛ ኮሚቴ እንዲቋቋም በማድረግ የሥራ አመራር አካላት ምርጫ እንዲከናወን እንዲወሰንለት ከሳሽ ጠይቋል፡፡ 
http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/8009-2012-10-06-12-21-48.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር