ኢሕአዴግ ቆራጥና ደፋር የውስጥ ትግል ያስፈልገዋል



ኢሕአዴግ በሕዝብ ተከብሮና ተደግፎ ጠንካራ መሠረት ይዞ ለመቀጠል ከፈለገ ይችላል፡፡ የሚችለው ግን ራሱን ሲያጠናክር ነው፡፡

ራሱን ማጠናከር የሚችለው ደግሞ ውስጡን ሲያፀዳ ነው፡፡ ውስጡን ማፅዳት የሚችለው ደግሞ ቆራጥና ደፋር የውስጥ ትግል ሲያካሂድ ነው፡፡

ደፋርና ቆራጥ የውስጥ ትግል ካካሄደ ፀድቶና ተጠናክሮ ይወጣል፣ ይቀጥላል፣ ይጓዛል፡፡ የለም አላደርግም፣ አልታገልም፣ አልቆርጥም፣ አልደፍርም ካለ ደግሞ ውስጥ ለውስጥ እየተሰነጣጠቀ፣ እየበሰበሰና እየተደረመሰ ይሄዳል፡፡ ይደክማል ከሕዝብ ይርቃል፡፡ የነበረው እንዳልነበረ ይሆናል፡፡

ኢሕአዴግ ቆራጥና ደፋር የውስጥ ትግል የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?
1.    ከላይ እስከታች በሙስና የተጨማለቁ በዝተዋል!
አዎን ንፁኃን የሕዝብ አገልጋይ፣ ለልማትና ለለውጥ የቆሙና የሚታገሉ አባላትም አመራርም በኢሕአዴግ ውስጥ አሉ፡፡ በዚያው አንፃር ደግሞ ከሕዝባዊ መስመር እየራቁና እየሸሹ ለግል ገንዘብ፣ ንብረት፣ ክብርና ኔትዎርክ የሚሯሯጡ፣ በጉቦ የተጨማለቁና በሙስና የተነከሩ አሉ፡፡ እነዚህ በውስጥ ትግል፣ በደፋርና በቆራጥ ትግል ካልተገለሉና ድርጅቱ ካልፀዳ ድርጅቱን እያበሰበሱ የሚገድሉት ናቸው፡፡

2.    አቅም አልባ… ምላስ  ብዙ በዙ!
በብቃት መመደብ እየቀረ ደጋፊ እስከሆነ ችግር የለም እየተባለ የተሾመው ሁሉ የድርጅቱን ዓላማ ማራመድ አልቻለም፡፡ ሕዝቡንም ማገልገል አልቻለም፡፡ ባለአቅም እየጠፋ ባለምላስ በዛ፡፡ ተንዛዛ በጣም በዙ፡፡ ሕዝብ ይህንን እያየና እያስተዋለ ምንድን ነው ነገሩ? እያለ ነው፡፡ አይወስኑም፣ ቢሮ አይገቡም፣ አያሳምኑም፡፡ አንዳንዶቹም ይህን እያወቁ ሀቅን ከመጋፈጥ ይልቅ ሽሽትና ድብብቆሽ እየመረጡ ናቸው፡፡ ሕዝብ በድርጅቱ ላይ አመኔታ እንዲያጣ እያደረጉ ናቸው፡፡

3.    ጠንካራ አንድነት በአባል ድርጅቶችና በአጠቃላይ በኢሕአዴግ ውስጥ በጠነከረ ሁኔታ አይታይም፡፡ 

ከተቃዋሚዎች ይልቅ የበለጠ አንድነት በኢሕአዴግ ውስጥ ይታያል፤ አለ፡፡ ይህ አንድነት ባይኖር ኖሮ በቅርቡ የታየው ተረጋግቶ የመሸጋገር ሁኔታ አይታይም ነበር፡፡

ሆኖም ግን ራሳችንን አናታልል፤ ያለው የዓለም ሁኔታ ከሚጠይቀው አንድነትና መጠናከር ከሚጠይቀው መመዘኛ አንፃር ሲታይ ያለው አንድነት ጠንካራ አይደለም፡፡ ተደፋፍሮ መገማገም፣ ቆራጥና ደፋር ትግል አካሂዶ አንድነትን እውን የማድረግ ሁኔታ በአጠቃላይ በኢሕአዴግ፣ በተናጠልም በእያንዳንዱ ድርጅት እየታየ አይደለም፡፡

ጠንካራ አንድነት በሕወሓት ውስጥ አይታይም፣ ጠንካራ አንድነት በብአዴን ውስጥ አይታይም፣ ጠንካራ አንድነት በኦሕዴድ ውስጥ አይታይም፡፡ ጠንካራ አንድነት በደኢሕዴን ውስጥም አይታይም፡፡ እርስ በርስም ጠንካራ አንድነት እየታየ አይደለም፡፡ ጠንካራ አንድነት ግን የግድና የግድ ይላል፡፡

4.    ዕቅዶች በተፈለገው ብቃትና ፍጥነት ተግባር ላይ እየዋሉ አይደለም፡፡ 
የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተዘጋጅቶ ፀድቆ ሥራ ላይ እየዋለ ነው፡፡ ነገር ግን ፍጥነቱና ይዘቱ በተፈለገው ደረጃ አይደለም፡፡ በአንዳንድ ሥፍራ ልማት እየቆመ ነው፡፡ የፍትሕ ሥርዓት እየተደረመሰ ነው፡፡ መንግሥት በቂ ገንዘብ ማሰባሰብ እያቃተው ነው፡፡ በብዙ ቦታዎች ንብረትና ገንዘብ እየባከነ ነው፡፡ የመንግሥትም የሕዝብም ጉጉትና ምኞት በተፈለገው ፍጥነት እውን እየሆነ አይደለም፡፡ የፌደራልና የክልል መንግሥታት ቆራጥና ጠንካራ ርብርብ እያሳዩ አይደለም፡፡ ይህን ለማየትም ጠንካራ፣ ቆራጥና ደፋር የውስጥ ትግል ያስፈልጋል፡፡

5.    የኢሕአዴግ የሕዝብ ግንኙነት እየላላ ነው፡፡
ሕዝብ መንግሥትን ለመደገፍ ጨዋነቱንና ኢትዮጵያዊነቱን ለማሳየትና ለማረጋገጥ በእጅጉ ዝግጁ ነው፡፡ በሐዘን ጊዜም በጋራ እንደ አንድ ሰው አልቅሷል፤ አዝኗል፡፡ ጨዋነቱንና ኢትዮጵያዊነቱን በግልጽ ለዓለም አሳይቷል፡፡ በእግር ኳስ ደስታም ማንነቱን በየጎዳናው አሳይቷል፡፡ ያኮራል፣ እውነትም ወርቅ ሕዝብ፡፡

ግን… ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያዊያን ተንቀሳቀሱና ማንነታቸውን አሳዩ ማለት ከመሪው ፓርቲ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በአዎንታ አንፀባረቁ ማለት አይደለም፡፡

ፍትሕ ሲጠፋ አቤት የምንልበት ጠፋ፡፡ ወደ ሕዝብ ቀርቦ፣ ወደ ሕዝብ ወርዶ የሚያነጋግረን ሹም ጠፋ እያሉ ነው፡፡ ይህ ማለት ሕዝቡ የሚፈልገውን ግንኙነትና ትስስር እያገኘ አይደለም፡፡

በኦሮሚያ ሕዝቡ የበለጠ መቀራረብ ከኦሕዴድ እየጠበቀ ነው፡፡ በአማራም የበለጠ መቀራረብን ከብአዴን እየጠበቀ ነው፡፡ በደቡብም እንደዚሁ የቅርብ ትስስሩን እየጠበቀ እያጣው ነው፡፡ በትግራይም እንደዚሁ የለመደው ጠንካራ ትስስር ሲላላ እያስተዋለ ነው፡፡ እነዚህ እንደማሳያ ይበቁናል እንጂ ብዙ መዘርዘር ይቻላል፡፡ 

ይህ ችግር የሥልጣን ሽግግር ከመጣ በኋላ የተከሰተ አይደለም፤ የነበረ ችግር ነው፡፡ የቆየ ችግር ነው፡፡ እያልን ያለነው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርና አዲሱ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጠንካራ ኢሕአዴግና ጠንካራ መንግሥት ይዘው የላቀ ድል እንዲያስመዘግቡና ኢትዮጵያን በላቀ የዕድገት ደረጃ እንዲመሩ፣ የገዢው ፓርቲ የኢሕአዴግ መጠናከር የግድ ይላልና ኢሕአዴግን ያፅዱ ያጠናክሩ፡፡

ከጥቂት ወራት በኋላ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች፣ ኢሕአዴግም እንደ ኢሕአዴግ ጉባዔዎች ያካሂዳሉ፡፡ ከጉባዔው በፊት ኢሕአዴግ ከአሁኑ ጀምሮ ለደፋርና ለጠንካራ የውስጥ ትግል ይዘጋጅ፣ ያቅድ ተግባሩን ይጀምር፡፡

ገዢው ፓርቲም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲጠናከሩ እንጂ ሲዳከሙ የሚጠቀም ሕዝብና አገር የለም፡፡ በተለይም እስከ ቀጣዩ ምርጫ ሥልጣን የያዘው ኢሕአዴግ ካልተጠናከረ ሊደርስ የሚችለው አደጋ ቀላል አይደለም፡፡ ያለው ሁኔታ ከባድ ነው፡፡ በውስጥም በውጭም፡፡

ስለዚህ ጠንካራ ኢትዮጵያን እያጣን እንዳንቀጥልና ከፍተኛ ዕድገት እያየን አስተማማኝ የዴሞክራሲ ጉዞ እውን እንድናደርግ፣ አንዱ ተፈላጊ ጉዳይ ጠንካራ የሕዝብ አገልጋይ መንግሥት በአስተማማኝ ደረጃ እውን ማድረግ ነው፡፡

ስለሆነም ጠንካራና አስተማማኝ ጉዞ እውን እንዲሆን ኢሕአዴግ ደፋርና ቆራጥ የውስጥ ትግል የግድ ይለዋል! በአስቸኳይ!   
http://www.ethiopianreporter.com/editorial/294-editorial/8221-2012-10-24-06-31-40.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር