ሚኒስቴሩ የሰንደቅ አላማ ቀን ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ቦንድ ለመግዛት ቃል በመግባት አከበሩ


አዲስ አበባ ጥቅምት 19/2005 5ኛውን ብሄራዊ የሰንደቅ አላማ ቀን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ ግንባታ ቦንድ ለመግዛት ቃል በመግባት መከበሩን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ። የሚኒስቴሩ ሰራተኞች "ሰንደቅ አላማችንን ከፍ አድርገን በታላቁ መሪያችን የተጀመረውን ህዳሴ እናረጋግጣለን” በሚል መሪ ቃል በዓሉን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች አክብረዋል። መላው የሚኒስቴሩ ሰራተኞች በቅርቡ በሞት የተለዩትን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ራዕይና ተልዕኮ ለማሳካት በተሰማሩበት የስራ መስክ በቁርጠኝነት የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል። ሰራተኞቹ የተጀመሩ የልማት የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን አጠናክሮ ለመቀጠል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል። በበዓሉ ላይ የተገኙት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አቶ ደሴ ዳልኬ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በአሁኑ ወቅት ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ለሚኒስቴሩ ሰራተኞች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የሚኒስቴር ሰራተኞች ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የጀመሩትን አስተዋጽኦ በመቀጠል በአንድ ዓመት ተከፍሎ የሚያልቅ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ቦንድ ለመግዛት በድጋሚ ቃል ገብተዋል። ሠራተኞቹ ባለፈው አመት ቃል ለገቡት የቦንድ ግዥ ማረጋገጫ ሰርተፊኬትም ከሚኒስቴሩ ተቀብለዋል፡፡ በበዓሉ ላይ በሰንደቅ ዓላማ ህጋዊ ማእቀፎች ዙሪያ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዳል። በሰራተኞች መካከልም የጥያቄና መልስ ውድድርና የግጥም ዝግጅት መካሄዱን ኢዜአ ዘግቧል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር