አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ

New

አዲስአበባ፣መስከረም5 2005 (ኤፍቢሲ) የኢህአዴግ ምክር ቤት አርብና  ቅዳሜ  ባደረገው መደበኛ  ሰብሰባው የግንባሩን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር መረጠ ።

ምክር ቤቱ   አቶ  ሀይለማሪያም ደሳለኝን  የግንባሩ ሊቀመንበር አድርጎ  የመረጠ  ሲሆን ፥  አቶ  ደመቀ መኮንንን  ደግሞ በምክትል ሊቀመንበርነት መርጧል ።

የምክር ቤቱ መደበኛ ሰብሰባ ውሳኔዎችን በተመለከተ ፓርቲው  ማምሻውን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ  ቅዳሜ ከሰዓት  በኋላ  በተደረገው  የአመራር  ምርጫ  አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ከቀረቡት ሶሰት እጩዎች  መካከል ሙሉ  ድምፅ  በማግኘት ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል ።

በመግለጫው ላይ እንደተመለከተውም የአመራር  ምርጫው ከመካሄዱ በፊት  የኢህአዴግ ምክር ቤት አባላት ቀደም ሲል ፓርቲው ባስቀመጠው የመተካካት እቅድ መሰረት ምርጫው እንዲካሄድ  ተስማምተዋል ።

በቀደመው አመራር የተጀመረው  ትግል የሚቀጥለው የተለያዩ  ትውልዶች ተቀበብለውት እንደሆነ በማስመርም  የህዳሴው አመራር ሙሉ  በሙሉ  ከአዲሱ  ትውልድ  እንዲሆን  በመወሰን እጩዎች እንዲቀርቡ መደረጉን ነው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና  የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ በረከት ስምዖን ያስረዱት  ።

አቶ በረከት በኢህአዴግ አሰራርም  አሁን በሊቀመንበርነትና በምክትል ሊቀመንበርነት የተመረጡት አመራሮች የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና ምክትል  ጠቅላይ ሚኒስትር  እንደሚሆኑም አመልክተዋል ።

አዲሱ ጠቅላይ  ሚኒስትርም በአገሪቱ  ህገ በመንግሰት መሰረት  ካቢኒያቸውን ማዋቀር እንደሚችሉ የገለፁት አቶ በረከት ፥  አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝም ከፓርቲያቸው ጋር በመመካከር ካቢኒያቸውን መልሰው ሊያዋቅሩም ሆነ ሊያስቀጥሉ እንደሚችሉ ነው ያመለከቱት ።
 
  

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር