ኢትዮጵያ የንቅናቄውን 15ኛ ዓለም ዓቀፍ ጉባዔ ከጥቅምት 12 ጀምሮ ታስተናግዳለች


አዲስ አበባ ጥቅምት 10/2005 ኢትዮጵያ 15ኛውን የትብብር ለታዳጊ ከተሞችና ልማት ንቅናቄ(ኮዳቱ)ን ዓለም ዓቀፍ ጉባዔን ለማስተናገድ ዝግጅቷን ማጠናቀቋን የጉባዔው ዝግጅት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከድርጅቱ ጋር በመተባበር ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ለአራት ቀናት በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ " የከተሞች ጉዞ ለከተሞች አደረጃጀትና እድገት" በሚል መሪ ቃል ይካሄዳል፡፡ የኮሚቴው ሰብሳቢና የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በድሉ አሰፋ ዝግጅቱን አስመልክቶ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ጉባዔው በከተማዋ የሚካሄደውን ፈጣን የለውጥ ጉዞ አጠናክሮ ለመቀጠል ያግዛል፡፡ ጉባዔው በከተማዋ በትራንስፖርት ዘርፍ ያለውን ዕድገት፣ ተሞክሮዎችንና አማራጮችን ለአገሪቷ በሚስማማ ሁኔታ ለመጠቀም እንደሚያስችልም አስረድተዋል። በጉባዔው ላይ ከ600 በላይ የከተሞች የትራንስፖርት አመራር አባላትና ባለሀብቶች እንደሚሳተፉበትና ከዚህ ወስጥ ከ250በላይ የሚሆኑት የአገር ውስጥ ተሳታፊዎች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም የከተማዋን እምቅ የኢንቨስትመንትና የንግድ አማራጮችን ለማስተዋወቅና የቱሪዝም መስህቦችን ለማስተዋቅ መልካም ዕድል እንደሚፈጥርም ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡ በጉባዔው ላይ የ30 አገሮች ተጨባጭ ተሞክሮዎች ይቀርባሉ ያሉት ሰብሳቢው፣በዚህም የሌሎች አገሮችን ልምድ ለመቅሰም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል፡፡ የጉባዔው ተሳታፊዎች አገሪቱን ለማወቅ የሚያስችላቸው ድረ ገጽ መከፈቱንና የትራንስፖርት አገልግሎት መዘጋጀቱን አቶ በድሉ ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም በእንግሊዝኛና በፈረንሳይና ቋንቋዎች ትርጉምና መረጃ በመስጠትና በማስተላለፍ በኩል ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣት ባለሙያዎች መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል፡፡ የዘርፉ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች፣ባለሀብቶች፣ ባለ ሆቴሎች፣የፀጥታ ኃይሎችና ሌሎች አካላት ለጉባዔው ስኬታማነት ሚናቸውን እንዲጫወቱ አቶ በድሉ አሳስዋል፡፡ ንቅናቄው እስካሁን በአውሮፓ፣ በእስያ ፣በደቡብ አሜሪካና በደቡብ አሜሪካና በአፍሪካ ጉባዔዎቹን ማካሄዱን ሰብሳቢው አስታውሰዋል፡፡ ንቅናቄው የአገሮችን ልምድ በማለዋወጥ፣የጋራ ችግሮችን በመፍታት፣ለመንግሥታትና ለከተሞች በጥናት የተመሰረተ ግብዓት በመስጠት ለሕዝቦች የተቃና እንቅስቃሴና የትራንስፖርት ፍሰት ላለፉት 32ዓመታት አገልግሎት የሰጠ ድርጅት መሆኑን መረጃዎች እንደሚያመለክቱ የዘገበው ኢዜአ ነው።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር