በሃዋሳ ከተማ የማታለል ወንጀል የፈጸሙ ወጣቶች ጥፋተኛ ተባሉ



አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) በሃዋሳ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ ተገኝቶ ለድሆች እንዲሸጥ የተደረጉ የተለያዩ እቃዎችን እንዲገዙ በማግባባት የማታለል ወንጀል የፈጸሙ ሁለት ወጣቶች ጥፋተኛ ተባሉ።

ጥፋተኛው አብዲ መሀመድ አሊ የተባለው የ20 አመት ወጣት በሃዋሳ ከተማ ጉዱማሌ በተሰኘው ቀበሌ ፥ መንገድ ላይ ያገኛቸውን አንድ ወንድ እና አንድ ሴት ፤ በኮንትሮባንድ ተይዞ በመንግስት ውሳኔ ድሆችን ከግምት ውስጥ ባስገባ ዋጋ ይሸጥ የተባለ እቃ ስላለ ከእሱ ጋር በመሆን አብረው እንዲገዙ በማግባባት ወንጀሉን ፈጽሟል።

ተከሳሹ ወንጀሉን ወደፈጸመበት ስፍራ ተበዳዮቹን ይዟቸው ካመራ በኋላ ፥ እቃዎቹን ለመግዛት ወደ ውስጥ ሲገባ ፤ እቃ በእጅ መያዝ እንደማይቻል  ነግሮ፤ ግብረ አበሩ የሆነው ሌላኛው ተከሳሽ እርሱ ሞባይል እና ወርቁን አስቀምጦ ለግብይት መግባት እንደሚፈልግ በመናገር በተበዳዮቹ ላይ እምነት እንዲያድርባቸው ካደረገ በኋላ እነርሱ ቀድመው  ለግብይት ወደ ግቢው ሲያመሩ እቃቸውን ይዞ ከአካባቢው ተሰውሯል።

ግብረ አበሩ የተበዳዮቹን አንድ ኖኪያና አንድ ሳምሰንግ ሞባይል፣ አንድ ላፕ ቶፕ፣ 7 ግራም የውጭ ወርቅ እና 250 ብር በመያዝ ነው ከአካባቢው የተሰወረው።

ይህን የተመለከተው አብዲ ጓደኛውን ተከትሎ ሲሮጥ ተይዞ ስለተመሰከረበት ፥ የቀረረበትን ክስ ሊያስተባብል ባለመቻሉ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብሏል።

ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የሃዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ፥ የአቃቤ ህግን የቅጣት አስተያየት ተቀብሎ ቅጣት ለመጣል ለመስከረም 29 ተለዋጭ ቀጠሮ መያዙን ጥላሁን ካሳ ዘግቧል።
http://www.fanabc.com/Story.aspx?ID=26242&K=

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር