የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ45ኛ ዳኞችን ሹመት አፀደቀ



አዲስ አበባ፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ያቀረቡትን የ45 ዳኞች ሹመት አፀደቀ። የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስን ዓመታዊ የመክፈቻ ንግግር ሞሽን ላይ በሚቀጥለው ሳምንት ለመነጋገር ወሰነ።

ምክር ቤቱ ትናንት ባካሄደው ሦስተኛ የሥራ ዘመን በአንደኛ መደበኛ ስብሰባው ሹመታቸውን ካፀደቀላቸው 45 ዳኞች መካከል አምስቱ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ዘጠኙ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲሁም 31ዱ ለመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በእጩነት የቀረቡ ናቸው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ስለቀረቡት እጩ ዳኞች ለምክር ቤቱ በዝርዝር ያስረዱት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መለስ ጥላሁን፤ ዳኞቹ የሕግ ምሩቃን፣ በሙያው በቂ ልምድ ያላቸው፣ ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ፣ በሥነ ምግባራቸው መልካም ስም ያተረፉና በዳኝነት ሙያ ለመስራት ፍላጎት ያላቸው መሆናቸውን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።
እጩ ዳኞቹ የተመረጡበትን መስፈርት በተመለከተ አንድ የምክር ቤቱ አባል የእጩዎቹ ምርጫ የብሔር ስብጥርን በተለይም የታዳጊ ክልሎችን ግምት ውስጥ ያስገባ እንዳልሆነ አስተያየት ሰጥተዋል። ሌላኛው የምክር ቤቱ አባል ደግሞ የዳኞቹ ሹመት የተረሱ ብሔረሰቦችን ሲያካትት በታሪክ የመጀመሪያው እንደሆነ በመግለጽ ሹመታቸው ከፀደቀላቸው ዳኞች መካከል የአርጎባ ብሔረሰብ አባል በመካተታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም በነበረው የዳኞች ሹመት ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ብቻ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ግን ከግል የትምህርት ተቋማት የተመረቁትን ጨምሮ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተካተቱበት መሆናቸውን በማድነቅ ይህ ሊለመድ እንደሚገባ አስተያየት ሰጥተዋል። ስለ እጩ ዳኞቹ በሚገባ ለማወቅ እንዲቻል መረጃቸው ከአንድ ወር በፊት ቢደርሳቸው የተሻለ እንደነበረ አስተያየት ሰጥተዋል። ለመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተቀረቡት እጩዎች ዕድሜአቸው ከ30 ዓመት በታች መሆን እንዳልነበረበት ሃሳብ ሰጥተዋል።
አቶ ግርማ «አብዛኛው እጩ ዳኞች ከክልል ወደ ፌዴራል መምጣታቸው የክልሎችን የባለሙያ እጥረት አያስከትልም ወይ?» የሚል ጥያቄም አቅርበዋል።
ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡት ጥያቄዎችና አስተያየት በምክር ቤቱ የሕግ፣ የፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ በሰጡት ምላሽ፤ የዳኞቹ ምልመላ በ2002ዓ.ም በፀደቀው የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አዋጅ መሠረት የተከናወነና አዋጁ ቀደም ሲል የነበረውን ክፍተት የፈታ መሆኑን ገልጸዋል።
አሰራሩን ግልጽ፣ ፍትሐዊ እና ተደራሽ ለማድረግ ማስታወቂያ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በማውጣት ለሁሉም ክልሎች በወረዳና በዞን በግልጽ ቦታ እንዲለጠፍ መደረጉን ገልጸዋል። በወጣው ማስታወቂያ መሠረት መስፈርት ያሟሉ የጽሑፍና የቃል ፈተና እንዲወስዱ ተደርጎ በገለልተኛ አካል ታይቶ ያለፉ መሆናቸውን አስረድተዋል። የቃልና የጽሑፍ ፈተናውን ካለፉ በኋላም ይሰሩበት ከነበረው ተቋም ስለ ሥነ ምግባራቸው፣ ስለታማኝነታቸውና ከሙስና የጸዱ ስለመሆናቸው ለማረጋገጥ ጥረት መደረጉን አስታውቀዋል። የሴቶችና የብሔር ተዋጽኦ ግምት ውስጥ መግባቱን ገልጸዋል። ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ ለማከናወን አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ መውሰዱን አመልክተዋል።
ምክር ቤቱ በግማሽ ቀን ውሎው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ መስከረም 28 ቀን 2005 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መደበኛ ስብሰባ ላይ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ የቀረበውን የድጋፍ ሞሽን በቀጣይ ሳምንት ለማየት ወስኗል። የምክር ቤቱ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ እና 3ኛ አስቸካይ ስብሰባ ቃለ ጉባኤዎችንም አጽድቋል። 
http://www.ethpress.gov.et/ethpress/main/news.php?newsLocation=home&newsInstruction=headline&newsId=9597


Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር