በሲዳማ ዞን በአዲሱ በጀት ዓመት 3 መቶ ሚሊዮን የሚጠጋ ገቢ የመሰብሰብ እቅዱን ለማሳካት እየሠራ እንደሚገኝ የዞኑ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡


ጽህፈት ቤቱ ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ ክፍሎችና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት በገቢ ግብር አዋጆች፣ ደንቦች እንዲሁም መመሪያዎችና በሂሳብ አያያዝ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰሞኑን ሰጥቷል፡፡
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተሻለ ቡላዶ እንደገለፁት ሥልጠናው ቀደም ሲል በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድ ይታዩ የነበሩ የግንዛቤ ክፍተቶችን ለመቅረፍና በዘንድሮው የበጀት ዓመት ከአምናው የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ የበለጠ አቅም ለመፍጠር የሚያስችል ነው፡፡

በተጨማሪ እሴትና ተርን ኦቨር ታክስ እንደዚሁም በገቢ መሰብሰቢያ ደረሰኝ ላይ የሚስተዋሉ የማጭበርበር ድርጊቶችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሥልጠናው ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡
በመንግስት ታትመው የሚሰራጩ ደረሰኞችን ወደ ጎን በመተው ህገ ወጥ ደረሰኞችን የሚጠቀሙ አንዳንድ ነጋዴዎች መኖራቸው እንደተደረሰባቸው የጠቆሙት ኃላፊው እንዲህ አይነት ድርጊት እስከ አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚያስቀጣም አስታውቀዋል፡፡
በጽህፈት ቤቱ የገቢ ጥናት ትምህርትና ሥልጠና ዋና ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ደሳለኝ ጋንጌ በበኩላቸው የንግዱ ማህበረሰብ ግብሩን በወቅቱ በመክፈል የዜግነት ግዴታውን መወጣት እንዳለበት አሳስበው ለዚህም የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ዘገባው የሲዳማ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነው፡፡
http://www.smm.gov.et/_Text/26MesTextN305.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር