የሲዳማ ክልል እውን ትሆናለች

ናት ሐመሶ

በሲዳማ ህዝብ ላይ ሲዶልቱ፣ ሲያሴሩ፣ ሲሰልሉና በህዝባችን ላይ በደል ሲፈጽሙ የነበሩ ትላንትና በሂስ ግለሂስ ወቅት ተጋለጡ
በሲዳማ ምክክር ፎረም (sidama dialogue forum) – ከዚህ ቀደም “የሲዳማ ታጋዮች ፎረም” ይባል የነበረው ነው፡፡
ሰሞኑን የደኢህዴን/ኢህአዴግ አመራሮችና ካድሬዎች (የሲዳማ ዘርፍ) ከያሉበት ተሰባስበው በሲዳማ ባህል አደራሽ ከተው ሲመክሩና ህዝባችንን ሲክዱ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ ስብሰባው የተጀመረው ባሳለፍነው ሳምንት ሰኞ መስከረም 13/2005 ዓ/ም ሲሆን እስከ ትላንትናው ቀን ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ ዘልቋል፡፡ ሽፈራውም በመኖሪያ ቤቱ በርካታ መንፈሳዊ አገልጋዮችንና መንፈሳዊ ሰዎችን ጠርቶና አስጠርቶ የምስጋና ጊዜ አዘጋጅቶ ቀኑን ሲያስብ የዋለው ቅዳሜ ቀን መስከረም 18/2005 ዓ/ም ነው፡፡ ይህ ቀን የተመረጠበት ምክንያት ግልጽ ነው - ከያሉበት አከባቢ ሁሉ የተሰባሰቡ ካድሬዎችን (እጅ ብቻ የሚያነሱ የማይናገሩና የራሳቸው የሆነ አቋምና ዓላማ የሌላቸው ሰው መሰል ፓርላማ ተብየ ፍጡራንን ጨምሮ) “ለሲዳማ ክልል አያስፈልገውም” በሚል ሀሳብ ዙሪያ እጅ አስነስቶ አስወስኖ የነበረ መሆኑ ነው፡፡ ይህ የክህደት ውሳኔ የተላለፈው “ከምስጋና ቀን” አንድ ቀን አስቀድሞ አርብ ለት  በ17/01/2005 ሲሆን ለምስጋና ፕሮግራም ቅዳሜ የተመረጠውም ለዚህ ነው፡፡ በርግጥ ይገባዋል፤ የሲዳማ ህዝብ ሁሉ “ደኢህዴንም ሆነ አንተ አትወክለንም፤ አንተ ከስልጣን ውረድ…” ብሎ በአንድ ሀሳብ ካወገዘውና የጫምባላላ ታዳሚ ሁሉ በረገመውና በሰደበው ማግስት ካድሬውን መልሶ ማሳመን ከቻለ ለርሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በርግጥ ስብዕና ቢኖረው ኖሮ ከዛ ሁሉ ውርደት በኋላ ሀገር ጥሎ በጠፋ ነበር፡፡ ቢሰደብ የሚዋረድ ስብዕና ስለለሌው ግን እንኳ አገር ጥሎ ሊሄድ ስልጣንም ሊለቅ አልፈቀደም፡፡ ሌላው የሚመለከተው የመንግሥት አካልማ የሚፈልገው ህዝብ የጠላውን መሾም ነው፡፡ አንድ የክልልም ሆነ የዞን መሪ ሥራ ሠርቶና ፍትህ ሰጥቶ በህዝብ የተወደደ አንደሆነ ወድያው ካለበት ይነሳል፡፡ ልክ እንደአባዱላ ገመዳ ማለት ነው፡፡ አባዱላ ኦሮሚያ ክልል ከቆየ ነገ ለኢህአዴግ ላይመች ይችላል፤ በህዝብ ተቀባይነት አለውና ህዝብን በመንግሥት ላይ ያስነሳል ተብሎ ይፈራል፡፡ ስለዚህ ወዲያው ተነስተው ከህዝብ የማይገናኙበት መቀመጥ ነበረባቸው፡፡ የእኛው ግን የህዝብ ልጆችን ብቻ እያሳደደ፣ ምንም ሳይሠራ ቁጭ ብሎ ው እየዘረፈ ያለው፡፡ ህዝብን የበደለና ህዝብ የጠላው “መሪ” በህዝብ ጫንቃ ላይ ይጫናል፡፡ ይህ ነው እንግዲህ የእኛ ሀገር ዴሞክራሲ፡፡
ወደዋናው መልዕክታችን እንመለስና ከጅምሩ አንስቶ እንዴት እንደዘለቁ ሌላ ጊዜ በሌላ ቀጠሮ እንመለሳለን፤ አሁን የትላንትና ውሏቸው በጥቂቱ ምን ይመስል እንደነበር ለማየት ወደድን፡፡ ሰሞኑን ስብሰባውን በጀመሩ አምስተኛ ቀን አከባቢ ከላይ እንደገለጽነው ሽፈራው “ለሲዳማ ክልል አያስፈልገውም፣ አይሰጠውምም፤ የሐዋሳን ከተማ ለጊዜው አሁን ባለበት ሁኔታ ቢቀጥልም ለወደፊቱ የስብጥር አስተዳደር ማስተዳደር አለበት… ይሄንን የሚደግፍ በእጅ ያሳውቅ” የሚል የውሳኔ ሃሳብ አንስቶ ካድሬዎቹ ደግፈው እጅ ካወጡ በኋላ በማግስቱ ጀምሮ የሂስ ግለሂስ መድረክ ተበጅቶ ሂስ-ግለ-ሂስ ሲያነሱ እስከትላንትና የዘለቁ ሲሆን ዛሬም በዚሁ መልኩ እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል፡፡ ታዲያ ይህችን መጣጥፍ እንድናደርስላችሁ ያነሳሳን ጉዳይም የተፈጠረው በዚሁ በትላንትናው ሂስ-ግለሂስ መድረክ ነው፡፡ መቼም የህዝብ አምላክ በአንድም ሆነ በሌላ እንደሚሠራና የኋላ ኋላ ህዝባችን የድሉ ባለቤት እንደሚሆን እናውቃለን፡፡ እነርሱ ያላወቁት ነገር ቢኖር የሲዳማን የክልል ጥያቄ ካድሬ ሊያፈርሰው ወይም ሊቀለብሰው እንደማይችል ነው፡፡ ታዲያ በህዝባችን ጫንቃ ላይ ተጣብቆ ከሚጠቡት ውስጥ ዋናው መዥገር ሳሙኤል ሼባ ሂስ ሲውጥ አንዱ ካድሬ ይነሳና “ለዚህ ሁሉ ችግር ተጠያቂ አንተ ነህ፤ የሐዋሳ ነዋሪ ሆኖ የሲዳማ ተወላጅ የሆነ ሰው ሁሉ ፋይል አንድ በአንድ ወጥቶ ተመርምሮና መረጃው ተሰብስቦ የተያዘና ወደክልል የተላለፈ መሆኑ የታወቀና ሁላችንም ምን ሊያመጡ ይችላሉ እያልን ህዝባችን ላይ ሊመጣ የሚችልን ችግር እያሰብን በስጋት ያለን ቢሆንም ብዙ አልተደነቅንም ነገር ግን እኛን ያሳዘነንና ግራ ያጋባን ፋይል ከማስመርመር አልፋችሁ እራሳችሁ የእያንዳንዱን የሲዳማ ተወላጅ ቤት በማፈላለግና በመሰለል፣ በማጥናትና ፎቶግራፍ በማስነሳት መረጃ ሰብስባችሁ አላስተላለፋችሁም? በሁሉም ወረዳዎች የሚገኙ በሲዳማ ተወላጆች የተያዙ መፈልፈያዎችን ሰልላችሁ መረጃ እየሰበሰባችሁ ፍቶግራፍ አላነሳችሁም? ሌላው ቀርቶ በሁሉም የዞኑ ወረዳዎችና የገጠር ቀበሌዎች ሳቀር ሰፊ መሬት፣ እርሻና ማንኛውም ዓይነት ኢንቨስትመንት የማን እንደሆነና የት እንደሚገኝ እየሰለላችሁ ፎቶግራፍና መሰል መረጃዎችን አልሰበሰባችሁም? በእናንተ እምነት መታሰር ያለባቸው እነማን እንደሆኑ እየመለመላችሁ አላሳሰራችሁም? አሁንም ለእስራትና ሰቆቃ ሰዎችን እየመለመላችሁና እያጫችሁ አይደለም? አንተ አብረውህ ከሚሠሩት ጋር የተደራጃችሁት በክልሉ ምክትል ር/መሥተዳደር ታገሰ ጫፋሞና በአለማሁ አይደለም? ወዘተ” የሚሉ በርካታ ጥያቄዎችንና ሂሶችን ያነሱለታል፡፡ ለመቀበል ይቸገራል፡፡ ሌሎች እውነታውን በቅርበት የሚያውቁ ካድሬዎች ተራ በተራ እየተነሱየነበረውን ሁኔታ ሊክድ በማይችል መልኩ ያሳዩታል፡፡ በዚህን ጊዜ መካካድ እንደማያዋጣ ሲያውቅ ሁሉንም ነገር እነርሱ ከጠበቁትና ከተናገሩት በላይ ያምናል፡፡ በአጭሩ እንዲህ በማለት - “በርግጥ የምትሉትን ሁሉ አድርጌያለሁኝ፡፡ በሲዳማ ተወላጆች የተያዙ የከተማ ቤቶችንና ቦታዎችን መርምረን፣ ጎብኝተን ፎቶግራፍና መሰል መረጃዎችን አጠናቅረን ወዳዘዘን አካል አቅርበናል፣ ሌሎችን የንግድ ሥራዎችንና ተቋማትን የሲዳማ ተወላጆች የሆኑትን ለይተን በሁሉም የዞኑ አከባቢዎች ገጠርን ጨምሮ መርምረን ፎቶግራፍ ማንሳትን ጨምሮ መረጃዎችን ሰብስበናል፤ የሲዳማ ተዎላጆች ንብረት የሆኑ መፈልፈያዎችንም እንዲሁ፡፡ የታሰሩ ሰዎችን የመለመልነው፣ የጠቆምነውና ያሳሰርነው በርግጥ እኛ መሆናችንን ልንክድ አንችልም ሁሉም የሚያውቀው ጉዳይ ስለሆነ፡፡ አሁንም ይሄንኑ ሥራ እየሠራን ነው ያለነው፡፡ ይሄንን ስሠራ ግን ብቻዬን አይደለሁም በኮሚቴ ነው የሠራነው፡፡ ያውም ደግሞ ተመልምለን ተደራጅተንና ታዘን ነው፡፡ ከእኔ ሌላ 1ኛ) ጌታሁን ጋሮ፣ 2ኛ) ጸጋዬ ለሌጎ፣ 3ኛ) መንክር (የወላይታ ተወላጅ)፣ 4ኛ) ስሞን (የወላይታ ተወላጅ)  አሉበት፤ ወዘተ” ብሎ ይመልሳል፡፡ ይሄኔ ይሄንን ሁሉ እውነታ የማያውቁ “እጅ አንሺ” ካድሬዎች - “ለካስ አርሶአደሮቻችን ‘የክልል ጥያቄያችን ይከበር፣ ደኢህዴን አይወክለንም እውቅና ነፍገነዋል፣ ከእንግዲህ ደቡብ ተብለን አንጠራም’ የሚሉት እውነታቸውን ነው፡፡
የቱ ጋ ነው ታዲያ አብሮነት ያለው? ታዲያ ምኑን ከደኢህዴን ጋር አብረን ሆንን? ይህ ሁሉ ሲሆን ሽፈራው አንተስ የምታውቀው ምንድነው? ከእኛ የተሻለ አርሶአደሩ አስቀድሞ አውቋል ማለት ነው፡፡ ወዘተ” እያሉ ይጠይቁታል፡፡ አርሶአደሩማ ከእናንተ አንድና ሁለት እጅ ነው እንዴ የሚበልጠው? መቶ ጊዜ ነው የሚበልጣችሁ፡፡ ሽፈራውም ወትሮ ነገር ሲበላሽ እንደሚሆነው ሁሉ ደንግጦ አላውቅም ብሎ ሽምጥጥ አድርጎ ይክዳል፡፡ ለዛውም እየማለ ነው አለማወቁን የተናዘዘው አሉ፡፡ ለነገሩ መች አምኖ ያውቃል፡፡ አንድ ወር በተከታታይ ቢናገር የሁሉም ቀን ንግግሮቹና አቋሞቹ ይለያያሉ፤ ማለትም እርስ በርስ ይጋጫሉ፡፡
እዚህ ላይ ከካድሬዎቹ ንግግር (ሂስ-ግለሂስ) እስኪ ለጥቂት ጊዜ ወደ እኛ አተያየት እንመለስ - እኛ ስለዚህ ተባለ ስለተባለው እውነታ ልቅም አድርገን ከማወቃችንም በላይ ጽፈናል፡፡ እጅግ ካሳዘኑን ጉዳዮች አንዱም ይሄው ነው፡፡ ታዲያ እንዴት ብሎ ነው ሽፈራው የማያውቀው? በፍጹም የማይመስል ነገር ነው፡፡ ካላወቀም ቦታውን ለሚያውቅ ሰው ይልቀቅ እንጂ ይሄንን ካላወቀማ ምን ሊሠራ ነው የተቀመጠው? “እያወቀ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማ” እንዲሉ ሆኖ ነው እንጂ ልቅም አድርጎ ያውቀዋል፡፡ ለመሆኑ ካድሬዎቻችንና አመራሮቻችን ምን ሊሉን ፈልገው ነው አሁን ነቃን የሚሉን፡፡ በርግጥ ብዙሃኑ ይሄንን እውነታ ላያውቁ እንደሚችሉ እኛም እናምናለን፡፡ የሚያውቅ ዓይነቱ መች ተመረጠና ቀድሞውኑ፡፡ መራጩስ ማን ሆነና፡፡ እንኳንስ በፌዴራል፣ በክልል፣ በዞንና በወረዳዎች ደረጃ ያሉ አመራሮችን ይቅርና የቀበሌ አመራሮችን እንኳ ሽፈራው ሳያውቅ መሾም እንደማይቻል ሁሉም ያውቀዋል፡፡
የመሾሚያ መስፈርትም የሽፈራው ዘመድ፣ ጎሳ፣ በአምቻ ወይም በጋብቻ የሚገናኝ፣ ካልሆነም ታማኝ የሆነ የመሆኑ ጉዳይ ሲሆን ይሄንን የሚያሟላ ካልተገኘም በቀላሉ እሺ ሊል የሚችል፤ ታዛዥ የሆነ፤ የራሱ የሆነ ማንነትና አቋም የለሌው አገልጋይ፤ ደኢህዴን/ኢህአዴግ ለእኔ እናቴ፣ አባቴ፣ ሚስቴ፣ ሀብቴ፣ ልብሴ ነው እርሱ ከለሌ መኖር አልችልም (እኔ ካለ ደኢህዴን ምን ነበረኝ ሙየሌያም አልነበርኩም) ብሎ የሚል ሰው ነው ሲሾምና ሲያሾም የቆየው፡፡ ይህ ከላይ በጥቂቱም ቢሆን የዘረዘርነው እኛ ያልነው አይደለም በርካቶቹ የሽፈራው አመራሮችና ካድሬዎች ሲሉ የቆዩትና አሁንም የሚያምኑበት ጉዳይ ነው፡፡ ለአብነት ያህል እንኳን በክልል ደረጃ የእርሱ አማካሪ ተብየው አኔሳ በዚሁ ከሰሞኑ ስብሰባቸው ላይ አቋሙን ሲገልጽ እንዲህ ብሎ ነበር - “እኛ ከደኢህዴን ውጭ መኖር አንችልም፤ ደኢህዴን እኛን እርቃናችንን ያለነውን ልብስ ያለበሰን ነው፤ ስለዚህ ለሲዳማ ክልል አያስፈልገውም ወዘተ” ብሎ ነበር፡፡ ይሄንን አባባሉን ሲሰሙ ደኢህዴኖቹ (እውነተኛዎቹ ማለትም የአሁኑን ጠ/ሚንስትር ጨምሮ) ሳይሳለቁበትና ሳይንቁት አይቀሩም፡፡ ለነገሩ እነርሱ ቀድሞውንም ያውቋቸው የለም እነርሱን ከመናቅ አልፈው ህዝባችንንም የናቁት ከዚህ የተነሳ ነው፡፡
አንዳንዶቹ የህዝባችንን ማንነት ቀድሞውንም የሚያውቁ ቢሆንም ከፊሎቹ ሲዳማን በእነ ሽፈራውና አኔሳ መነጽር ማየታቸው አይቀርም፡፡ እውነተኛውን የህዝባችንን ማንነት የሚያውቁበት ጊዜ ግን ሩቅ አይመስለንም፡፡ ስለአመራሮቹ አመላመል የአሁኑ ጠ/ሚንስትርም አውቀውበት ከሽፈራው ጋር አብረው ሲያስፈጽሙ ቆይተዋል፡፡ እርሳቸውም ከዚህ ቀደም ሽፈራውን የመምረጣቸውም ጉዳይ እንዳሻቸው ዓላማቸውን ማስፈጸም ይችሉ ዘንድ ነው፡፡ ሽፈራው ጥሩ መሳሪያ ሆኗቸው ቆይቷል (ወደ መጨረሻ አከባቢ ታው ስለሚፈለግ ቢጠላም፡፡ ከነአካተው እንዳይወገድ የዛኔ ተሰናባቹ ጠ/ሚንስትር የሲዳማን ህዝብ የሚያባብሉበት ምርኩዝ ነበርና እነኃይለማሪያም እንዳሰቡት በቀላሉ ሊነሳላቸው አልቻለም፡፡ ስለዚህም ተጠላ)፡፡ ዋው! ይህ ማለት በአሁን ጊዜ ለወቅቱ ጠ/ሚንስትር ሽፈራው ከተራ መሳሪያነትም ባለፈ መልኩ አጥፍቶ ጠፊ ሆነላቸው ማለት ነው (suicide bomber)፡፡ ፈንድቶ እስከሚገላገል ከዚህ መቅሰፍት እግዝአብሔር ህዝባችንንና እኛን ይጠብቀን፡፡ አሜን፡፡
ሲዳማ እውነተኛ የሆነ፣ አቅም ያለውና ለሥርዓቱ ያለው ታማኝነት እንደተጠበቀ ሆኖ (ከዚህ ጋር ኢህአዴግ እንደማይደራደር እናውቃለንና) ለህዝብ ወገንተኛ የሆነና ህዝብ የሚወደው አመራር እንዳይኖር እነሃኃይለማሪያም ሆን ብለው ሲሠሩ እንደቆዩ ለማወቅ የፈለገ ሰው አሁን ያሉትን ተሿሚዎች ብቻ ማየት በቂው ነው፡፡ ለምን ቢባል በሐዋሳም ከተማ ሆነ በቀሪው የሲዳማ ዞን የትኛውንም ወሳን ሹመትም ሆነ ውሳኔ ለማስተላለፍ የእነአቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ፣ አቶ አለማየሁ (የደኢህዴን መሪ)፣ አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ አቶ መኩሪያ ሀይሌና ባልደረቦቻቸው ይሁኔታና ውሳኔ ወሳኝ ሆኖ እንደቆየ ይታወቃል፡፡ እነርሱ የፈለጉት ይሾማል፤ እነርሱ ያልፈለጉትአይሾምም፡፡ የሄንን ተግብረው ሲያበቁ ግን አቶ ኃይለማሪያም እውነተኛ አዛኝ መስለው “የሲዳማ ህዝብ ጥሩና ጠንካራ ህዝብ ነበር፤ ነገር ግን ምን ያደርጋል መሪ የለውም፡፡” ብለው እንደነበር ከራሳቸው አፍ የሰማ ሰው በየዋህነት እውነት ነው ብሎ ተቀበሎ ሲያወራ የሰማነው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ እውነት ነው በዚህ ሥርዓት ውስጥ መሪ የለውም፡፡ እንዳውም ገዳዩና ቀባሪው ነው ያለው፡፡
መሪ ያሳጡት አንዱና ዋነኛው ግን አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ነበሩ፡፡ ጉልቻ ቢለወጥ ወጥ አያጣፍጥ አለች አሉ በአጼው ያዘኑ አንዲት እናት፡፡ ያው አሁንም የሆነው እንዲህ ነው፡፡ ስለ እርሳቸው በርግጥ ከዚህ ቀደም በግርድፉ ብዙ ብንልም አሁን ግን ይሄንን ትልቅ የሃላፊነት ቦታ ከያዙ በኋላ ያልነው የለም፡፡ ትንሽ ስለእርሳቸው መጻፍ እንዳለብን እናምናለን፡፡ ለዚህ ግን አሁን ቅድሚያ ባንሰጥም አንድ ነገር ግን ማለት እንዳለብን አመንን፡፡
ልክ እርሳቸው እንደተሾሙ (እንደእርሳቸው አባባል እንደተበደቡ) የእርሳቸው “አድናቂዎች” ብዙ ብለዋል፡፡ ከተባለው በጥቂቱ እኛ
ዛሬ ማንሳት የፈለግነው - ‘አካዳሚካሊ’ ጥሩ መሠረት ያላቸው፣ በደቡብ ክልል ጥሩ አመራር ሰጥተው ስለነበር ከዚህም የተነሳ በእድገት ወደፌዴራል የተዛወሩና ጥሩ አመራር ሊሰጡ የሚችሉ ጥሩ ስብዕና ያላቸው ሰው እንደሆኑ ተነግሮላቸዋል፡፡ ከአንድ ነገር
በቀር እኛ በምክንያትና በመረጃ የተባለው ሁሉ ቢያንስ ከበፊቱ ማንነታቸው አንጻር ውሸት መሆኑን ለማንሳት እንወዳለን፡፡ በርግጥ
አንቱ የተባሉ የትምህርት ማንነት እንዳላቸው እኛም እንመሰክርላቸዋለን፡፡ ይህ ማንነታቸው ግን ተግባራዊ የሆነው ግን እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በዩንቨርሲቲ አከባቢ ብቻ ነው፡፡ በደቡቡ ክልል ስልጣን ላይ በነበሩ ጊዜ ግን በሲዳማ ህዝብ ላይ ያልፈጸሙት በደልና ደባ አልነበረም፡፡ በህዝባችን ላይ የራሳቸውን ወገን አስፍረዋል፤ ቁልፍ ቁልፍ በሆኑ የአመራር ቦታዎች የራሳቸው ወገን የሆነ ሰው (ወላይታ) እንዲሆን ሠርተው አሳክተዋል (ለምሳሌ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕረዝደንት ወንድማቸው እንዲሆን ፈልገው ቢሰሩም ተሰናባቹ ጠ/ሚኒስትር ተው ስላሏቸው ም/ፕረዝደንት አድረገው ሾመው አሁንም በስልጣን ላይ እንዳለ ይታወቃል፡፡ በሶዶ ዩንቨርሲቲ የአሿሿም ሁኔታ ግን ለማንም ግልጽ ነው)፡፡ በአሁን ጊዜ እንኳን በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ስድስት ክፍለ ከተማዎች ውስጥ ስድስቱ አመራሮች ወላይታ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ስብጥር የተባለው ሙሉ በሙሉ የሲዳማ አመራሮችን አስወግዶ በወላይታ ለመተካት ካልሆነ በስተቀር አሁንም የወላይታ አመራሮች ቁጥር የትየለሌ ነው፡፡ ወላይታ ባይሆን ቢያንስ ሲዳማ ያልሆነ የሚያምኑት ሰው እንዲሆን ተግተው ሠርተዋል፡፡ ለዘመና አብሮ ሲኖር አንድም ቀን ተቃቅሮ የማያውቅ የሲዳማና የወላይታ ህዝብ ጦር ተማዞ ነበረው በርሳቸው የአመራር ወቅት ነው፡፡ ሰላማዊ ተቃውሞውን ሊያሰማ የወጣውን ህዝባችን በደብዳቤ አዘው ያስጨፈጨፉም እርሳቸው ናቸው፡፡ ሌሎች ግብረአበሮች የሉም አላልንም፡፡ እንዲህ በቀላሉ ተዘርዝሮ የሚያልቅ ስላይደለ ቀሪውን በደል ግን ለአንባቢው ህሊና ተውን፡፡ እንግዲህ ይሄንን ያልነው ትንሽ ስለርሳቸው ያለፈ አስተዳደር ትንሽ ቢገልጽልን በሚል ተስፋ ነው እንጂ ያለፈ ቁርሾ ለመቁጠር አይደለም፡፡ በቅንነት ነው ያነሳነው፡፡ ዋናው ነገር ግን እርሳቸው የደቡብ አመራር በነበሩ ጊዜ መልካም አስተዳደር አልሰጡም፤ ሊሰጡም አልቻሉም፤ ይልቅ ከዚህ የተቀየሩት አከባቢው የሁከትና ነውጥ ቀጠና ስለሆነ ሄንን ለማርገብ ተፈልጎ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ በሹመት ነው የሚል አካል ካለ ግን መከራከር አንፈልግም፡፡ ለእኛ ግን ፍትህ እንዳልሰጡን፣ እርሳቸው ክልሉን ሲመሩም ሆነ አሁንም ከሩቅ ሆነው ሲቆጣጡሩ (ሲመሩ) ፍትህ አላገኘንም፡፡ ህዝባችን መልካም አስተዳደር ሊያገኝ ቀርቶ በአጠገቡ ሲያልፍ እንደነገሩ አልሸተተውም፡፡ አንድ አመራር ወይም መሪ የቱን ያህን ‘የአካዳሚ’ እውቀት ቢኖረው ሚዛናዊ አመራር መስጠት ካልቻለና መልካም አስተዳደር ካላሰፈነ አቅም አለው ሊባል ከቶ ከወዴት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ጥሩስ ስብዕናቸው የቱ ነው? የለም፡፡
ቢያንስ አልነበረም፡፡ ለወደፊቱ የሚሆነውን ግን በቅንነት አብረን ለማየት ወስነናል፡፡ ለወደፊቱ አይሳካላቸውም አንልም ምኞታችንም ይሄ አይደለም፡፡ እንዳውም ምኞታችን እንዲሳካላቸው ነው፡፡ ማለትም መልካም አስተዳደር መስጠት እንዲችሉ፣ የህዝቦችንን ጥያቄ እንዲመልሱ፣ ፍትህ እንዲሰጡና አንቱ እንዲባሉ በርግጥ ምኞታችን ነው፡፡ የሲዳማን ህዝብ ቁስል እንዲጠርጉና እንዲያክሙ ምኞታችን ነው፡፡ በርግጥ ይሳካላቸው ይሆናል ማን ያውቃል፡፡ እግዚአብሔር በዚህ ሊረዳን ፈልጎ እንደሆንና እርሳቸው ሲመደቡ የሆነው ዓይነት ያልተጠበቀ መልካም ነገር ቢሆን መልካም ነው፡፡ ይሄንን የምንመኘው ለርሳቸው ብለን አይደለም ለሀገራችን ብለን ነው፡፡ ሀገራችን ሲሳካለት ህዝባችንም ይሳካለታል፡፡ ዋናው ማጠቃለያውም ሆነ የነገራችንም ፍሬ ነገር ያለው ከዚህ ቀጥሎ ነው፡፡ በርግጥ ሲዳማ ከጎናቸው እንዲሆን የሲዳማን ጥያቄ ማክበርና የሲዳማ ክልል እውን እንዲሆን መፍቀድ አለባቸው፡፡ ለዚህ መሥራትና ዋጋ መክፈል አለባቸው፡፡ ስለዚህ መፍትሄው ህዝባችንን ማሠር ሊሆን አይችልም፡፡ ይልቅ መፍትሄው የታሰሩትን ልጆቻችንን መፍታት፤ ማሰርና ማሰቃየቱን ማቆም፤ በህዝባችን ላይ ተንጠላጥለው እንደመዥገር የሚበሉትን ከላይ በአንድም ሆነ በሌላ የጠቃቀስናቸውን መዥገሮች ማስወገድ፣ የህዝባችንን ጥያቄ መመለስ ነው፡፡ ይሄንን ካደረጉ የሲዳማ ህዝብ በሙሉ ከጎናቸው እንደሚሆን እሙን ነው፡፡ እኛም በዚህ እናምናለን፡፡ ይሄ ሳይሆን ግን፣ የሲዳማ ጥያቄ ሳመለስ ግን፣ የሲዳማ ቁስል ሳይሽር ግን፣ ሲዳማ ክልል ሳይሆን ግን አብሮነት አይታሰብም፡፡ እናም ሲዳማ ከጎናቸው ሊሆን ቀርቶ እንደወትሮው ሊታገላቸው ግድ ይላል፡፡ ከአምስት ሚሊዮን የሚበልጥ ህዝብ ሳይዙ ጉዞ ግን የሚሳካ አይመስለንም፡፡ አሁን ላይ ሆነው ግን ይሄንን ያለፈው ዓይነት አስተዋይነት የጎደለው አማራጭ ይመርጣሉ ብለን አንጠብቅም፡፡ በርግጥ አስተዋይ ያልሆኑ እንደሆን ሊያስቡት ይችሉ ይሆናል፡፡ በፊት ሞክረውታልና አይቀጥሉምም አይባልም፡፡
ህዝብን ሳይሰሙ ግን ስኬት የማይታለም ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ እዚህ ላይ እኛ አቋማችን ግልጽ ነው፡፡ በድፍን ጥላቻ ውስጥ
አልገባንም፡፡ እድል ሊሰጣቸው እንደሚገባ አምነናል፡፡ ለዚህም ከበደል ብዛት የተውነውን አንቱታም ጀምረናል፡፡ ሌላው አብሮነት
እንዲቀጥል ግን የርሳቸው አካሄድ ነው ወሳኙ፡፡
አመራሮቻችንና ካድሬዎቻችንም ደኢህዴን ምን ጊዜም ለሲዳማ ጥሩ እንደማይመኝና እንደማይተኛልን፣ ጥሩ ማሰብ ከጀመረም አሁንከሲዳማ ጋር ለመቀጠል ጊዜው እንዳለፈበት፣ ሲዳማ ክልል ካልሆነ ሌላ አማራጭ እንደለሌውና እንደማይቀበልም አውቀው ሲዳማ ክልል እንዳይሆን የመወሰንም መብትና ስልጣን እንደሌላቸው አውቀው ወደአእምሯቸው እንዲመለሱ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

ቸር እንሰምብት፡፡
ናት ሐመሶ
http://sidamaliberation-front.org/Sidama-Kilil%20-Question.pdf

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር