የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይጠበቅበታል

ሃዋሳ ጥቅምት 09/2005 የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የድርሻቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ገለፀ፡፡ በሀዋሳ ሲካሄድ የቆየው የክልሉ ትምህርት ቢሮ የ2004 አጠቃላይ የትምህርት ጉባዔ ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል፡፡ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች፣ ባለድርሻ አካላትና የትምህርት አመራሮች ማበረታቻ ሽልማትና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡ የቢሮው ኃላፊ አቶ መሃመድ አህመዲን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ ሁሉም የህብረተሰብ ከፍልና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል፡፡ ክልሉ ከፍተኛ በጀት በመመደብ የሳይንስ ዘርፍ ትምህርትን ለማጠናከር ኮምፒዩተሮች እንደሟሉና የቤተ ሙከራ ግብአቶችን በማቅረብ አበረታች ስራ እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመስራት ለትምህርቱ ጥራት ልዩ ትኩረት በመስጠትና በአግባቡ እንዲመራ በማድረግ በኩል ለሌሎች አርአያ እንዲሆን የሚያስችል ስራ ማከናወኑን አመልከተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከ30 ሺህ በላይ የወላጅና የመምህራን ህብረት አመራሮች በትምህርት ቤቶች በመደራጀት በየጊዜው የተለያየ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል ለትምህርት ቤቶች ድጋፍና ክትትል በማድረግ የትምህርት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ በማድረግ በኩል አበረታች ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡ በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት ካመጡት ተማሪዎች መካከል ተማሪ ቤተልሄም ታሪኩ፣ ገዛህኝ አበራ፣ ኢዩኤል ተከተልና ተማሪ ዲቦራ አበራ በሰጡት አስተያየት በትምህርት ቤቶች የተፈጠሩ አደረጃጀቶች፣ የመምህራን የዕለት ተዕለት ክትትልና አስፈላጊ የትምህርት ግብአቶች በመሟላታቸው ጥሩ ውጤት ሊያስመዘግቡ ችለዋል፡፡ መምህራኖቻቸው ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ የሚሰጧቸው ድጋፍ እንዲሁም ወላጆች ከትምህርት ቤት መልስ ብዙ ጊዜያችንን በጥናት እንድናሳልፍ የሚያደርጉት ዕገዛ ለጥሩ ውጤት አብቅቶናል ብለዋል፡፡ ከተሸላሚ መምህራን መካከልም መምህርት አልማዝ አስራት፣ መምህር ታረቀኝ ታሪኩና ወጁ ተፈራ በበኩላቸው የተሰጣቸው ሽልማት በትምህርቱ ዘርፍ የተቀመጡ ግቦችን በማሳካት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ራዕይ እውን ሆኖ ሁሌም እንዲታወስ ለማድረግ ከፍተኛ መነሳሳት ፈጥሮላቸዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር