ለአህጉራዊ የየብስ ትራንስፖርት ትስስር ኢትዮጵያ የቤት ሥራዋን በማጠናቀቅ ዋዜማ ላይ ትገኛለች ፤ኢትዮጵያም የአፍሪካ አገራትን በየብስ ትራንስፖርት ለማገናኘት እየተገነቡ ካሉት ዘጠኝ ዋና መንገዶች የኬፕታውን-ካይሮ መንገድ ፕሮጀክት አካል የሆነውን የአዲስ አበባ-ናይሮቢ-ሞምባሳ አገናኝ መንገዶች ግንባታ ተያይዛዋለች። በዚህም መሰረት የዚህ ፕሮጀክት አገናኝ ለሆነው አዲስ አበባ-ሐዋሳ-ሀገረማርያም-ያቤሎ-ሜጋ-ሞያሌ መንገድ ግንባታ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡


የአፍሪካ አገራትን የንግድ ልውውጥ ለማፋጠን ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን የሚያጠናክሩና ድህነትን የሚቀንሱ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል፡፡ ይህን የአገራቱን ግንኙነት ለማጠናከርም ለመንገድ ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የ«ትራንስ አፍሪካን ሃይ ዌይስ»ፕሮጀክት ተቀርፆ ተግባራዊ እየሆነ ነው፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በ«ትራንስ አፍሪካን ሃይ ዌይስ" ፕሮጀክት የአህጉሪቱን ሀገሮች የሚያስተሳስሩ ዘጠኝ ዋና ዋና መንገዶች ይገነባሉ፡፡እነዚህም 56ሺ683ኪሎ ሜትር ይሸፍናሉ፡፡እነዚህ ዋና መንገዶች ከሰሃራ በታች በሚገኙ 41 ከተሞች የሚያልፉ ሲሆን፤ 500 ሚሊዮን ያህል ዜጎችንም ያገናኛሉ፡፡ የመንገዶቹ መገንባት የባህር በር ለሌላቸው አገራት የሚሰጠው ጠቀሜታም እጅግ የላቀ በመሆኑ መንገዱ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች የሚገኙ አገራት የመንገዱ አካል የሆኑ መንገዶች በመገንባት ላይ ናቸው።
ኢትዮጵያም የአፍሪካ አገራትን በየብስ ትራንስፖርት ለማገናኘት እየተገነቡ ካሉት ዘጠኝ ዋና መንገዶች የኬፕታውን-ካይሮ መንገድ ፕሮጀክት አካል የሆነውን የአዲስ አበባ-ናይሮቢ-ሞምባሳ አገናኝ መንገዶች ግንባታ ተያይዛዋለች። በዚህም መሰረት የዚህ ፕሮጀክት አገናኝ ለሆነው አዲስ አበባ-ሐዋሳ-ሀገረማርያም-ያቤሎ-ሜጋ-ሞያሌ መንገድ ግንባታ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡
የአዲስ አበባ-ናይሮቢ-ሞምባሳ መንገድ ፕሮጀክት አካል የሆነው የአዲስ አበባ-ሐዋሳ መንገድ በመጀመሪያው የመንገድ ልማት ዘርፍ መርሐ ግብር ከ10 ዓመት በፊት ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣94 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የሃገረማርያም-ያቤሎ መንገድም በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ እየተገነባ ይገኛል፡፡ ግንባታውም በግብፁ «ዓረብ ኮንትራክተርስ» እየተከናወነ ሲሆን፣ «ጓፍ ኢንጂነርስ አማካሪ መሐንዲሶች» ደግሞ የማማከሩን ሥራ ያከናውናል፡፡ ለግንባታውም የ740 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞለታል፡፡
ግንባታው እኤአ ሚያዝያ 11 ቀን 2011 የተጀመረ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ ሚያዝያ 10 ቀን 2014 ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃም ነው የሚጠበቀው። ለግንባታ የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችንና ቁሳቁስን በማጓጓዝ ረገድ በሥራ ተቋራጩ በኩል በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ድክመት መታየቱን የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ መሐንዲስ ሚስተር ጌርድ ቬበር አልሸሸጉም፡፡
« ካለ በቂ መሳሪያ ጥሩ አፈፃፀም ማስመዝገብ አይቻልም» ያሉት ተቆጣጣሪ መሐንዲሱ፤ ከዚህ ችግር ለመውጣትና ሥራውን በተቀመጠለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ሥራ ተቋራጩ አስፈላጊዎቹን መሳሪያዎች እያሟላ ነው። ይህም ግንባታውን በኮንትራት ውሉ መሰረት ለማጠናቀቅና ግንባታው በተቀመጠለት የጥራት ደረጃ መሰረት መከናወኑን ለመቆጣጠር ያስችላል።
የፕሮጀክቱ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ በኢትዮጵያ በመንገድ ግንባታ ዘርፍ የተሰማራ የመጀመሪያው የግብፅ ኩባንያ ነው፡፡"የግንባታው ሥራ ሲጀመር በማኔጅመንት በኩል ክፍተት ነበር፡፡ይህም በሥራው ላይ መጓተትን አስከትሏል "ይላሉ የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ሚስተር አይማን አተያ፡፡በአሁኑ ወቅት ሥራ ተቋራጩ አስፈላጊ መሳሪያዎችንና የሰው ኃይል በማሟላቱ ግንባታውን በታቀደለት ጊዜ በማጠናቀቅ እንደሚያስረክቡ ነው የተናገሩት።
የያቤሎ-ሜጋ መንገድ ግንባታም እ.ኤ.አ በታህሳሥ 2010 ተጀምሯል፡፡፡እ.ኤ.አ በታኅሣሥ ወር 2013 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ መንገዱ 98 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ሲሆን፤ ለግንባታውም 770 ሚሊዮን ብር ተመድቦለታል፡፡
የግንባታው ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ «ቻይና ቴሲጁ ሲቪል ኢንጂነሪንግ ግሩፕ» ሲሆን የጣልያኑ «ሬናርዴት አማካሪ መሐንዲሶች» ደግሞ የማማከሩን ሥራ ያከናውናል፡፡ የመንገዱ ግንባታ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ መሐንዲስ ተወካይ አቶ ፈለቀ በቀለ ይናገራሉ፡፡ ህብረተሰቡም የመንገዱን ልማት በመደገፍ እንደሚተባበራቸው ነው ያመለከቱት። 
የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ው ዚችው የመንገዱን ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ አሁን ባለው
አፈፃፀምም አብዛኛው የአፈር ሥራ ተጠናቋል፡፡የተወሰነ የመንገዱ ክፍልም አስፋልት ለማልበስ በሚያስችል ደረጃ ዝግጁ ተደርጓል፡፡የፍሳሽ ማስወገጃ ሥራዎችም በስፋት ተከናውነዋል፡፡ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ አጠናቆ ለማስረከብም በትኩረት እየሠራነው። 
የእነዚህ መንገዶች አካል የሆነውና 197 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የሐዋሳ-ሃገረማርያምን የመንገድ ግንባታ በ2005 ዓ.ም ለማስጀመር በሚያስችሉ ነጥቦች ዙሪያ ያተኮረ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር በሐዋሳ ከተማ ተደርጓል፡፡ግንባታውን ለማስጀመርም ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቅቆ በጨረታ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል፡፡ግንባታው ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ይፈጃል፡፡ለዚህም የአፍሪካ ልማት ባንክ 167 ሚሊዮን ዶላር ብድር ፈቅዷል፡፡ከአፍሪካ ልማት ባንክ በብድር ከተገኘው ገንዘብ በተጨማሪ ከአጠቃላይ የግንባታው ወጪ የኢትዮጵያ መንግሥት ስምንት በመቶውን ይሸፍናል፡፡ይህም መንገዱ በሚያልፍባቸው አካባቢ ለሚነሱ ነዋሪዎች የመኖሪያና የእርሻ ቦታን ለመሳሰሉ ንብረቶች ለካሳ ክፍያ የሚውል ነው፡፡ 
የመንገዱ መገንባት ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገሮች ጋር በየብስ ትራንስፖርት በማገናኘት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማጠናከር እንደሚረዳ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የደቡብ ሪጅን ጊዜያዊ ዳይሬክተር አቶ መሐመድ አብዱራህማን ይናገራሉ።«የመንገዱ ግንባታ ኢትዮጵያ የሞምባሳ ወደብን እንደ አማራጭ ለመጠቀም የምታደርገውን ጥረት ያቀላጥፋል፤ ምቹ ሁኔታንም ይፈጥራል» የሚል እምነት አላቸው።
በአፍሪካ ልማት ባንክ ዋና የትራንስፖርት መሐንዲስ ሚስተር ሙሚና ዋቼንዶም የመንገዱ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በድጋሚ ተሻሽሎ መገንባቱ ክልላዊ፤አገራዊና አህጉራዊ ፋይዳ እንዳለው ያስረዳሉ። እርሳቸው እንዳሉት፤ መንገዱ ከደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን እስከ ግብፅ ካይሮ ድረስ የሚገነባው የ"ትራንስ አፍሪካን ሃይ ዌይስ"አገናኝ መንገድ አካል ነው፡፡በመሆኑም የአፍሪካ አገሮች በመንገድ ትራንስፖርት የሚገናኙበትን ዕድል ያሰፋል፡፡ አገናኝ መንገዱ የሚያልፍባቸው አገራትን የመንገድ ትራንስፖርት ትስስር ያጠናክራል፡፡ የዚህ ጥረት ውጤትም በአምስት ዓመት ውስጥ ዕውን ይሆናል፡፡ይህም በመሆኑ የዚህ አገናኝ መንገድ አካል የሆኑ ግንባታዎችን ለሚያከናውኑት ለኢትዮጵያ፤ኬንያና ታንዛኒያ የአፍሪካ ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡ኢትዮጵያ የድርሻዋን በመወጣት ረገድ ረጅም መንገድ ተጉዛለች፡፡
በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገሮች ጋር በየብስ ትራንስፖርት ለሚያስተሳስሩ መንገዶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ቀደም ሲል አዘዞ-መተማና ጅጅጋ-ቶጎጫሌን የመሳሰሉ መንገዶች ተገንብተዋል፡፡እነዚህ መንገዶች ኢትዮጵያን ሱዳንና ከሶማሊላንድ የጎረቤት አገሮች ጋር በመንገድ ትራንስፖርት የሚያገናኙ ናቸው፡፡አማራጭ ወደብን ለመጠቀም ያስችላሉ፡፡
ግንባታቸው የተጀመሩት የሃገረማርም-ያቤሎ-ሜጋ መንገዶችም በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በባለስልጣኑ በኩል ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ነው፡፡ የመንገዶቹ ግንባታ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት ለማጐልበት፤ ማህበራዊ ትስስርን ለማጠናከርና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን ለማሳደግም ያግዛሉ፡፡ከሜጋ-ሞያሌ ያለውን የመንገድ ግንባታ ለማስጀመርም ጨረታ መውጣቱን አቶ ሳምሶን ጠቁመዋል፡፡የዚህም አሸናፊ እንደታወቀ ወደ ግንባታ ይገባል፡፡
የመንገዱ መገንባት ኢትዮጵያ ኬንያና ደቡብ ሱዳን በቀጣይ የኬንያ ወደብ ላሙን ለመጠቀም ሊገነቡ ለተስማሙባቸው የመንገድና የባቡር መስመሮችም ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል። 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር