ምክር ቤቱ የሕዳሴ ጉዞን በሚያስቀጥሉ አቅጣጫዎችና ስልቶች ላይ ከስምምነት ደረሰ




አዲስ አበባ፡- የኢህአዴግ ምክር ቤት ሕዝቡን በማሳተፍ የተጀመረውን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ የሕዳሴ ጉዞ ለማስጠቀል በሚያስችሉ አቅጣጫዎችና ስልቶች ላይ ከስምምነት ላይ ደረሰ።
የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ለዝግጅት ክፍላችን እንዳስታወቀው፤ የሕዳሴውን ጉዞ መላው የግንባሩ አባላትና የትግሉ ደጋፊዎች እንዲሁም የለውጡ ባለቤቶችና ተጠቃሚዎች የሆኑት መላው ኢትዮጵያውያንን በማሣተፍ ማስቀጠል እንደሚገባ ምክር ቤቱ ስምምነት ላይ ደርሷል።
ትናንት የተጀመረው የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ለታላቁ የድርጅቱ ሊቀመንበር ለክቡር አቶ መለስ ዜናዊ የሕሊና ፀሎት በማድረግ ተከፍቷል። ከአራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች በእኩል ድምፅ የሚወከሉት የምክር ቤቱ አባላት ምልዓተ ጉባኤ መሟላት መሠረት በማድረግ ከሕሊና ፀሎቱ በኋላ ለምክር ቤቱ በመወያያነት በቀረቡት አጀንዳዎች ዙሪያ ተወያይቶ በማፅደቅ ሥራውን ጀምሯል። በዚሁ መሠረት በሁለቱ ቀናት ምክር ቤቱ ለመወያየት ከያዛቸው አጀንዳዎች መካከል በቅድሚያ፡-የሚመክረው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ተግባራዊ ልዕልናን በማረጋገጥ የመለስ/ኢህአዴግን ራዕይ ለማሳካት እንረባረብ በሚል ርዕስ የተዘጋጀና በታላቁ መሪና በድርጅቱ አመራር የተገኙትን ስኬቶች ማስቀጠል በሚቻልባቸውና ቀጣይ ፈተናዎችን ለመቋቋም በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ነው። ከዚህ በማስቀጠልም ታላቁ መሪ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ተዘጋጅቶ በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውይይት ተደርጎበት የነበረው የአመራር ግንባታና የሕዳሴው ጉዞ በሚል ርዕስ ኪራይ ሰብሳቢነትን ከምንጩ ለማድረቅና የሕዝቡን ዘላቂ ጥቅምና ተጠቃሚነት በሕዝቡ የተደራጀና ቀጣይነት ያለው ንቅናቄና ተሣትፎ ማረጋገጥ ይቻል ዘንድ እና ከዚሁ ሂደት ጠንካራ የድርጅትና መንግሥት አመራር መፍጠር በሚቻልባቸው የአሠራር የአደረጃጀትና የአስተሳሰብ አቅም ግንባታ አቅጣጫዎች ዙሪያ በተዘጋጀ ጽሑፍ ላይ ይመክራል። 
ሦስተኛው አጀንዳ በእነዚህ አጠቃላይ አቅጣጫዎች ተመስርቶ በ2005 በመንግሥት ድርጅት ዘርፍ መከናወን በሚገባቸው የልማትና መልካም አስተዳደር እንዲሁም የፖለቲካና ድርጅት ሥራዎች አጠቃላይ አቅጣጫዎች ዙሪያ የሚመክር ሲሆን፤ በመጨረሻ የታላቁ መሪ የክቡር አቶ መለስ ዜናዊን ሕልፈት ተከትሎ የተፈጠረውን የአመራር ክፍተት የድርጅቱ ሕገ ደንብ በሚያዘው መሠረት ምርጫ በማካሄድ እንደሚሞላ ይጠበቃል።
ምክር ቤቱ ትናንት ቅድሚያ ሰጥቶ በተወያየበት የመጀመሪያው አጀንዳ ዙሪያ በመከረበት ወቅት ከአቶ መለስ ሕልፈት በኋላ በአገራችንና በአካባቢያችን እንዲሁም ከእኛ ሁኔታ ጋር በተያያዙ በሌሎች የዓለም ክፍሎች የተፈጠረውን ሁኔታ በመገምገምና ከዚህም በመነሳት በአገራችን መካሄድና ይበልጥ መጠናከር ያለበትን የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አጠናክሮ ማስጠቀል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክሯል። በተጨማሪም የአቶ መለስን ሕልፈት ተከትሎ መላው የአገራችን ሕዝቦችና አፍሪካውያን ወገኖቻችን እንዲሁም ታላላቅ የዓለም ተቋማትና ሀገራት መሪዎች ለታላቁ መሪያችንና በእርሱም አመራርነት በሀገራችን ለተመዘገበው ለውጥ የሰጡትን ታላቅ አክብሮትና እውቅና በማድነቅና ምስጋናውን በማቅረብ ከተሰጠው ምስክርነት ጋርም ለድርጅቱ የተሰጠው አደራ ከፍተኛ መሆኑን ተገንዝቧል። በዚሁ መሠረት መላውን የድርጅቱን አባላትና የትግሉን ደጋፊዎች እንዲሁም የለውጡ ባለቤቶችና ተጠቃሚዎች የሆኑትን መላውን የኢትዮጵያ ሕዝቦችን በማሣተፍ የተጀመረውን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ የሕዳሴ ጉዞ ለማስቀጠል በሚያስችሉ አቅጣጫዎችና ስልቶች ዙሪያ መክሮ ከስምምነት ላይ ደርሷል። ውይይቱ በዛሬው ዕለትም በሌሎች ጭብጦችና አጀንዳዎች ዙሪያ የሚያደርገውን ውይይት ይቀጥላል።
በዚህ የኢህአዴግ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ የሶማሌ፣ የአፋር፣ የሐረሪ፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝና የጋምቤላ ክልሎች አጋር ድርጅቶች ሊቀመናብርትና የየክልሎቹ ፕሬዚዳንቶች በተጋባዥነት ተሣትፈዋል። 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር