ሲዳማን ጨምሮ ቀይ መስቀል በደቡብ ክልል ለአምስት ዞኖች አምቡላንስ አከፋፈለ


አዋሳ መስከረም 21/2005 የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ አምቡላንሶችን ለአምስት ዞኖች አከፋፈለ። በክልሉ ከሚገኙ ቅርንጫፍ ማህበራት አምስቱ ከህብረተሰቡ ባሰባሰቡት ገንዘብና ከማህበሩ ከ18 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ እንዲገዙ ከታዘዙት 20 አምቡላንሶች የአስሩ ትናንት ርክክብ ተደርጓል። በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ የደቡብ ክልል ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የቦርድ ሰብሳቢና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታመነ ተሰማ እንዳሉት መንግስት በነደፈው ዕቅድ መሰረት የእናቶችና ህጻናት ሞትን ለመቀነስ ለሁሉም ወረዳዎች እንዲዳረስ እያደረገ ነው። መንግስት እየተገበረ ያለውን የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ እያደረገ ያለውን ጥረት መንግስታዊ ያልሆኑ ማህበራትና ህብረተሰቡ እያደረጉ ያለው ተግባር የሚያበረታታ መሆኑን ጠቁመው የደቡብ ቀይ መስቀል ማህበር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የገዛቸው አምቡላንሶች የእናቶችና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል። አምቡላንሶቹ ለታለመላቸው አገልግሎት ብቻ እንዲውሉ በማድረግ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡና የወረዳዎቹ ማዘጋጃ ቤቶች የነዳጅና አስፈላጊ ወጪያቸውን በመሸፈን ድጋፍ እንዲያደርጉ አቶ ታመነ አሳስበዋል። በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መኮንን ፋራ አዲስ የተገዙት አምቡላንሶች በክልሉ የነበረውን የአምቡላንሶች ጣቢያ ከ22 ወደ 44 የሚያሳድገው መሆኑን ጠቁመው የጋሞጎፋና ደቡብ ኦሞ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን 944 ሺህ ብር ወጪ በማድረግ ለደቡብ ኦሞ ዞን ሀመር ወረዳ አንድ አምቡላንስ መግዛታቸውን ተናግረዋል። አምቡላንሶቹ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች አረጋውያንና ነፍሰጡር ሴቶችን ወደ ህክምና በማድረስ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። የቤንች ማጂ ደቡብ ኦሞ ጋሞጎፋ ሲዳማና ጉራጌ ዞኖች ቀይመስቀል ማህበራት አምቡላንሶቹን የተረከቡ ሲሆን ቀሪዎቹም አስር አምቡላንሶች በቅርቡ እንደሚገቡ ገልጸዋል።
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=2644&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር