መምህራንን ለመመዘን ዝግጅቱ ተጠናቅቋል




ሃዋሳ፡- የመምህራንን የሙያ ምዘና ለማካሄድ ዝግጅት መጠናቀቁን ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ። የመጀመሪያው የመምህራን ምዘና በሕዳር 2005 መጨረሻ እንደሚካሄድ አስታወቀ።
የደቡብ ክልል 18ኛ አጠቃላይ የትምህርት ጉባዔ ሰሞኑን በሃዋሳ ከተማ ሲዳማ ባህል አዳራሽ በተካሄደበት ወቅት በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራን ሙያ ፈቃድ አሠጣጥና እድሳት ዳይሬክተር አቶ ሳህሉ ባይሳ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት የመምህራንን የሙያ ምዘና በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማካሄድ በመንግሥት በኩል ዋና ዋና ዝግጅቶች ተጠናቅ ቀዋል።
ለምዘና ሥራው የሚረዱ ስታንዳርዶችን የማውጣትና እነዚህን ለማስፈፀም የሚረዱ መመሪያዎችን የማዘጋጀቱ ሥራ መጠናቀቁን የገለጹት አቶ ሳህሉ፤ ለምዘና ሥራው አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁስ መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል። የፈተናው ዝግጅት ሥራም በትምህርት ሚኒስቴር በኩል እየተከናወነ መሆኑንና በተያዘው ዓመት መጀመሪያ ተጨባጭ ተግባራት ለመጀመር መታቀዱን አብራርተዋል።
በአገራችን የመምህራን ሙያ ፈቃድ አሰጣጥና ዕድሳት ሥርዓት ሲጀመር ይህ የመጀመሪያው እንደሚሆን አቶ ሳህሉ ገልጸው፤ የመምህራን ምዘና ለትምህርት ጥራት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል። መምህራን በተቀመጠላቸው ስታንዳርድ መሠረት ሙያቸውን እየፈፀሙ መሆኑን ለማወቅ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
የምዘና ሥራው በዋናነት በክልሎች እንደሚመራ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ትምህርት ሚኒስቴር ስታንዳርዶችንና መመሪያዎችን የማውጣትና የምዘና ሥራውን በበላይነት የመቆጣጠር ሥራ እንደሚያከናውን አስረድተዋል። በቅርቡ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጠው ፈተና በትምህርት ሚኒስቴር እንደሚዘጋጅና በቀጣይ ፈተናው በክልሎች የሚዘጋጅ መሆኑንም አስረድተዋል። ፈተናውን የመምራትና የማስተዳደር ኃላፊነትም የክልሎች እንደሚሆን አስታውቀዋል።
የመጀመሪያው ምዘና በሕዳር 2005 ዓ.ም መጨረሻ እንደሚሰጥ አቶ ሳህሉ ገልጸው፤ የምዘና ሥራው ከአፀደ ሕፃናት እስከ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋማት ያሉ የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች መምህራንን እንደሚያካትት ተናግረዋል።
በወጣው መርሐ ግብር መሠረትም በመሰናዶ ትምህርት ቤቶችና በመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች የሚያስተምሩ መምህራንም በቀጣይ እንደሚመዘኑ አስታውቀዋል። በተከታታይ ዓመታትም መዛኞችን በብዛት በማፍራት ሁሉም መምህራን ተመዝነው የሙያ ፈቃድ ባለቤት እንዲሆኑ የሚደረግ መሆኑንም አስረድተዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፉአድ ኢብራሒም በበኩላቸው፤ የምዘና ሥራው የመጀመሪያ ተግባር መዛኞችን ማፍራት እንደሆነ ተናግረዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ1ሺ 200 በላይ መዛኞችን ለማፍራት መታቀዱንም እንዲሁ።
መዛኝ ለመሆን በቅድሚያ የሚመዘኑት በፈቃደኝነት የመጡ መምህራን እንደሆኑ የገለጹት አቶ ፉአድ፤ በቀጣይ ሁሉም መምህር ራሱን እያበቃ የሚሄድበት አቅጣጫ መቀመጡን ጠቁመዋል። በመጀመሪያ ምዘና ላይ የታዩ ችግሮች ተስተካክለውና ሞጁል ተዘጋጅቶ መምህራን ራሳቸውን እንዲያበቁ የሚደረግ መሆኑንም አመልክተዋል።
ፈተናውን የሚወድቁ መምህራን በተደጋጋሚ የመፈተን እድል እንዳላቸው አመልክተው፤ በቀጣይ ወደ መምህርነት ሙያ የሚገቡ አዲስ መምህራን እየተመዘኑ እንደሚገቡ ተናግረዋል። ሁሉም ነባር መምህራንም በሂ ደት ይመዘናሉ ሲሉ አስረድተዋል።
ሀገራችን ለጀመረችው ፈጣን የኢኮኖሚ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ወሳኝ መሆኑን አቶ ፉአድ ገልጸው፤ ብቃት ያለውን የሰው ኃይል ለማግኘት የትም ቦታ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ መምህራንን በቅድሚያ ማፍራት ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል። 
http://www.ethpress.gov.et/ethpress/main/news.php?newsLocation=home&newsInstruction=headline&newsId=9800

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር