ስለድጐማ በጀትና ገቢዎች ድልድል በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር ታቅዷል



አዲስ አበባ፡- በ2005 በጀት ዓመት የድጐማ በጀትና የገቢዎች ድልድልን በተመለከተ በቂ ግንዛቤ የማስፋፋት ሥራ እንደሚያከናውን ፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።
በምክር ቤቱ የድጐማ በጀትና የገቢዎች ድልድል ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ትናንት በተካሄደው የምክር ቤቱ አራተኛ ዘመን ሦስተኛ ዓመት አንደኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ የቋሚ ኮሚቴውን የ2005 በጀት ዓመት ዕቅድና የትኩረት አቅጣጫዎች ባመለከቱበት ወቅት እንደገለጹት፤ ዘንድሮ ግንዛቤ የማስፋፋት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት ተግባራዊ ይደረጋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትንና የቋሚ ኮሚቴ አባላትን አቅም መገንባት፣ የክልል መንግሥታት የገቢ አሰባሰብና የቀመር ባለሙያዎችን አቅም ማጠናከር እንዲሁም የክልል ምክር ቤት አባላት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትንና የልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ተወካዮችን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ በስፋት እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
የክልሎች ገቢ የመሰብሰብ አቅም የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በመውሰድና የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በመገምገም እንዲጠና የሚደረግ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሽፈራው፤ ሥራው በየወቅቱ መከናወን እንዲችልና ተቋማዊ ባለቤት እንዲኖረው ጥናታዊ አስተያየት ተዘጋጅቶ እንደሚቀርብ አመልክተዋል።
ለድጐማ በጀት ቀመር ዝግጅት ከተለያዩ ምንጮች የተገኙ ልዩ ልዩ መረጃዎች ጥቅም ላይ የዋሉ ቢሆንም ለቀመር ዝግጅቱ ዋነኛ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ያገለገለው ከደቡብ አፍሪካ ስታትስቲክሰ መሥሪያ ቤት የተገኘው እንደሆነ ገልጸዋል።
በፌዴራል ደረጃ በአዲሱ የድጐማ በጀት ማከፋፈያ ቀመር ላይ አገራዊ መድረክ የማዘጋጀት ዕቅድ መኖሩን ያመለከቱት አቶ ሽፈራው፤ ከተያዘው የበጀት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ በተደረገው የድጐማ በጀት ማከፋፈያ ቀመር ላይ በዘርፉ ምሑራን የምክክር ዓውደ ጥናት እንደሚዘጋጅ አብራርተዋል። በዓውደ ጥናቱ ላይ ስለቀመር ማዕቀፎች፣ መርሆዎች፣ ይዘቶችና አመልካቾች ጠንካራና ደካማ ጐኖች በጥልቀት ገምግሞ ስምምነት የተደረሰባቸውን ነጥቦች ለሚቀጥለው ቀመር ዝግጅት ለግብአት በሚሆን መልኩ እንደሚያደራጅ ተናግረዋል።
የመረጃ ጥራትና ወቅታዊነትን ለማረጋገጥ ተከታታይ የሆነ ጥናትና ምክክር እንደሚካሄድ የገለጹት አቶ ሽፈራው፤ « የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ፍላጐት መሠረት ያደረገ የመረጃ ጥናት እንዲያካሂድ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል» ብለዋል።
ከሥራው ስፋትና ክብደት አኳያ የማስፈፀም አቅም ማነስ፣ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የሚኖረው ቅንጅትና ትብብር ማጣት እንዲሁም ለሚከናወኑ ሥራዎች የበጀት ችግር በበጀት ዓመቱ የዕቅድና የትኩረት አቅጣጫዎችን በማስፈፀም ሂደት ወቅት ያጋጥማሉ ተብለው የተቀመጡ ስጋቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል። የምክር ቤቱን ባለሙያዎችንና ሌሎች አጋር አካላትን የቅንጅት አሠራር ለማጠናከር ትኩረት በመስጠትና ከመንግሥት በጀት በተጨማሪ ሌሎች ምንጮችን በማፈላለግ ችግሩን ለመፍታት መታሰቡን አቶ ሽፈራው አመልክተዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ካሣ ተክለብርሃን በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በአገሪቱ ሀብት ሁሉም ዜጐች እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዲፈጠር መንግሥት ጠንክሮ ይሠራል።
ቀመሩ ፍትሐዊነትን ያረጋገጠ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቶ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው፤ ተግባራዊነቱን ለማረጋገጥ ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። 
የድጐማ በጀትና የገቢዎች ድልድል ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በ2005 በጀት ዓመት ዕቅድና የትኩረት አቅጣጫ ብሎ የለያቸውን ሥራዎች የምክር ቤቱ አባላት በሙሉ ድምፅ አፅድቀዋቸዋል። 
http://www.ethpress.gov.et/ethpress/main/news.php?newsLocation=home&newsInstruction=headline&newsId=9562

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር