የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተቀዛቅዝዋል


ከጠ/ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ዜና ዕረፍት ወዲህ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ስራ  እንደተቀዛቀዘ ባለጉዳዮች የተናገሩ ሲሆን፤ከፍተኛ ባለስልጣኖች ለስብሰባ አዲስ አበባ መምጣታቸው እና የተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት ሳይካሄድ መቆየቱ ተጨማሪ ምክንያቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
በየመስሪያ ቤቱ የመንግስት ስራ መቀዛቀዙን የሚገልፁ ባለጉዳዮች፤ በተለይ የከፍተኛ ባለስልጣናትንና የቢሮ ሃላፊዎችን ውሳኔ የሚጠይቁ ጉዳዮች በቀጠሮ እንደተጓተቱባቸው ተናግረዋል፡፡
የጠ/ሚኒስቴር መለስ ዜና እረፍት ከተሰማበት ወቅት አንስቶ እስከ እለተ ቀብር ድረስ በአገሪቱ የነበረው የሀዘን ስሜትና ድባብ ከፍተኛ ቢሆንም፤ የመንግስት ሥራ ሳይቋረጥና ቢሮዎች ሳይዘጉ ቀጥለዋል፤ ሆኖም ስራዎች መቀዛቀዛቸው አልቀረም ይላሉ ባለጉዳዮች፡፡
በቀብር ስነስርዓቱ ማግስት ጊዜያዊ ጠ/ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በሰጡት መግለጫ፤ ሁሉም ሰው በቁጭትና በተጨማሪ ብርታት ወደ ስራ እንዲመለስ ማሳሰባቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በበርካታ ቦታዎች መደበኛ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ይሁንና በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ የመንግስት ቢሮዎች፤ ቀጠሮ ተይዞላቸው የነበሩ ጉዳዮች ውሳኔ ሳያገኙ በቀጠሮ እንደተራዘሙባቸው የሚገልፁ ባለጉዳዮች፤ በርካታ ከፍተኛ ባለስልጣናት በቢሮዋቸው እንደማይገኙ ተናግረዋል፡፡
በርካታዎቹ ባለሥልጣናት ሰሞኑን የኢህአዴግ ምክር ቤት ለሚያካሂደው ስብሰባ አዲስ አበባ መግባታቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ በዚህ ምክንያት ብዙ ባለስልጣናት በቢሯቸው እንዳይገኙ አንድ ምክንያት ሊሆን ይችላል ተብሏል፡፡ 180 አባላትን የያዘው የኢህአዴግ ምክር ቤት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅዱን በተመለከተ ውይይት እንዲካሄድ፤ የፅሁፍ ሰነዶች ተዘጋጅተው ለሁሉም የአመራር አባላት እንደተሰጠ ምንጮች ጠቅሰዋል፡፡ የስብሰባው ዋና አጀንዳ ግን ተተኪ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና ምክትል መሰየም ነው ተብሏል፡፡
አራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እጩ ሊቀመንበር ለምርጫ እንዲያቀርቡ ተጠይቀዋል ያሉት ምንጮች፤ ሦስቱ ድርጅቶች እጩ ማቅረባቸውን ገልፀዋል፡፡ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ አቶ ግርማ ብሩ፣ እና አቶ ደመቀ በእጩነት እንደቀረቡም ምንጮች ተናግረዋል፡፡ የኢህአዴግ ሊቀመንበር እና ምክትል ሆነው የሚሰየሙ መሪዎች፤ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ምክትል እንዲሆኑና ሹመታቸው እንዲፀድቅ ወደ ፓርላማ ይቀርባሉ ተብሏል፡፡
የኢህአዴግ መሪዎች ለስብሰባ ከመጠራታቸው በተጨማሪ፤ ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሾም መቆየቱ የመንግስት ቢሮዎችን ስራ ሳያቀዘቅዝ እንዳልቀረ የተናገሩ ባለጉዳዮች፣ ስብሰባው ሲጠናቀቅና ሹመቶቹ ሲፀድቁ ስራ ይነቃቃል ብለው ተስፋ አድርገዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ከጠ/ሚ መለስ ዜናዊ እረፍትና የቀብር ስነስርዓት በኋላ ያለው ድባብ የቤት አስተዳዳሪ ወይንም አባወራ ሲሞት እንደሚቀዘቅዘው የቤተሰብ ኑሮ ይመስላል በማለት የተናገሩ ባለጉዳዮች፤ ሁኔታው መስተካከል እንዳለበት ይገልፃሉ፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር