መንግሥት ባከናወናቸው ተግባራት የዋጋ ግሽበቱ ወደ 19 በመቶ ዝቅ ማለቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ገለጹ


አዲስ አበባ ጥቅምት 6/2005 መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ባከናወናቸው ተግባራት ባለፈው ዓመት የዋጋ ግሽበቱ ከ40 በመቶ ወደ 19 በመቶ ዝቅ ማለቱን የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አስታወቁ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ መስከረም 28 ቀን 2005 የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ስብሰባ ላይ ያደረጉትን ንግግር አስመልክቶ ከምክር ቤት አባላት በቀረበው የማሻሻያ ሞሽን ላይ ተወያይቶ አጽድቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ እንደገለጹት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር መንግሥት በገበያ ውስጥ ያለውን የገንዘብ መጠን በመቆጣጠር፣ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግና የንግድ ሥርዓቱን ዘመናዊ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት የዋጋ ግሽበቱ ዝቅ ብሏል።

መንግሥት የሚያጋጥመውን የበጀት ጉድለት ለመሸፈን የብሔራዊ ባንክ ብድር ሳይወስድ የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድን በመሸጥ የበጀት ጉድለቱ ከ1 ነጥብ 2 በመቶ እንዳያልፍ ማድረጉን አብራርተዋል። መንግሥት በጅምላ ንግድ ውስጥ የሚታዩትን ችግሮች ለማስወገድ ያካሄደው ጥናት በማጠናቀቁ የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር ጥናቱ በዚህ ዓመት ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል። የዋጋ ግሽበቱን በመቆጣጠር ረገድ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ወሳኝ በመሆኑን በመገንዘብ ባለፈው ዓመት ከ1ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያና ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ምርጥ ዘርፍ ለአርሶ አደሮች እንዲሰራጭ መደረጉን ተናግረዋል። የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት በተያዘው በጀት ዓመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ኃይለማርያም አመልክተዋል። እንዲሁም የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር መንግሥት ለዝቅተኛ የኀብረተሰብ ክፍሎች ስንዴ፣ ዘይትና ስኳር ምርቶችን ከውጭ በማስገባት ድጎማ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል። የሴቶችና የወጣቶችን የገቢ ምንጭ ለማሳደግ በርካታ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ርብርብ የሚያደርግ ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት የተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ዘንድሮም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። 

አንዳንድ ባለሀብቶች በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳለ አድርገው የሚፈጥሩት ውዥንብር የውጭ ምንዛሪ እጥረት ይገጥመናል በሚል የፈጠሩት በመሆኑ በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደሌለም አስረድተዋል። ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ የተሸጠው የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር በ12 ነጥብ 5 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን ገልጸዋል። የአገሪቱን የቁጠባ ባህል ለማሳደግ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ ላይ ከ6 ወደ 15 በመቶ ለማድረስ መቀመጡን ያስታወሱት አቶ ኃይለማርያም፤ ባለፈው ዓመት የዜጎች የቁጠባ ባህል ዘጠኝ በመቶ ማደጉን ተናግረዋል። መንግሥት በሁሉም የአገሪቱ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ባንኮችና አነስተኛ የቁጠባና የገንዘብ ብድር ፋይናንስ ተቋማት እንዲከፈቱ በማድረጉ የአገሪቱ የቁጠባ መጠን በ35 በመቶ ማደጉን አብራርተዋል። በአገሪቱ የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም የገንዘብ እጥረት እንዳያጋጥም የቁጠባ ባህልን ለማሳደግ በርካታ ተግባራት እንደሚከናወን አስረድተዋል። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በመገንባት ላይ የሚገኝ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ፣በአሁኑ ወቅት 11 ነጥብ 4 በመቶ አፈጻጸም መመዝገቡን ገልጸዋል። የባቡር መስመር ግንባታን ለማከናወን ከቻይና፣ ከጃፓንና ከደቡብ ኮሪያ መንግሥታት ጋር ስምምነት የተደረገ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የሚዘረጋው የባቡር መሥመር ግንባታ ባለፈው ሰኔ ወር 2004 መጀመሩን ተናግረዋል። የቴሌኮም ጥራት ላይ ችግር ያስከተለበት ምክንያት ከተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር መጨመርና በአዲስ አበባ ከተማ ረጃጅም ሕንጻዎች ግንባታ ጋር በተያያዘ የሞገድ መጨናነቅ በመፈጠር እንዲሁም የፋይቨር ኦፕቲክስ መሥመር በሕገ ወጥ ሰዎች በመቆረጡ ምክንያት እንደሆነም አስረድተዋል። የጥራት ችግሩን ለማስወገድ በረጃጅም ሕንጻዎች ላይ የሞገድ ማሰራጫ መሣሪያዎች ተከላ ይከናወናል። 

የፋይቫር ኦፕቲክስ መሥመር ከመሬት ውስጥ ይልቅ በኤሌክትሪክ ምሰሶች ላይ እንደሚዘረጋ አቶ ኃይለማርያም አስታውቀዋል። በተመሳሳይ በኤሌክትሪክ አቅርቦት ላይ የሚታየውን የኃይል መቆራረጥ ችግር ለማቃለል በኃይል ማሰራጫ መሥመሮች ላይ የሚደርስ ጉዳት ለመከላከል ኀብረተሰቡ ከፍተኛ ሚና እንዲጫወት አሳስበዋል። የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የጥራት ማረጋገጫ ፓኬጅን ተግባራዊ በማድረግ ባለፉት ዓመታት ጥሩ ውጤት መመዝገቡንና ጥረቱ የተሰጠው ትኩረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል። ዴሞክራሲንና መልካም አስተዳደር ለልማት ወሳኝ መሆኑን በመረዳት መንግሥት ዲሞክራሲንና መልካም አስተዳደር ሥርዓት ለመገንባት ከፍተኛ ርብርብ ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም በአንዳንድ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በመልካም አስተዳደር ችግር ሕዝብ እንደሚማረርባቸው መንግሥት እንደሚያውቅ ተናግረዋል። ሕዝብ የሚማረርባቸውን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የመልካም አስተዳደር ችግር ለማስወገድ ዘንድሮ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሁሉም የኀብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ እንደያደርጉና በተለይ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ ከፍተኛ ሚና ሊጫወት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የመልካም አስተዳደር ንቅናቄ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የኢህአዴግ አባላት ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባም አቶ ኃይለማርያም አሳስበዋል። በአዲስ አበባና በሌሎች አካባቢዎች የሚካሄደው ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን እንዲሁም በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግሥት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር እንደሚሰራም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር