ባለፉት ሁለት ዓመታት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ የተጀመረው ጥረት ውጤት እያስገኘ ነው-ሚኒስትር ደሴ


አዲስ አበባ ጥቅምት 6/ 2005 ባለፉት ሁለት ዓመታት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ የተጀመረው ጥረት ውጤት እያስገኘ መሆኑን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ አስታወቁ። የቅጂ መብት ጥሰት መጠን ከ95 በመቶ ወደ 65 በመቶ መውረዱንም ገልጸዋል። ሚኒስትሩ አቶ ደሴ ዳልኬ ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ የተጀመረውን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ዘላቂነት እንዲኖረው ጠንካራ አገራዊ የቴክኖሎጂ አቅም የመገንባቱ ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል። በአገሪቱ የውጭ ቴክሎጂዎችን የመማር የማላመድና የመጠቀም አቅም አሁንም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቢሆንም፤ ባለፉት ሁለት አመታት ግን አመርቂ የሚባል መሻሻል ተመዝግቧል።
ፈጣኑን የኢኮኖሚ እድገት በሳይንስና ቴክኖሎጂ እውቀት እንዲታገዝ አገራዊ ጥረት እየተደረገ መሆኑንምተናግረዋል። የዩኒቨርሲዎችና የኢንዱስትሪዎች ትስስርን ከማጠናከር አኳያም የተሻለ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል። አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማፈላለግ የማስገባትና የመጠቀም አቅምን የሚያዳብሩ የአሰራር ሥርዓቶች በመዘርጋታቸው ቴክኖሎጂን በማዛመድና በመቅዳት ረገድ ጥሩ ጅምሮች እየታዩ ስለመሆኑም አስረድተዋል። ቴክኖሎጂን አስመስሎ በመስራት ከውጭ የሚገቡትን በአገር ውስጥ በማስቀረት ረገድም ተስፋ የሚሰጥ ውጤት እየታዬ መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ቅበላ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ የሰው ኃይል ልማት ፍላጎት ጋር እንዲጣጣምና የተግባር ስልጠናውም ከማምረቻና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር የማስተሳሰሩ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ከሆነ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የቅጅ መብት ጥሰትን ለመቆጣጠር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በተካሄደው የጋራ ጥረት የሚያበረታታ ውጤት ተገኝቷል። 
በአሁኑ ወቅት የቅጅ መብት ጥሰት በአገር አቀፍ ደረጃ 65 በመቶ ገደማ ሲሆን፣ ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን ተከታታይ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በቅርቡ በፈጠራና የምርምር ስራዎች የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ስድስት ኢትዮጵያውያን ጨምሮ 204 ግለሰቦች በአገር አቀፍ ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሸለሙም ገልጸዋል። ከተሸላሚዎቹ መካከልም 60ዎቹ ሴቶች ሲሆኑ የእውቅና ሰርተፊኬትን ጨምሮ የሜዳሊያና መጠነኛ የገንዘብ ሽልማት ይበረከትላቸዋል ሲል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር