ልዩነት ለዘለዓለም ይኑር!

ሰላም! ሰላም! እንዴት ናችሁልኝ? ‹‹እንደርሳለን ብለን ከመሸ ተነስተን፣ ስንገሰግስ ነጋ ምንድን ነው የሚሻለን?›› አለችላችሁ አንዷ አዝማሪ። እውነቷን ነው እኮ! ‹‹በዚህ አካሄዳችን እንኳን ልንደርስ የት እንደምንሄድም የምናውቅ አንመስልም፤›› ከእንቅልፌ እንደተነሳሁ ማንጠግቦሽን እንዲህ ብላት፣ ‹‹ኧረ ተረጋጋ። እንዴ ቅዠትና እውነትን ለይ እንጂ፤›› አለችኝ። ስንት መልካም ጅማሮዎች ባሉት በዚህ ጊዜ የእኔስ እንዲህ ማለት አይገርማችሁም?

‹‹የእኔ ባትሆኝ ይቆጨኝ ነበር፤›› አልኩ። የእውነት የእኛ አልሆን እያለን የሚያስቆጨን በዝቷል። ሌላ ምንም ሳይሆን የገዛ ኑሯችንን መውሰድ ትችላላችሁ። እኛ እየኖርነው የእኛ ይመስላል? እሱ በፈለገው እንጂ እኛ በፈቀድነው እንመራዋለን? ኧረ ጣጣ ነው ዘንድሮ ወገኖቼ! እውነቴን ነው የምላችሁ ልቤ ክፉኛ የሚዝለው እንዲህ እንዲህ ሳስብ ነው። የደላላ ልብ ጥቁር ድንጋይ ነው ያለው ማን ነው? ‹‹እኛም እኮ አንዳንዴ ሰው ነን፤›› አለች አሉ ጦጣ። ‘እኛም በቤታችን እህህ አለብን’ ሲባል ባትሰሙ ነው? ይህችን እንኳን የእኛ ሠፈር አባባል ስለሆነች ላትሰሙዋት ትችላላችሁ። አንድ ደፋር ነው አሉ፣ ‹‹ማንም ያለሙያውና ዕውቀቱ ስንት ቦታ እየገባ ነገር ሲያበላሽ እየታለፈ የእኛ ሠፈር በዚህ አባባል አትጠቆርም፤›› ብሎ የለፈፈው። ወይ የዘመኑ ፈጠራ!

ሁሉንም ነገር ካዛመድነው እዚህ አገር ስለሙያና ባለሙያው ብዙ ይወራል። በየዘርፉ ለሥራቸው ባላቸው ትጋት ምሥጋና የምንቸራቸው ሰዎች ጥቂት አይደሉም እኮ። ባናስተውለው ነው እንጂ! ታዲያ በዚያው ልክ ያለ ቦታው ገብቶ የሚያደናቁረውን ስታዩ የማማረሪያ ቃላት አይበቋችሁም። በነገራችን ላይ የዘንድሮ ቃሪያ አንሰፍስፎ አላቃጥል ያለን ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ያለቦታቸው የገቡ የሰው ቃሪያዎች በየጉዳይ ማስፈፀሚያው ስለሚያቃጥሉን እኮ ነው። ባሻዬ ባለፈው የጡረታ መብታቸውን በተመለከተ አንዳንድ የመንግሥት ተቋማት ሄደው ሲመጡ የማላውቃቸው ሰው አድርጓቸው ነበር። ‹‹ከልጅነት እስከ አዛውንትነት ዕድሜዬ ድረስ በኖርኩባት አገሬ እንዲህ ዓይን ያወጣ ሌብነት?›› አሉኝ እንደ እብድ አድርጓቸው። ‹‹ምን አጋጠመዎት?›› ስላቸው፣ ‹‹እንዴ? አንበርብር መነግሥት በሙሰኞች ላይ አልጨክን ብሎ እስከ መቼ በሁለት ቢላ ልንታረድ ነው? ግብር ስንከፍል ያው ደመወዛቸው ማለት ነው። እህ? ያለ እጅ መንሻ ሳያጉላሉ ማስተናገድን ለምኔ ያሉ ይመስላሉ፤›› ሲሉኝ እንዲያ ነው ነገሩ ብዬ ዝም አልኩ። ‹‹አቋራጭን እንደ ዕድገት መሰላል ተጠቅሞ በየመሥርያ ቤቱ ሕዝቡን የሚመዘብር ሁላ ደም እንደሚመጥ መዥገር እንጂ ሰው ነው ብሎ ለማሰብ ይከብዳል፤›› ያለኝ የባሻዬ ልጅ ትዝ አለኝ። እንግዲህ እንዲያም አልነው እንዲህ አብዮት የጠማው ዋነኛ ችግር ሆኖ ሙስና አብሮን ይኖራል። የአብዮቱ ዘመን መፈክር ትዝ አላለኝ መሰላችሁ? ‘በምን ትዝ አልኩሽ አነሳሽኝ ዛሬ?’ የሚለውም ዘፈን ጭምር!     

በዚህ መነሻውና መድረሻው በተዘበራረቀበት የሰው ልጅ የአኗኗር ሁኔታ መስመር አስምሮ መጓዝ እጅግ ከባድ ነገር ነው። በተለይ የሚሳካላቸው እጅግ በጣም ለጥቂቶች ነው። ከሕይወት አንፃር የሚሳካላቸው ጥቂት መሆናቸው ቢያሳዝነንም በሌላ በሌላ ግን እፎይ ልንልባቸው የሚገቡ አሉ ወዳጆቼ። ‹‹እንደ አንዳንድ ዳያስፖራዎቻችን ማለትህ ነው?›› ብሎ ጠየቀኝ የባሻዬ ልጅ። ‹‹ታዲያስ! እንደሚወራው ከሆነማ የሚሠሩት ሥራ የሚያስቡት ሐሳብ ነውር አይገልጸውም፤›› ስለው፣ ‹‹አንበርብር አሁን አንተ እንዲህ ስትል ቢሰሙህ እኮ ምን እንደሚሉ ታውቃለህ? ካድሬ ነው ብለውህ አንተንም የኢሕአዴግ ደጋፊ ያደርጉሃል። ችግር አለባቸው የሚላቸው ሁሉ ለእነሱ የመንግሥት ወገን ነው፤›› አለኝ። ታዲያ እንዳሰቡት ቢሆንና ቢሳካላቸው ምን ሊያደርጉንና ሊያደርጉልን እንደሚፈልጉ ማሰብ ይከብደኛል። አይገርማችሁም? የማይከብድ ነገር መማር ብቻ ሆነ አሉ አንዳንድ ፎጋሪዎች። ‹‹ሲማሩም ሆነ ተምረው መክበድ ድሮ ቀረ፤›› ይላሉ እነባሻዬ። በተረፈ ሌላው ግን ያንገዳግደናል። ኑሮና አንዳንዱ ፖለቲካማ እንጃለት ማብረጃውን!     

አንድ በይደር አቆይቼ የምጨርሰው ሥራ ስለነበረኝ ማንጠግቦሽ ሳታየኝ ተነሳሁላችሁና ወጥቼ ገሰገስኩ። መቼም እሷ ከአልጋ ወርዳ የሚታያት ቁርስ አሰናድታ አብረን መቀማመስ ነው። ብታየኝማ እህል ሳልቀምስ መውጣቴን በምንም ዓይነት ሁኔታ አትቀበለውም። ‹‹የዘመኑን የየዕለት ሰቀቀን እንኳን ሳንበላ በልተንም አልቻልነው፤›› ትለኛለች። ‹‹የበላና የተማረ ወድቆ አይወድቅም›› የሚባለውን ሰምታ ነዋ። እኛም ሲባል (ድሮ ነው ታዲያ) እናስታውሳለን። አሁን አሁን ግን ሰምቻት የማላውቅ አባባል ብትኖር ይህችው የበላና የተማረ የምትባለዋን ነው። ለምን አትሉም? ተበልቶም ተምሮም አልሆንል ብሏላ። ቀልዴን እኮ አይደለም! እንቀልድ ብንልስ አጠገባችን ያለው ተጨባጭ ሀቅ እንዴት ያስችለናል? ትንሽ እንደተጓዝኩ ይሞረሙረኝ ጀመር። የወጣሁበትን ሳላሳካ እንደማልመለስ ለራሴ ቃል ገባሁ። ኑሮ ሲወደድ አማራጩ እንዲህ ራስን ማበረታታት ነው። አይመስላችሁም? ‹‹መንግሥትም ግሽበትን መቆጣጠር ካልቻለ ከኢቲቪ ጋር ተባብሮ ኑሮን በፅናት ለመጋፈጥ የሚስችል ቅስቀሳ ቢያስደምጠን ሳይሻል አይቀርም፤›› ይለኛል የባሻዬ ልጅ። ‹‹ከወደቅንም የቻሉትን ያህል ተላትመዋል ብሎ ዶክመንተሪ ቢያሠራልን ቀላል ውለታ አይደለም፤›› ይለኛል። ነገረኛ ነው እኮ አንዳንዴ። ለ‹‹ሌጋሲ›› ማሰብ ማለት ከዚህ ይጀምራል አልኩና ለራሴ ብቻዬን በሳቅ ተንፈራፈርኩ!     

የቁሳቁስ ደላላ መሆኔ ስንት ነገር ያሳየኛል መሰላችሁ? ከአንዱ ወዳንዱ ስዘዋወር የማላየው ታሪክ የለም። እኔ ልሙት! አንድ ቤት ገብቼ የሰማሁትና ያየሁት ግን  አስደነገጠኝ። በጥሩ ሁኔታ የተያዘ ቁም ሳጥን በአዲስ ሊተካ ተፈልጎ እሱን ተዟዙሬ እያየሁ ዋጋ እገምታለሁ። ባል ሚስትን ‹‹ያን የምወደውን እንቁላል ፍርፍር በሥጋ ሥሪልኝ?›› እያለ ይለማመጣል። ‹‹ራስህ አትሠራም? ገረድህ መሰልኩህ?›› ስትለው ጆሮዬን ተጠራጠርኩ። ሙያሽ ናፈቀኝ ማለት ነው ይህን ያህል የሚያናግር ብዬ ክው አልኩ። በዚህ ዓይነትማ ምን ኑሮ ብቻ ተወደደ? የሚስቶቻችንም እጅ ነው እንጂ! ሲገኝም እኮ ጣፍጦ ካልተቀመሰ ዋጋ የለውም። የእኔን ትዳር ባየ ቁጥር፣ ‹‹አንበርብር እንዳንተ የታደለ ሰው አለ?›› የሚለኝ ትኩስ ጎጆ ወጪ ወዳጅ አለኝ። ‹‹እንዴት?›› ስለው፣ ‹‹የእኔዋ እኮ እንትን አማረኝ፣ እንትን የሚባል ቤት ተከፍቷል፣ እዚያ ሄደን እንብላ ቅብጥርሶ እንጂ እስኪ ዛሬ ሙያዬን ቅመሰው ብላ አመስግኛት አላውቅም፤›› ይለኛል ምርር ባለ ድምፀት። 

እንግዲህ ሁሉም እንደሚያውቀው ማንጠግቦሽን በጣም የማከብራትና የምወዳት ባለቤቴ ናት። ሴቶች ወደ ማጀት ወንዶች ወደ ደጅ የሚባል የአረጀ የአፈጀ ተረት እኛ ቤት አይሠራም። ግን የተፈጥሮ ነገር ሆነና ከእኔ በላይ እሷ ጓዳ ስትገባ ነገሩ ሁሉ ይሰካካላታል። እጇ እንዴት ባለሙያ ነው መሰላችሁ? ሙያ በባለሙያና አቅሙ ባለው ሰው ሲከውን ወደር የለውም ያልነው እኮ ለዚህ ነው። የውዷን ባለቤቴን እጅ ለምጄ ደጅ ለደጅ በየካፌው የማባክነው ረብጣ የለም እላችኋለሁ። መተባበር ሳይረሳ ነው ታዲያ። መታደል ነው አትሉም?!

የእኩልነት ትርጉሙ የተዛባባቸው እህቶቻችን አንዳንድ ያልተገባ አመልና ባህሪ ሲያሳዩ ብዙ የምታዘብበት ሁኔታና ወቅት አያሌ ነው። ለአገርና ለዓለም ስንጠብቃቸው አንድ ታዋቂ ‹‹ብራንድ›› ቻፒስቲክ እንደ ትልቅ ሥራ በፍለጋ ቀንና ሳምንት ሲያቃጥሉ ሳይ እጅግ አዝናለሁ። ታዲያ አንዷን መንገድ ላይ መሬት መሬቱን ስታይ አገኘሁዋት። የጣለችውን ዕቃ እንደምትፈልግ ጠረጠርኩ። በጠዋቱ ምን ዕቃ ጣልሽ ስላት እንባዋ ዱብ ዱብ አይል መሰላችሁ። ወርቅ ይሆን? የለም የአልማዝ ፈርጥ መሆን አለበት እያልኩ ከራሴ ጋር እሟገታለሁ። ‹‹እህቴ ለቅሶ ምን ይፈይዳል? ንገሪኝ የጠፋብሽን?›› ስላት ‹‹ማታ ወደቤት ስገባ እዚህ ጋ ነው የጣልኩት፤›› አለችኝ። ‹‹እኮ ምንድነው እሱ?›› ስላት ጭንቅ ብሎኝ ‹‹ቻፒስቲክ›› ብላኝ እርፍ። እውነትም ሥራ አጥነት ተስፋፍቷል። ይኼ ዘመናዊነት ያልደረሰበት ሥፍራና ሰው እንዳለ አስተዋልኩ!

ውበታቸውን ለመጠበቅ የውዴታ ግዴታ እንዳለባቸው ባምንም ከልክ ያለፈ የሚመስለኝ ወቅት ግን ተደጋጋሚ መሆኑን ሳልናገር ማለፍ አልችልም። በበኩሌ እንደማንጠግቦሽ ቆንጆ ያለ አይመስለኝም። (ለራስ ሲቆርሱ አትሉም?) ታዲያ ይህ ስጦታ እንዲጠበቅና በአግባብ እንዲያዝ የበኩሌን ሚና ተጫዋች ነኝ። ‹‹ባለማወቅ የተገፉትን ግፍ ዛሬ በሚያስንቃቸውና በሚያዋርዳቸው ቦታ ለማካካስ ሲቻኮሉም ሳይ ወይ ጊዜ እላለሁ። ታዲያ ሁሉም አይደሉም። ፈርጦችም ደግሞ አሉ። ለአገርና ለወገን ሐሳባቸውና አርዓያቸው ሰፊ የሆኑ እንስቶችን ስታይ ምነው እናንተን ባደረገን ያሰኛሉ፤›› ይለኛል የባሻዬ ልጅ። የባሻዬ ልጅ እንደኔው ይኼ ጉዳይ ዘወትር እንዴት እንደሚከነክነው ባያችሁ። ‹‹አንበርብር ዘንድሮ እኮ ትርጓሜው ገደለን፤››  ይለኛል። ‹‹እንዴት?›› ስለው፣ ‹‹እንጃ ብቻ ይኼ እኩልነት በደንብ የገባን አይመስለኝም። ለትምህርት፣ ለሥራ፣ ለፖለቲካ ተሳትፎና ለመሰል ተግባሮች እኩል መሳተፍ አለብን ስንባል ከቡቲክና ከፋሽን እልፍ አልል ብለን፣ በሚጠበቁብን ትልልቅ ሥፍራዎች ላይ መታየት አቅቶናል፤›› ይለኛል። ይኼ ግን ፆታ የሚመርጥ አይመስለኝም። ታዲያ ‹‹ምን ታደርገዋለህ?›› ብዬ ዝም ነው። ክር ቢያከሩት ይበጠሳል ነዋ ስንል የኖርነው!

በሉ እንሰነባበት። የሄድኩበትን ጉዳይ ረፋዱ ላይ ጨራርሼ ደህና ረብጣ መቁጠሬን ሳረጋግጥ ዳቢትና ሻኛ ባይኔ ላይ ሄዱ። የሚያምረንና የሚመጥነን ማስታረቅ እንዴት ከባድ እንደሆነ እንደኔ ደህና ዝግ ስትዘጉ ታውቁታላችሁ። ብቻ ምን አባቱ ሺሕ ዓመት አይኖር አልኩና መቼም ብቻዬን መቁረጥ አልወድም ደውዬ የባሻዬን ልጅ ጠራሁት። አስቆርጠን በአዋዜ መተምተም እንደጀመርን የባሻዬ ልጅ ጨዋታ ጀመረ። ‹‹እኔምለው አንበርብር ሰሞኑን አንድ የአገራችን ታላቅ ባለሀብት ምን እንዳሉ ሰማህ?›› አለኝ። ‹‹ምን አሉ?›› ብለው፣ ‹‹ነጋዴዎች ስንባል ቀጣፊዎች ነን ብለው መንግሥት አንዳንዴ ዓይኑን ቢጨፍንልን ጥሩ ነው አሉ ተባለ፤›› ብሎኝ አዋዜው ላይ አነጣጥሮ ዝም አለ። ምን ሊለኝ እንደፈለገ አልገባኝም። እናስ ስለው፣ ‹‹መንግሥት የሕዝብ ተወካይ ነው። ሕዝብ ነው የሾመው። እናም አላግባብ የሚባክን ሀብትን እየተከታተለ ሥርዓት ማስያዝና ለሕዝብ ማሳወቅ አለበት። ለዚህ ነው ሕዝብ መንግሥትን ወክለኝ ያለው። የእኝህ ሰው አባባል ከዚህ ተወካይነቱ ውረድ ማለት አይመስልህም?›› ሲለኝ የፈራሁት መጣ አልኩ። በፍጥነት ያጠቀስነው አዋዜ ማለቁን አየና አዋዜ ጭማሪ ጠይቆ፣ ‹‹እንዲህ የቁርጥ ፍቅር ላይ የጣለን እኮ አዋዜ የተባለው ማጣፈጫ ነው። 
ቆንጠጥ ሲያደርገን ጣዕሙ ይታወቀናል፤›› ብሎኝ ዝም ሲል ከጥያቄው ጋራ የአዋዜ ትንታኔውን እንዳገናኘው የፈለገ መሰለኝ። ጭማሪ አዋዜው እስኪመጣ ትንሽ ካረፍን በኋላ ሲመጣ እውነትም ጣዕሙ የበለጠ ሆነ። ‘ያለ አዋዜ ቁርጥ ያለ መንግሥት አገር’ እንደማይታሰብ ገባኝ።

ማወራረጃ ፍለጋ የተለመደችው ግሮሰሪ ስንደርስ የሐበሻ ልጆች ነገን የረሱ እስኪመስሉ ድረስ ያንቆረቁሩታል፡፡ ከጂን እስከ ቢራ፣ ከቢራ እስከ ቮድካ፣ ሁሉም እንደቅሙ ይመገምጋል፡፡ ወጉም ከኳስ ጨዋታ እስከ አሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎች ፉክክር ድረስ ጦፏል፡፡ ከሪያል ማድሪድና ከባርሴሎና ኤል ክላሲኮ እስከ ባራክ ኦባማና ሚት ሮምኒ ድረስ ይሰለቃል፡፡ ወደ አገር ወስጥ ስንመለስ ከገበያው ውጣ ውረድ እስከ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ድረስ የማይባል የለም፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ ሞቅ ያላቸው ከተከፈተው የሙዚቃ ቅኝታ ጋር ድምፃቸውን ሞርደው ያንጎራጉራሉ፡፡ የባሻዬ ልጅ ይኼንን ትዕይንት በተመስጦ እያየ፣ ‹‹ምነው ሁሉም ሰው በመረጠውና በፈለገው መንገድ ሕይወቱን እንዲመራ ቢደረግ?›› አለኝ፡፡ ምን ለማለት ፈልጎ ይሆን በማለት፣ ‹‹አልገባኝም›› ስለው፣ ‹‹አንበርብር አባባሌ ግልጽ ነው፡፡ ማንም ሰብዓዊ ፍጡር የፈለገውን የመደገፍ፣ ያልመሰለውን በሰላማዊ መንገድ የመቃወም፣ የሚፈልገውን አመለካከት የመያዝ መብቱ ቢከበርለት፤›› ሲለኝ በውስጤ ልዩነት ለዘለዓለም ይኑር አልኩ፡፡ መልካም ሰንበት! 

http://www.ethiopianreporter.com/component/content/article/304-delalaw/7968-2012-10-06-10-34-10.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር