የትምህርት ባለድርሻ አካላት ለተማሪ ውጤት ትኩረት እንዲሰጡ ይደረጋል



ዋሳ፦ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ለተማሪ ውጤትና ሥነ ምግባር መሻሻል ትኩረት እንዲሠጡ ማድረግ የዘንድሮ የትምህርት ዘመን ቁልፍ ተግባሩ መሆኑን የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ገለጸ። በክልሉ በ2004 ዓ.ም በትምህርት ሥራ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ መምህራን፣ ርዕሳነ መምህራን፣ ተማሪዎችና ሱፐርቫይዘሮች ተሸለሙ።
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት 18ኛ አጠቃላይ የትምህርት ጉባኤ ሰሞኑን በሃዋሳ ከተማ በተካሄደበት ወቅቱ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ አህመዲን እንደገለጹት፤ የተጀመረውን የትምህርት ልማት ሠራዊት ግንባታ ሥራ በማጠናከር ባለድርሻ አካላት ለተማሪ ውጤትና ሥነምግባር መሻሻል ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ማድረግ የበጀት ዓመቱ ቁልፍ ተግባር ነው።
ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት በክልሉ በትምህርት ሠራዊት ግንባታ ሥራ መሠረት መጣሉን አስታውሰው፣ በ2005 ዓ.ም ሠራዊቱ ትክክለኛ ቁመና ተላብሶና የተቆጠረ ተግባር ወስዶ በተማሪዎች ውጤት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
ዘንድሮ በትምህርት ልማት ሠራዊት ውስጥ ያሉ ባለድርሻ አካላትን ውጤት ሊያመጣ በሚችል መልኩ ለማንቀሳቀስ መታሰቡን ያመለከቱት አቶ አህመድ፤ በሚሌኒየሙና በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ የተቀመጡትን ግቦች ከማሳካት አኳያ በተያዘው ዓመት ለትምህርት ተደራሽነት ሥራም ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ አመልክተዋል። በጎልማሶች ትምህርት ላይም የተሻለ ሥራ ለመሥራት መታቀዱን አብራርተዋል።
የትምህርትን ጥራት የሚያረጋግጥ ሥራ በዋናነት የሚመራው በመምህሩ እንደሆነ ጠቁመው፤ ክልሉ የመምህራንን አቅም ለማጎልበት የቅድመ ሥራ ላይ ሥልጠና፣ የሥራ ላይ ሥልጠናና አጫጭር ሥልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል በቅርቡ ከ35ሺ በላይ በምሥክር ወረቀት ደረጃ የሠለጠኑ መምህራንን ወደ ዲፕሎማ እንዲያድጉ በኮሌጅ ገብተው እንዲማሩ እየተደረገ መሆኑን አስረድተ ዋል። ለሥልጠናውም ከ86 ሚሊዮን ብር ያላነሰ መመደቡን ነው የገለጹት።
በጉባኤው ማጠቃለያ የክልሉ ትምህርት ቢሮ በሥሩ ካሉ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ጋር የግብ ስምምነት ማድረጉን አቶ አህመድ ገልጸው፤ ስምምነቱ ከትምህርት ቢሮ እስከ መምህርና ተማሪ ድረስ እንደሚወርድ አስረድተዋል። ስምምነቱ በጋራ ለመንቀሳቀስና ውጤታማ ስትራቴጂን ለመንደፍ ከመርዳቱ በተጨማሪ የተቆጠረ ተግባር ለመስጠትና፣ ድጋፍ ለማድረግ ዓይነተኛ መሳሪያ መሆኑንም አብራርተዋል።
በተያያዘ ዜና በ2004 ዓ.ም በክልሉ በትምህርት ሥራና የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ መምህራን፣ ርዕሳነ መምህራን፣ ተማሪዎች የገንዘብ ሽልማት ተበርክቷል።
በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ዣ ወረዳ የአገና 01 አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሰ መምህር ታደሰ ብርሃነ እና የአርቤጎና ሁለተኛ ደረጃ መሰናዶ ት/ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ሰለሞን ስዩም በበኩላቸው፣ በትምህርት ቤታቸው የትምህርት ጥረት ማረጋገጫ ፓኬጅ መርሃ ግብሮችን በአግባቡ በመተግበራቸው ችግር ፈቺ እቅዶችን አቅደው ወደተግባር በመግባታቸውና የተማሪዎችን ውጤት በማሳደጋቸው ሽልማቱን ማግኘታቸውን ተናግረዋል። የዋንጫ፣ የሠርተፊኬት፣ የፎቶ ኮፒ ማሽንና የገንዘብ ስጦታ ተሸልማዋል ብለዋል።
ከደቡብ ክልል ባስኬቶ ልዩ ወረዳ በ10ኛ ክፍል ፈተና አራት ነጥብ በማምጣቷ የሠርተፊኬትና የገንዘብ ሽልማት የተበረከተላት ተማሪ ቤተልሄም ታሪኩ በበኩሏ፤ ሽልማቱ የተለየ ደስታና ለቀጣይ ትምህርቷ መነሳሳት እንደፈጠረባት አስረድታለች።
ከጥቅምት 5 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ቀናት በተካሄደው በዚህ ጉባዔ የክልሉ ትምህርት ዘርፍ የ2004 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸምና የ2005 ዓ.ም እቅድ አቅጣጫ ቀርቦ ውይይት ተደርጎባቸዋል። ምርጥ ተሞክሮዎች ቀርበው ልምድ የተቀሰመባቸው ሲሆን፤ ጉባኤው ባለ 12 ነጥብ የአቋም መግለጫና ውሳኔ በማውጣት ተጠናቋል። 
http://www.ethpress.gov.et/ethpress/main/news.php?newsLocation=home&newsInstruction=headline&newsId=9730

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር